የኢንተርኔት አገልግሎትና ተማሪዎች | ባህል | DW | 28.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የኢንተርኔት አገልግሎትና ተማሪዎች

እስቲ የተወሰኑ አመታት መለስ ብለን እናስብ፤ የኢንተርኔት አገልግሎት ባልነበረበት ጊዜ። ማንኛውንም መልዕክት ይሁን መረጃ ለማግኘት ከባድ እና ጊዜን የሚወስድ ነበር። የኢንተርኔት አገልግሎት ለትምህርት፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ለመገናኘትም ይሁን ዜና እና መረጃን ለማግኘት ምን ያህል ጠቅሞናል? ጉዳቱስ እንዴት ይገለፃል?

በበርካታ የዓለማችን ክፍል እንደ ፌስቡክ ያሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች፣ ዮ-ቲውብ እና ጉግል ውስጥ ገብቶ መረጃ መፈለግ ፤ ከወጣቱ የዕለት ከዕለት ህይወት ፈፅሞ የማይለይ ሆኗል። በተለይ የኢንተርኔት አቅርቦቱ ይበልጥ በተስፋፋባቸው ሀገራት ሬዲዮ እና ቴሌቭዥንን ኦንላይን መከታተል እንዲሁም ስልክ መደወል ይቻላል። ይህ ኢንተርኔት በርካታ በጎ ጎኖች ይዞ ከመምጣቱ ባሻገር የሚያሲይዘው ሱስ እና መጥፎ ጎኖችም አሉት። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ መምህርን አነጋግሬያለሁ እንዲሁ በፌስ ቡክም አስተያየታቸውን ያካፈሉን አሉ።

ዮናታን ተስፋዬ ከ 9-11ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ያስተምራል። የ26 ዓመቱ ወጣት መምህር ኢንተርኔት መጠቀም ከጀመረ ስምንት ዓመት ሆኖታል። ብዙ ጥቅሞች አግኝቶበታል። መለስ ብሎ የተማሪነት ጊዜውን ሲያስታውስ እሱም፤ ያለ ኢንተርኔት አድጓል። የኢንተርኔት አጠቃቀምን በተመለከተ በፌስቡክ ገፃችን ላይ እንዲሁ አስተያየት እንዲሰጡን የጠየቅናቸው ነበሩ።

መቅዲ ለምሳሌ፤ ጥሩ እና መጥፎ ጎኖች አሉት ፤ በኔ አስተሳሰብ ለተማሪዎች ጉዳቱ ያመዝናል ካለች በኋላ ራሷን እንደምሳሌ በመጥቀስ፤ ከትምህርት ቤት እቤት ከገባሁ በኋላ የማደርገው ነገር ቢኖር ዮ ቲውብ ላይ ቪዲዮ መመልከት ነው። እና ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል ብላለች። ዮናታን በዚህ ሙሉ በሙሉ ባይስማም ለተማሪዎቹ የቤት ስራ ሲሰጥ ኢንተርኔት ላይ መረጃ እንዲያሰባስቡ አጠቃቀሙንም እንዲማሩ በሚፈቅድበት ጊዜ አንዳንድ እድሉን ለመጥፎ የሚጠቀሙ ተማሪዎች አስተውሏል።

Symbolbild Internet Porno

ወላጆች ልጆቻቸው ኢንተርኔት ውስጥ የሚፈልጉትን ካልተከታተሉ፤ አዳጊ ወጣቶች በቀላሉ የወሲብ ገፆችን ሊጎበኙ ይችላሉ

ድጋፌ የተባለ የፌስቡክ ተከታታያችን ደግሞ በበኩሉ፤ኢንተርኔትን በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጥቅም አለው። ነገር ግን በአግባቡ ካልሆነ ገንዘብ እና ጊዜ ላይ ተፅዕኖ አለው ብሏል። ዮናታን የኢንተርኔት አገልግሎት በተሻለ መልኩ በሚገኝበት አዲስ አበባ ከተማ ነው የሚኖረው። አዲስ አበባም ቢሆን በሚፈልገው መልኩ ኢንተርኔት መጠቀም እንዳልቻለ ነው የገለፀልን።

ሳዳም የተባለ የፌስቡክ ተከታታያችን ደግሞ አንዳንድ መጥፎ መጥፎ ገፆች አሉ ከኛ ጋር የማይሄዱ እነኚ ማንነተን የሚያጠፉ ነገሮችን በተቻለን አቅም ልናወግዛቸው ይገባል ብሎ አንዳንድ ይጎዳሉ ያላቸውን አስተያየቶች ከሰነዘረ በኋላ ከጥቅሙ በኩል ስናስበው ድምፃችንን በአለም መድረክ አንድ እምናደርግበትን አጋጣሚ ከፍቶልናል በመጠኑም ቢሆን በአጠቃላይ ትምህርት ቤት ሆኗል ማለት ይቻላል ነው ያለው።

ሙሉውን ዘገባ በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic