የኢንተርኔት የመረጃ መረብና ጦርነቱ፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 15.12.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የኢንተርኔት የመረጃ መረብና ጦርነቱ፣

በየጊዜው፣ ከዓመት -ዓመት፣ በሳይንስ የሚደረገው ምርምር ፣ በሥነ ቴክኒክ ረገድ የሚቀርበው የፈጠራ ውጤት ፣ የሰውን ልጆች አኗኗር ለማቅለል፣ ለወቅታዊ ችግሮች መላ ለመሻት መሆኑ ቢታሰብም፣ ከቅንጦት ጋር የተያያዘም እንደሚገኝበት የሚያጠራጥር አይደለም።

default

የ«ዊኪሊክስ» መስራች ጁልያን አሳንጅ፣

በዛሬው ሳይንስና ኅብት ረተሰብ ቅንብራችን፣ በማክተም ላይ ባለው 2010 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ፣ ጠቃሚም አሳሳቢም ሆነው ከተገኙት ፣ በተለይ በሥነ-ቴክኒኩ ረድፍ፣ በመረጃው ሥነ ቴክኒክ ፣ በኩል የተከሠተውን ግብግብ እንዳስሳለን።

የሰውን ልጅ ጤንነት ለማሻሻል ፤ ምድራችንን ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ፣ የባህርን ፣ የአየርንና የየብስን ይዞታ በተቻለ ንፅህና ለመጠበቅ የሚውሉ የሥነ ቴክኒክ ፈጠራዎች በየጊዜው ተከሥተዋል። አየርን ከብክለት ለማዳን ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አውቶሞቢሎች ለናሙና ያህል ቀርበዋል። በሃድሮጂን ጋዝ የሚሽከረከሩ መኪናዎች፣ ሌሎችን ሁሉ እንዲተኩ ማድረግ እንደማያቅትም፣ የሥነ-ቴክኒክ ተመራማሪዎችና ቴክኒሺያኖች ሲናገሩ ዓመታት አልፈዋል። በኤሌክትሪክ የሚሠራ አኤሮፕላንም ፣ ይበልጥ የተሻለ መሆኑን ፣ ኃይለኛውን ድምጽም በዚህ ረገድ መግታት እንደሚቻል፣ በሙከራ መረጋገጡን ፣ በዚህ ዓመት ባቀረብናቸው ዝግጅቶች ጠቁመናል። ያለዘዋሪ ከቦታ -ቦታ የሚሽከረከሩ የታክሲ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አውቶሞቢሎችን ማሠማራት እንደማያቅት ተረጋግጧል። ለጊዜው ለህዝብ የሚፈቀድ ባይሆንም ፣ ለህክምና እርዳታ አቅራቢ ክፍሎችና ለመከላከያ መ/ቤቶች አገልግሎት መስጠት የሚችሉ በየብስ ሲሽከረከሩ ቆይተው እንደአስፈላጊነቱ እንደ አሞራ ብድግ ብለው የሚበሩ ተሽከርካሪዎችም ተሠርተዋል። አሽከርካሪዎች ሲደክማቸው የዓይናቸውን ይዞታ ተከታትሎ ማስጠንቀቂያ ምልክት የሚሰጥ መሳሪያም ፣ በተለይ ለአውቶቡስ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች የሚውል ተሠርቷል። ከትራፊክ መብራት ጋር በምልክትና በድምፅ የመረጃ ልውውጥ የሚያደርግ መሳሪያ የተገጠመላቸው የ Audi መኪና አሽከርካሪዎች ፍጥነት የት መቀነስና መጨመር እንደሚኖርባቸው ያውቃሉ። በዚህ አጠቃቀም ነዳጅ አላግባብ ማባከንም አይችሉም። አውቶሞቢሎቹ የሚተፉት የተቃጠለ አየር መጠንም ጥቂት ስለሚሆን የአየር ብክለትን ለመግታት ጠቀሜታ አለው። እ ጎ አ በ 2006 እንግሎሽታት በተሰኘችው ከተማ የተጀመረው የሥነ-ቴክኒክ ምርምር በአሁኑ ጊዜ በሰፊው ተሻሽሎ አጥጋቢ ውጤት ማስገኘቱ እየተነገረለት ነው። በዩናይትድ እስቴትስና በጀርመን በተጠቀሰው ዘዴ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች፣ 17 ከመቶ ነዳጅ መቆጠብ እንደሚችሉ፣ እ ጎ አ በ 2006 አዲሱ ሥነ ቴክኒክ ሲሞከር ለማረጋገጥ ተችሎ እንደነበረ ታውቋል። ለምሳሌ በጀርመን እንደሚባለው እያንዳንዱ ተሽከርካሪ በተጠቀሰው የሥነ ቴክኒክ መሣሪያ (Travolution)ቢገለገል በያመቱ የተቃጠለ አየር መጠንን በ 2 ሚሊዮን ቶን መቀነስ በተቻለ ነበር። በከተሞችም የተቃጠለ አየር መጠን በ 15 ከመቶ ይቀንሳል። ዘንድሮም ሆነ ባለፉት ጥቂት ዓመታትም፣ በሥነ ቴክኒክ ስለተደረጉ ግሥጋሤዎች በዚህ ክፍለ-ጊዜ ምንጊዜም መለስ ብለን መዳሰሳችን የማይቀር ነው ለዛሬ ግን ይበልጥ ለማትኮር የምንፈልገው፣ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው በኢንተርኔት በኩል በሚደረገው፣ ሥነ-ቴክኒክ ባስገኘው ጥበብ በሚከናወነው፣ የሰነድ ምሥጢር የመጠበቅና ፣ ሰነድ የመዝረፍ ይሁን የማጋለጥ ጦርነት በተሰኘው ጉዳይ ላይ ነው።

የምንኖርበት ዘመን በመረጃ አሰባሰብና አጠቃቀም፣ አብዮት የተካሄደበት ነው። የመገናኛው አገልግሎት በእጅጉ ተስፋፍቷል። ሰፊ መረጃ በቀላል መሣሪያ የሚጠራቀምበት ሥነ ቴክኒክም ተራቋል። 2010 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት፣ የኢንተርኔት የመረጃ ሥነ ቴክኒክ፤ በውትድርናው ዘርፍ ያለውን ምሥጢራዊ ሰነድ ሠርስሮ ለማወቅ እስከምን ድረስ ጥረት እንደተደረገ የታየበት ዘመን ተብሎ በታሪክ የሚመዘገብበት ሁኔታ ሳይኖር አይቀርም።

Stuxnet የተባለውን ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር የተከሠተውን ልዩ የኮምፒዩተር መርኀ- ግብር የሚያፋልስ ፤ የሚያበላሽ፣ ሰው ሠራሽ የሥነ ቴክኒክ ተኀዋሲ ተግባር ልብ ይሏል። «እስታክስኔት» ፣ የደባ ተግባር እንዲያከናወን የተዘጋጀ፣ የኢንዱስትሪ አውታሮችን ሥራ የሚያጨናግፍ ሰው- ሠራሽ ተኀዋሲ ነው። ይኸው «ሶፍትዌር»፤ በርከት ያሉ የመረጃ ሥነ ቴክኒክ ጠበብት እንደሚሉት ፣ ምንጩ፣ ትክክለኛ ዒላማው፣ ፣ ደራሲውም ሆነ ደራሲዎቹ አይታወቁም። ይሁን እንጂ፤ የኢራንን የአቶም መርኀ-ግብር በተለይም ዩሬኒየምን ለአቶም ማገዶ ለማዋል የሚሠራበትን ዘዴ እንዲያሠናክል የተሞከረበት ነው።

እስታክስኔት በዓለም ዙሪያ፣ የኢንዱስትሪ አውታር ማንቀሳቀሻ መርኀ ግብሮችን ለምሳሌም ያህል የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮችን የሥነ ቅመማ ፋብሪካዎችን፤ ወይም የነዳጅ ማጣሪያ ማዕከላትን፣ እንዲያሠናክል የሚያደርግ በመሆኑ በጥሞና ሊታስብበት ይገባል የሚሉ ጠበብት ጥቂቶች አይደሉም። በቦን የሚገኘው ፤ የጀርመን የመረጃ ሥነ ቴክኒክ ማዕከል የደኅንነት ጉዳይ ተጠሪ እስቴፋን ሪተር እንዲህ ይላሉ።

1,«አንድ የተገኘ መረጃ አለ። እንዲሁ እንደዋዛ የሚነገር ማስጠንቀቂያ ወይም ጠበብት እንዲሁ በጓዳ የሚመክሩበት አሥጊ ነገር አይደለም። በእርግጥ ተጨባጭነት ያለው እጅግ አደገኛ ጉዳይ ነው። »

የዚህ አሰናካይ አቅድ ሁኔታ ያሳሰበቻቸው የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ድርጅት (ኔቶ)አባል ሀገራት መሪዎች፣ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ሊዝበን ፣ ፖርቱጋል ውስጥ ባካሄዱት ጉባዔ፣ ከአሸባሪነትና ጅምላ ጨራሽ ጦር መሣሪያ ሌላ፤ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ከሩቅ በመገናኛ አውታር በኩል ሊሠነዘር የሚችል ሥውር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል ስልት እንዲቀየስ መስማማቱ የሚታወስ ነው። ይኸው ስልት የተዘጋጀው የቀድሞዋ የዩናይትድ እስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ወ/ሮ ማርሊን ኦልብራይት በሊቀመንበርነት በሚመሩት ቡድን ነው።

2,«የመረጃ መለዋወጫው የኮምፒዩተር መረብ ሊተኮርባቸው ከሚገባ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን አውቀናል። »

በዩናይትድ እስቴትስ ጦር ኃይል ውስጥ፤« የኮምፒዩተር መረብ እዝ» የሚባል ክፍል አለ። ይህን የሚመሩት ጀኔራል ኬይት አለክሳንደር የተባሉት የስለላው አገልግሎት ኀላፊ ናቸው።

3, በ«ኮምፒዩተር እዝ» በኀላፊነት የምንገኝ ሰዎች፤ የዕለቱን ተግባር መቆጣጠር ፤ የመከላከያ ሚኒስቴሩን የመረጃ መረብ መጠበቅ ፣ ከመከለከያ ሚንስቴሩ የአሠራር ሥነ ሥርዓት ጋር የተስማማ አቅድን መከተል፤ ወሳኝነት ያላቸውን የኮምፒዩተር መረብ የሥራ እንቅሥቃሴዎችን ማቀናጀት ነው ሥራችን። ከፕሬዚዳንቱ፤ ከመከላከያ ሚንስትሩና ከስልታዊ ልዩ ጦር አዛዦች፤ መመሪያ ከተሰጠንም ፣ ወታደራዊውን የኮምፒዩተር መረብ ግብረ ኃይል ለዩናይትድ እስቴትስና ለተጓዳኞቿ ነጻነት ስንል እናሠማራለን።»

ዋሽንግተን ፖስት የተባለው ጋዜጣ እንዳብራራው ከሆነ፣ በጥቅምት ወር መጨረሻ ገደማ ላይ፣ «የኮምፒዩተር መረብ እዝ » የተባለው ጦር ክፍል እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ባሳወቀ በ 3ኛው ቀን፤ ጀኔራል አሌክሳንደር በሰጡት ቃል፤ የአሜሪካን ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኮምፒዩተር መረቦች በመላ ጥቃት እንዲሠነዝርባቸው የሚሹ መሆናቸውን በግልጽ ነበረ የተናገሩት።

ይህም ማለት ፣ ባለፈው ሐምሌ ወር 3ኛ ሳምንት ገደማ ላይ የአፍጋኒስታኑን ጦርነት በተመለከተ ከሞላ ጎደል 80ሺ ምሥጢራዊ ሰነዶችን ይፋ ያደረገውን «ዊኪሊክስ» የተሰኘውን የኢንተርኔት መረብ ስንክልክሉ እንዲወጣ ማድረግን ይመለከታል ማለት ነው። የአሜሪካ ጦር ኃይል በዊኪሊክስ ተግባር በግኗል። የመከላከያ ሚንስትር ሮበርት ጌትስ፣ የዊኪሊክስ መሥራች ጁሊያን አሳንጅ ብርቱ ጉዳት እንዲከተል አድርጓል በማለት ብርቱ ዘላፋ ማሰማታቸው የሚታወስ ነው።

4,«እነዚህን ሰነዶች ይፋ ማድረጉ፤ በዐውደ-ውጊያው ላይ ከባድና አደገኛ ክስተትን በወታደሮቻችንና በተጓዳኞቻችን ላይ አስከትሏል። በአነዚህ ወሳኝነት ባላቸው አገሮች፣ ያለንን ስምና ግንኙነታችንንም መቅኖ የሚያሳጣ ነው።»

ጁልያን አሳንጅ፣ ዝም አላሉም ወዲያው አጸፋዊ መልስ ሰጥተዋል።

5,«የመከላከያ ሚንስትር ጌትስ በመላምትነው ስለደም መፍሰስ የሚናገሩት። ይሁን እንጂ፤ በኢራቅና በአፍጋኒስታን አፈሩ በደም የራሰ ነው። የመከላከያ ሚንስትሩ፣ በእነዚህ አገሮች፣ በሺ የሚቆጠሩ ህጻናትና ትልልቆች እንደሚሞቱ ያውቁ ነበር።»

ዊኪሊክስ፣ ጥቅምት 12 ቀን 2003 ዓ ም፣ የኢራቁን ጦርነት የሚመለከት ወደ 400,000 የሚጠጋ ምሥጢራዊ ሰነድ ይፋ ካደረገ በኋላ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ ኅዳር 20 የአሜሪካን የውጭ አመራር የሚያስደነግጥ፣ ዲፕሎማቶቿ ያስተላለፏቸውን 250,000 ምሥጢራዊ ሰነዶችን በኢንተርኔት መረብ መበተኑ የሚታወስ ነው። የአሜሪካ መገናኛ ብዙኀን እንደሚገምቱት ሰነዶቹን 2,5 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ሳያገኙ አልቀሩም።

ይህ ፤ በእርግጥ፣ የጠላትነት ተግባር ወይስ ህዝብ ሊያውቅ የሚገባው ነው በማለት የተወሰደ የታታሪ ጋዜጠኞች አሠራር ዓይነት ነው? እንዳከራከረ ያለ ጉዳይ ነው።

እዚህ ላይ ፤ በከፊል ዘመናዊው የመረጃ መለዋወጫ ፣ ሥነ-ቴክኒክ እመርታ ያስገኘው ውጤት መሆኑን አሌ ማለት አይቻልም።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ