የኢንተርኔት ስለላ በኢትዮጵያ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 08.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢንተርኔት ስለላ በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ባሥልጣናት የኢንተርኔት መከታተያ እና መቆጣጠሪያ መሣሪያዎችን ዜጎችን ለመሰሰል አልግባብ ተጠቅመውበታል በሚል ሂውማን ራይትስ ዎች ያወጣው ዘገባን በርካቶች ተቀባብለውታል። የ«ሲትዝን ላብ» ጥናትን በማያያዝ እንደቀረበው የሂውማን ራይትስ ዎች ዘገባ ከሆነ፦ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢንተርኔት የሚያከናውነውን ስለላ አጠናክሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:29

በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ስለላ መጠናከሩን ሲትዝን ላብ አስታወቀ

በዩናይትድ ስቴትስ፤ በዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም በሌሎች ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የመንግሥት ተቃዋሚዎች እጅግ ለተራቀቁ የኢንተርኔት ስለላ መተግበሪያዎች ዒላማ ሆነዋል ይላል፦ «ሲትዝን ላብ» የተሰኘው ተቋም ያወጣው የሰሞኑ ዘገባ።

ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ካናዳ የሚገኘው በዓለም አቀፍ ደህንነት በሰብአዊ መብቶች፤ ብሎም በስነ ቴክኒክ ጥልቅ ምርምር የሚያካሂደው «ሲትዝን ላብ» የጥናት ተቋምእንደዘገባው ከሆነ የኢንተርኔት ስለላው የሚከናወነው ለተሰላዩ በአዶቤ ፍላሽ  እና ፒዲኤፍ ማገናኛዎች ስም በሚሰደዱ የኢሜል መልእክቶች ነው። አዶቤ ፍላሹ ቪዲዮ መመልከቻ፤ ፒዲኤፉ ደግሞ ጽሑፍ ማንበቢያ ተብለው ነው የሚላኩት። የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹ ላይ በኢንተርኔት መጠነ-ሰፊ ስለላ አጠናክሮ፡ቀትሏል መባሉ በርካቶችን አነጋግሯል። 

የኢቲዮጵያ ተቃዋሚዎች ለአዲስ የንግድ የስለላ መተግበሪያ (App)ዒላማ ሆነዋል የሚለው «የሲትዝን» ላብ ጥናታዊ ሰነድ ይፋ የሆነው በዚሁ ሳምንት ነው። ይህ የስለላ መተግበሪያ የተሠራው ሳይበርቢት (Cyberbit) በተባለ የእስራኤል አንድ ኩባንያ ሲሆን፤ ፒሲ መሰለያ ስልት (PSS) የሚል ስያሜ ይዟል።

ይህ የኢንተርኔት የስለላ መተግበሪያ በስውር የተያዘበት ለስለላ የሚላከው ኢሜል መጀመሪያ የሚሰለለው ሰው ኮምፒውተር አለያም የተነቀሳቃሽ ስልክ ላይ ይጫናል። ከዚያ በኋላም ነው ስለላው የሚጀምረው። በመጀመሪያ በኢሜል የሚላከው ሰነድ ተቀባዩ ጥርጣሬ እንዳያጭርበት ሰላዩ አካል ተዓማኒ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል።

የሚላከው ሰነድም፤ የቪዲዮ አለያም የጽሑፍ መልእክት ሊሆን ይችላል። የቪዲዮ ከሆነ ምስሉን ለመመልከት ይህን አዶቤ ፍላሽ ማጫወቻ ይጫኑ የሚል መልእክት ተያይዞ ይላካል። የጽሑፍ ከሆነ ደግሞ ጽሑፉን ለማንበብ አዶቤ ፒዲ ኤፍ ራየተርስ ማንበቢያውን ይጫኑ ይላል መልእክቱ። እነዚህን መልእክቶች ካልከፈቱ ምንም የሚፈጠር ነገር የለም። ችግር የሚፍጠረው በጉጉትም ይሁን ባለማወቅ ሰነዶቹ የተከፈቱ ጊዜ ነው።

ሰነዶቹ በተከፈቱ አፍታም ሳየቆዩ መሰለያ መተግበሪያው ሥራውን ማቀላጠፍ ይጀምራል። ተስላዩ አንዳችም ነገር ሳያውቅ ኮምፒውተርም ይሁን ዘመናዊ ስልክ የተጠቃሚው ካሜራ፤ መቅረፀ ድምፅ፤ ብሎም አጠቃላዩ ሰነድ በሰላዩ ቁጥጥር ስር ይወድቃል። ሰላዩ የትኛውም የዓለማችን ክፍል ሆኖ የትኛውም ቦታ የሚገኝ ኮምፒውተር ወይንም ስልክ እንዳሻው ይበረብራል። አዶቤ ተቋም የአዶቤ ምርቶች ያለአግባብ ለስለላ ተጋባር እንደዋለበት ሲትዝን ላብ በደብዳቤ አስታውቋል። አዶቤ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ ለሲትዝን ላብ በደብዳቤ አሳውቋል።

ይህ የስለላ መተግበሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሰላዮች ጥቅም ላይ መዋሉን በሒውማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ አና የኤርትራ አጥኚ ፌሊክስ ሆርን በትዊተር ገጻቸው አንዲህ ሲሉ ጽፈዋል። «አዲሱ የሲትዝን ላብ ዝርዝር መረጃ ኢትዮጵያ መንግሥት ጃዋር ሞሐመድን እና ዩኤስ፤ ካናዳ፤ ጀርመን፤ ብሪታንያ እና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ዒላማ ለማድረግ የእስራኤል የስለላ መተግበሪያን እንዴት እንደሚጠቀምበት ያብራራል።” ሲሉ አስነብበዋል። ፌሊክስ ክመልእክታቸው ጋር የየሲትዝን ላብ ጥናታዊ መረጃን አያይዘዋል።

የፌሊክስ ሆርንን ትዊተር አያይዞ መልዕክቱን እዛው ትዊር ላይ ያሰፈረው አምደ መረብ ጸሐፊው ዘካሪያስ ዘላለም ደግሞ፤ «ወዳጆች በኢሜል የሚደርሷችሁ ማገናኛዎችን ተጠንቀቁ። ዘርዘር ያለው መረጃ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ተቺዎች ኮምፒውተሮችንና ሌሎች መሣሪያዎችን ለመበከል ጥቅም ላይ ያዋላቸው የስለላ ቴክኖሎጂዎች ዘመናዊነት እጅግ መጨመሩን ነው።» ብሏል።

አያና በሚል የትዊተር ተተቃሚ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል። «ይህ በጣም አስደንጋጭ ነው። የስለላ መተግበሪያው ማንኛውም ጠለፋ የተከናወነበት ግለሰብ ወሳኝ መረጃዎቹ መቅረጸ ድምጽ እና ቪዲዮው፤ የኢንተርኔት አሠሣ ታሪኩ እና  የአንተርኔት መግቢያ ቁልፎቹ፤ የስካይፕ ጥሪ ዝርዝሮቹ እና ስልኩ ላይ የሚገኙት ስሞች ወዘተረፈን ለሰላዩ ይሰጣል።»

የሲትዝን ላብ ሠነድ  አንደሚጠቁመው ከሆነ ሠላኢኡ አካል በተሰላዩ ዘመናዊ ስልክ (ኮምፒውተር)አማካኝነት ተሰላዩ የት ቦታ እንደሚገኝ፤ ምን አይነት መለዕክቶችን እንደተለዋወጠም ማወቅ ይችላል። ከዚያም ባሻገር ምን አይነቶች ሠነዶችን እንዳተመ፤ ብሎም ምን አየጻፈ (እየተየበ)   እንደሆነ ማወቅ ያስችለዋል ብሏል። ያ ግን የተላከው የስለላ አታላይ ኢሜል በተሰላዩ ከተከፈተ ብቻ ነው። ዋናው ነገር አጠራጣሪ መልዕከቶችን አለመክፈት ነው ተብሏል።

Computer Überwachung

ወሰንሰግድ ዘሪሁን በበኩላቸው በፌስ ቡክ ባስነበቡት ጽሑፉ «በኢንተርኔት አፈናና ስለላ የሕዝብን ትግል ማስቆም አይቻልም!» ብለዋል። ዐምደ ጽዮን ዘአክቲሳኒስ ደግሞ እዛው ፌስ ቡክ ላይ «የወያኔ የኢንተርኔት ስለላ (ካርታ )» ያሉትን እያይዘዋል። «ሲትዝን ላብ» በጥናታዊ ሠነዱ ላይ ያሰፈረው ካርታ የኢትዮጵያ መንግስት ከኢትዮጵያ በሚቆጣጠረው የስለላ ቋት በኩል በመላው ዓለም የሚገኙ አህጉሮች ላይ የተቆላለፈ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ያመላክታል።

«የህወሃት ብሄራዊ መረጃ ስለላ ሶፍት ዌር ሰናከል» ሲሉ የጻፉት ደግሞ ክንዱ ዳኜ ናቸው። ክንዱ በጽሑፋቸው «የህወሃት ብሔራዊ መረጃ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎችን ለመሰለል ከእስራኤል ኩባንያ የተገኘ ማልዌር ( Malware ) የተሰኘ የስለላ ዘዴ ቢጠቀምም የስለላላ መረቡ ኢላማ በተደረጉ ተሰላዬች ቁጥጥር ስር ወድቋል.. .ኤስ.ኤስ.(PSS) ፒሲ ሰርቪሊያንስ ሲስተም ( PC Surveillance System ) ተብሎ የሚጠራ የዊንዶ ፕሮግራም የተጠቀመዉ የህወሃት ብሄራዊ መረጃ ያሳበዉን ሳያሳካ አለማቀፋዊ ስህተት ዉስጥ እራሱን ከቷል።» ሲሉ አስነብበዋል። በነገራችን ላይ የሲትዝን ላብ ከፍተኛ ተመራማሪ አና ስለ ስለላው ጽሑፍ ያቀረቡት ቢል ማርቻክ በኢቲዮጵያ መንግስት መሰለላቸውን እንደደረሱበት ገልጠዋል።

መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጪ በተቃዋሚዎቹ ላይ በዘመናዩ ቴክኖሎጂ መጠነ ሰፊ የኮምፒውተር ጠለፋና የስለላ ዘመቻ ያካሂዳል የሚለውን ዜና ከተመለከቱ በኋላ ለድርጊቱ ድጋፋቸውን የሰጡም አልታጡም።

ረድዔት ዓለሙ በአጭሩ «ደግ አረገችለህዝባቸውና ለሃገራቸው ደንነት ሁሉም ሀገሮች ያደረጋሉ።» የሚል አስተያየት አኑራለች። ዘመን በተስፋ «በጣም ደስ ይላል» ሲሉ፤ «ደግ አረገ። እየሰለለ ደህንነታችን የማይጠብቅ ከሆነማ ምን መንግሥት ተባለ ያሉት ሙሉጌታ መለሰ ናቸው። ተሰማቸው ሞገስ ደግሞ «ለእኛ አዲስችን አይደለም። እንደጥሩ ነገር እየተላመድነው ነው መፍትሄ ነው ያጣን።» ብለዋል። «ሰዎች ጠንቀቅ! የኢትዮጵያ የመሰለያ መተግበሪያው ነገር ቀልድ ይየደለም» ሲል ማስጠንቀቂያ የሰጡት አንዋር አዱሼ ናቸውው በትዊተር መልዕክት።

ሌሎች በሳምንቱ ውስጥ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተነሱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የወልዲያ እና የመቀሌ እግር ኳስ ቡድኖች ወልዲያ ከተማ ውስጥ ሊያካሂዱ የነበረው ግጥሚያ ከተማዋ ላይ በደጋፊዎች መካከለ በተቀሰቀሰ ገጭት ሳይካሄድ መቅረቱ ነው።

በግጭቱ በሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ገብረ ሥላሴ ጌታሁን የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ «የተፈጠዉ ችግር ምንም ጥቅም የለዉም ለሁሉም አይጠቅምም ቶሎ ይታረም ጥፋቱ የመንግስት ነዉ አገርን ወክሎ የመጣ ተጫዋች የሄደበትን አገር ማክበር አለበት» ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። ግርማይ በርሄ «የትም ይሁን ለስው ልጅ ክብር ይኑረን» ሲል  ናንዬ ዋርካ ደግሞ «ብሄር ተኮር ላለመሆን ምን ዕድል አለዉ ?።  25ዓመታት የነበረዉ ወያኔ  ፖለቲካ ውጤት ነዉ።» ብለዋል። ዘላለም ሹመቴ «በጣም ያሳዝናል። ኧረ ኢትዮጵያ ወዴት እያመራች ነው ሲሉ በጥያቄ አጠቃለዋል።

ጀርመናዊ ቱሪስት እና አብሮት የነበረው ሀገር አስጎብኚው አፋር ውስጥ መገደላቸውም ሌላኛው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተነሳ ጉዳይ ነበር። ይኽኛው ጉዳይ ግን ጥቃት አድራሹ ይሄ ነው ያ ነው የሚል መጠቋቆም የተስተዋለበት ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic