የኢንተርኔት እገዳ በካሜሩን | አፍሪቃ | DW | 09.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኢንተርኔት እገዳ በካሜሩን

ካሜሩን በእንግሊዘኛ ተናጋሪ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ካገደች ትናንት 50 ቀን ሞላው ። መንግሥት እርምጃውን የወሰደው እንግሊዘኛ በሚናገሩት በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች  የተቃውሞ ጥሪዎችን ለማስቆም ነው ። እገዳው የኢንተርኔት የገንዘብ ልውውጦችን አሽመድምዷል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58

50 ቀናት ያለ ኢንተርኔት

በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች« ኢንተርኔታችንን መልሱልን »«ኢንተርኔታችንን መልሱልን »እያሉ ይጮሀሉ ። ወጣቶቹ ይህን የሚሉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቢያ በእንግሊዘኛ ተናጋሪዎቹ በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ካሜሩን አካባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን እና የንግድ እንቅስቃሴም እንደ ቀድሞው እንዲቀጥል እንዲደራደሩ ወደ አካባቢው የላኳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ፊሌሞን ያንግን አናሳልፍም ብለው እየታገሉ ነው ።ተቃዋሚዎቹ  ያለ ኢንተርኔት ሰላም ሊኖር አይችልም ነው የሚሉት ። ከመካከላቸው አንዱ በድሀ የአፍሪቃ ሀገራት የሚገኙ ጎበዝ ተማሪዎች በለሙ ሀገራት ነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙ አገናኝ ሆኖ የሚያገለግለው ኦፕን ድሪምስ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ አካባ ጀምስ ነው ። 
«ኢንተርኔት ለኛ እንደ ኦክስጂን ነው .በእያንዳንዱ ደቂቃ በእያንዳንዱ ጊዜ እንጠቀምበታለን ። እናም ኦክስጂን እንደተወሰደብን ነው የምንቆጥረው ።በዚህ ምክንያት ሁሌም ወደ ያዉንዴዋ ባፉሳም እንጓዛለን ። ውጭ ከሚገኙ በርካታ ዩኒቨርስቲዎች ጋር እንሰራለን ።ውጭ የሚገኝትን እና እዚህ ያሉትን ተማሪዎችን  እናገናኛለን ።በርካታ ምርምሮችም እናካሂዳለን ።እንደ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉልን አጋሮቻችን ሁል ጊዜ ሪፖርት ማቅረብ አለብን ።ይህን ማድረግ አልቻልንም ። ይህ ለኛ ትልቅ ችግር ነው ። »
ጀምስ የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ወዲህ ዋና ከተማይቱ ያውንዴ ነው ያለው ። ከያዉንዴ የመጣው አገልግሎቱ እንዲቀጥል ግፊት ለማድረግ ነው ። ካናዳ መማር የሚያስችለው የነፃ ትምሕርት እድል ያገኘው የ18 ዓመቱ ሙሀማዱ አወልም ለትምህርቱ ድጋፍ ከሚሰጡት ጋር በኢንተርኔት መገናኘት እንዲችል ወደ ያውንዴ ሄዷል ።ይሁን እና ሙሀማዱ እንደሚለው ሁሉም

ተማሪዎች ይህ እድል አላቸው ማለት አይደለም ።«እያሽመደመዳቸው ነው ምክንያቱም ለነፃ ትምሕርት እድል ማመልከት አይችሉም ።እኔ ካመለከትኩ በኋላ ነበር የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠው ። በዚህ የተነሳም ሚቡዲ ፣ባፉሳን እና ያውንዴም ድረስ እንሄድ ነበር ። »
ሥራቸው ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ ተመራማሪዎችም ችግር ላይ ወድቀዋል ። «ድንበር የለሹ ኢንተርኔት»የተባለው የኢንተርኔት አገልግሎትን እና ሃሳብን በነፃ መግለፅን የሚያበረታታው ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ኢንተርኔት መዘጋቱ ኤኮኖሚውን እየጎዳ ነው ።በኢንተርኔት የሚካሄዱ ክፍያዎች እና የገንዘብ ዝውውሮች ጥናቶች እና ሌሎች አገልግሎቶች መሰናከላቸው ኤኮኖሚውን ለጉዳት ከዳረጉት ምክንያቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው ። በተመድ የሰብዓዊ መብቶች አጥኚ ዴቪድ ኬይ በካሜሩን የተወሰኑ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲዘጋ መደረጉን ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብትን በእጅጉ የሚጋፋ ሲሉ ነቅፈው መንግሥት አገልግሎቱን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ።ይሁንና ትናንት ኢንተርኔት ከተከለከለባቸው አካባቢዎች ባሜንዳን የጎበኙት  የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፊልሞን ያንግ  ግን በተቃውሞ ሰበብ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንደገና መከፈትና የተገቱ የንግድ እንቅስቃሴዎችም መቀጠል ላይ ነበር ያተኮሩት ።  
« በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ፍርሃትን መንዛት ማቆሚያ ጊዜው አሁን ነው ። ፍርሀት ሀገርን ሊገነባ አይችልም ። ፍርሀት በራስ መተማመን ያሳጣል ። ፍርሀትን በንጹሀን ልጆች ወላጆች እና ነጋዴዎች ላይ መንዛትን ሁላችንም መቃወም አለብን ። »
ጠቅላይ ሚኒስትሩ  በተገኙበት ስብሰባ ላይ የተካፈሉት የኢንተርኔት ካፌ ባለቤት አሶንግዌ ኤትየን እንደነገሩዋቸው ግን የኢንተርኔት እገዳ ካልተነሳ እና የታሰሩ ካልተፈቱ ፣ትምሕርት ቤቶች ፈጽሞ አይከፈቱም ፤ ኦና የሚቀሩ ከተሞችም በየሳምንቱ  በእጥፍ ይጨምራሉ  ።ካለፈው ህዳር አንስቶ በእንግሊዘኛ ተናጋሪዎቹ አካባቢዎች መምህራን እና ጠበቆች የሥራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው ።አካባቢዎቹ እንዲገነጠሉ የሚሟገቱ ወገኖችም ከነርሱ ጋር አብረዋል ። አንዳንድ የተቃውሞ ሰልፎች ብጥብጥ አስከትለው በርካቶች ታስረዋል ። 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች