የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በኢትዮጵያ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 02.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎቱ ድርግም ብሎ ሲጠፋ ዓለም በአንጻሩ በዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ተጀምሮ ያላለቀ ትዊተር መልእክት ሲሳለቅ ለሊቱን አጋምሷል። በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥን በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተሰጡ አስተያየቶች ምን ይመስላሉ?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:51

ሄድ መለስ የሚለው የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ ኢትዮጵያ ከተነገረ ወዲህ የኢንተርኔት አገልግሎት ሄድ መለስ ማለቱ የተለመደ ይመስላል። አንድ ጊዜ የተንቀሳቃሽ ስልኮች ዳታ አገልግሎት ሲቋረጥ ሌላ ጊዜ በገመድ ግንኙነት የሚያደርገው ይሠራ ነበር። ከማክሰኞ የጀመረው ግን ለየት ያለ ነው። በኢትዮጵያ ከጥግ እስከ ጥግ ሊባል በሚችል መልኩ የኢንተርኔት አገልግሎት ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ መቋረጡ ታውቋል። እንዲያም ኾኖ ግን ቴሌ ኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤትን ጨምሮ አንዳንድ ተቋማት የኢንተርኔት አገልግሎት ተነጥሎ እየተሰጣቸው መኾኑን የሚናገሩ አሉ። የዛሬው የማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ቅኝት መሰናዶዋችን ማጠንጠኛ ነው።

ረቡዕ ግንቦት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. እኩለ-ሌሊት። የኢንተርኔት አገልግሎት ለ24 ሰአታት በቀላሉ የሚያገኘው ሌላው የዓለም ክፍል አንዳች የሚሳለቅበት ነገር ይዟል።  የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ተጀምሮ ያልተቋጨ ምናልባትም በስህተት ኢንተርኔት ውስጥ የገባ የትዊተር መልእክት ላይ ዓለም ሌሊቱን ሲያላግጥ ነው ያደረው። ፕሬዚዳንቱ ባልተቋጨ መልእክታቸው ውድቅት ላይ በእንግሊዝኛ የማይታወቅ ቃል መጠቀማቸው፤ ትንሽ ቆይ መልእክቱን ከኢንተርኔት መደምሰሳቸው እና የቃል ስህተት እንዳልተደረገ መስለው ከ20 ደቂቃ በኋላ በሌላ የትዊተር መልእክት ብቅ ማለታቸው በመላው ዓለም ለኢንተርኔት ሥላቅ ዳርጓቸዋል። 

Einfach mal den Stecker ziehen

በዛች ውድቅት ግን መላ ኢትዮጵያ እንደ ድቅድቁ ጭለማ የኢንተርኔት አገልግሎቱ ተቋርጦ ጽልመት ውጦታል። ዓለም ላይ ምን እየተከሰተም ላያውቅ ኢንተርኔቱ ድርግም ብሎ ጠፍቶ ነበር። ወትሮ የሞባይል ዳታ ኢንተርኔቱ ሲቋረጥ  በተለያዩ ዘዴዎች ከኢትዮጵያ በትዊተር እና በፌስቡክ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ የነበሩ ተጠቃሚዎችም በዚህ ሳምንንት ከመስመሩ ጠፍተዋል። ኢንተርኔት በኢትዮጵያ ስለመቋረጡ እና ሀገር ውስጥ ስላለው ኹኔታ ደውለው በመጠየቅ መልሰው ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ አስተያየት የሚሰጡት እውጭ ሀገር ነዋሪ የሆኑ ተጠቃሚዎች ናቸው።

በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ሠራተኛ የነበሩ የቀድሞ ባለሙያ አሁን በስደት የሚኖሩ አንድ አድማጫችን  የኢንተርኔት መቋረጥ ሒደቱ ተደጋጋሚ እንደሆነ እና «ፍራቻ ሲኖር ሊቋረጥ» እንደሚችል ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኢንተርኔቱ መቋረጥ ሰበብ የ10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተጀመረበት ወቅት በመሆኑ ነው፤  ያ ደግሞ ተገቢ ነው ሲሉ አስተያየት የሰነዘሩ አልጠፉም። በዋትስ አፕ ከደረሱን መልእክቶች የአንዱ እንዲህ ይነበባል፦ «ለተፈታኞች መልካም ፈተና እንዲሆን እየተመኘው እንደ አምናው የጎበዝ ተማሪዎች ዓዕምሮ እንዳይረበሽ በጥብቅ እንደሚሠራ አምናለሁኝ። እናመሰግናለን መልካም የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተፈታኞች» መልእክቱ የደረሰን ከሱዳን  ነው። ዓምና የፈተናው ሾልኮ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ መበተኑ እና ብዙ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወሳል።

ዳዊት ፈቃዱ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንዲህ ሲል ሲል ጽፈዋል። «እንደፈለጋቸው የሚዘጉት የሚከፍቱት ኢንተርኔት ዛሬም በፈተና ሰበብ ከማክሰኞ ጀምሮ ቆልፈውታል!» ከሳዑዲ ዓረቢያ ረቡዕ ዕለት የድምጽ መልእክት በዋትስ አፕ አድራሻችን የላኩልን አድማጫችን በበኩላቸው የኢንተርኔት መቋረጡ በሰበብ አስባቡ የሚደጋገም መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢንተርኔት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡ ይፋ በሆነበት ቀን ማለትም ከትናንት ወዲያ ኢንተርኔትን በመጠቀም በዋትስአፕ ከኢትዮጵያ መልእክት ደርሶናል። መልእክቱ እንዲህ ይነበባል፦ «ኢንተርኔት የተቋረጠው ትናንት 8 ሰአት ላይ ነው። እስካሁን አይሠራም ግን በፊሲፎን የሚባል ማስተናበሪያ (apps )እየተጠቀምን ነው»።

ቀደም ሲል በኢትዮ ቴሌኮም ውስጥ ሠራተኛ የነበሩትድ አድማጫችን በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰዎች ኢንተርኔት እንደሚጠቀሙ ደውለው ማረጋገጣቸውን ገልጠውልናል። ትእዕግስት ኤም የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ሰዎች ፌስ ቡክ ሲጠቀሙ መመልከታቸውን ጽፈዋል።  

በዶቸቬለ  ፌስቡክ ገጽ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፦ «ሲጀመር የተሟላ ኢንተርኔት አለ እንዴ?» ያሉን ደብረ እጅጉ የተባሉ ተከታታያችን ናቸው። ሠላም አብደላ ደግሞ «ያለችውም ከጠፋች ሳምንት አለፋት!!» ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። እንዳለው ፍስሐ በበኩላቸው «ተቋርጧል የሚባለው የተሞላ ኢንተርኔት አገልገሎት ሲኖር ነው» ብለዋል።

ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የትምህርት ሚንሥትር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወሮ ሐረጓ ማሞ የኢንተርኔት መቋረጡ ከፈተናው ጋር ግንኙነት እንደሌለው ገልጠዋል። «ምንም ከፈተናው ጋር በተያያዘ ኢንተርኔት አይዘጋም። ፈተናው በተሳካ ኹኔታ እየተከናወነ ስለሆነ ምንም ከፈተናው ጋር ተያያዥነት የሚኖረው አይመስለኝም፤ ያለውም አይደለም»

የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ  የህዝብ ግኑኝነትና የኮሙኒኬሼን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረዲ ሽፋም ተቀራራቢ መልስ አላቸው። መሥሪያ ቤታቸው ቴሌ ኮሙኒኬሽንንም ሆነ መንግሥትን «ቀጥታ አቅጣጫ ሰጥቶ በዛ መልኩ የተዘጋበት ኹኔታ» እንደማያስታውሱ ለዶይቸ ቬለ ገልጠዋል።

ኢንተርኔት በኢትዮጵያ  የተቋረጠበትን ምክንያት እንዲነግሩን  የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽቤት እንዲሁም የኮሙኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ሚንሥቴርን ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን ሙሉ ለሙሉ ለማቋረጥ ከቻይና በኩል የገነባችውን አቅሟን እየፈተሽ ነው ብለዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic