የኢትዮ ኮለኝ የስፖርትና የባህል ማኅበር ዓመታዊ በዓል | ባህል | DW | 15.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የኢትዮ ኮለኝ የስፖርትና የባህል ማኅበር ዓመታዊ በዓል

ከተመሰረተ ከ10 ዓመት በላይ የሆነዉ የ«ኢትዮ ኮለኝ የስፖርትና የባህል ማሕበር» ዓመታዊዉን ባህላዊ መድረክ ሲያዘጋጅ ይህ ለሁለተኛ ግዜ መሆኑ ነዉ። በኖርዝ ራይን ዊስት ፋልያ እንዲሁም አቅራቢያ ግዛቶች ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የተሰባሰቡበትን ባህላዊ መድረክ ቃኝተን በዕለቱ ዝግጅታችን ይዘን ቀርበናል።
በርካታ ኢትዮጵያዉያን የተገኙበት የኢትዮ ኮለኝ የስፖርትና የባህል ማሕበር ዓመታዊ በዓል ፤ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዉና ከመገናኛ መድረክ ባለፈ፤ የኢትዮጵያን ባህላዊ ወጎች፤ ምግብ፤ አልባሳት፤ የሚተዋዉቅበት መድረክ ሲያዘጋጅ ይህ ለሁለተኛ ግዜ መሆኑ ነዉ። ባህላዊ ሙዚቃና ዉጥዋዜ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳት ትርኢት፤ ታሪክ ነክ ትያትሮችና፤ ዘመናዊ የጃዝ ሙዚቃ ቅንብር ፤ ሥነ-ግጥምና መነባንብ፤ አስደናቂ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማለትም «ሰርከስ»

የሥነ-ጥበብ ዓዉደ ርዕይ፤ ባህላዊ መድረኩን እጅግ ዉበት የሰጡት ዝግጅቶች ነበሩ። በሌላ በኩል እጅ የሚያስቆረጥመዉ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግብና መጠጥ ባህላዊዉ ጠጅም ጭምር ቀርቦ ነበር። በመድረክ የቀረበዉ ባህላዊ ክንዉን እንዲሁም ባህላዊዉ ምግብና ጠጁ በወቅቱ ጀርመን ዉስጥ ያለዉን ብርድ ከበር ዉጭ አባሮ እድምተኛዉን ሙቀት፤ ደስታ፤ ፍቅር አጎናፅፎት አምሽቶአል። የማኅበሩም ዓላማ በአካባቢዉ ላይ በተለያዩ ሥራዎች ተጠምዶ ተለያይቶ የሚገኘዉን የኢትዮጵያዉያ ማኅበረሰብ ማሰባሰብ ፤ማቀራረብና፤ በስፖርትና በባህላዊ ክንዉኖች ማሳተፍ እዚህ የተወለዱትንም ኢትዮጵያዊያን ቋንቋ ባህልና ታሪክን ማስተማር መሆኑን የማኅበሩ መስራች አቶ ተስፋዬ አበበ ገልፀዉልናል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያዉያን የሥዕል ዓዉደ ርዕይ፤ ትያትር፤ ግጥም፤ መነባንብ፤ የአልባሳት ትርኢት በኢትዮያዉያኑ ቀርብዋል። የኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች ሙዚቃና ዉዝዋዜም ታይቶአል። መድረኩ ይህን ለማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ችሎታ ያለቸዉን ሰዎችንም ለማገናኘት ለማኅበረሰቡ ለማስተዋወቅም እንደሆነ ነዉ አቶ ተስፋዬ የተናገሩት።
እንደ አቶ ተስፋዬ የኢትዮ ኮለኝ የስፖርትና የባህል ማኅበር በቀጣይ ጀርመን ለተወለዱ ኢትዮጵያዉያን አማርኛ ለማስተማር ዝግጅቱን አጠናቆአል።


በጀርመን ሀገር አጎቱ ጋር መጥቶ የሚኖረዉ ወጣት አቤል ወደ ጀርመን የመጣዉ የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ ነዉ። በአማርኛ መናገር ቢከብደዉም ግን አይታማም ስምህ ማነዉ ስል መቅረፀ ድምፄን ይዤ ቀረብ ብዬዉ ነበር። ስሙን ቢናገርም በጀርመንኛ ማዉራትን መርጦ በጀርመንኛ ስለ ማኅበሩ እድናቆቱን እንዲህ ሲል ገልፆአል።


«ይህ ማኅበር እዚህ ለተወለዱ ኢትዮጵያዉያን አልያም ኢትዮጵያን በደንብ ለማያዉቁ ቋንቋዋን ለማይናገሩ እጅግ ጥሩ ነዉ። ብዙ ግዜ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰማዉ ችግር ብቻ ነዉ። እኔ ወደጀርመን ከመጣሁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ አልሄድኩም አልተመቸኝም፤ እናት አባቴም ሞተዉብኛል። እዚህ ጀርመን የእግር ኳስ ተጫዋች ነኝ ። ይህ ምሽት ይህ የመገናኛ መድረግ እጅግ አስደስቶኛል። ግን ምንg ግዜም ቢሆን የትዉልድ ሃገር ጥሩ እንደሆን አዉቃለሁ።»
ዘጠኝ ቁጥር ማልያን ለብሶ ለማኅበሩ የእግር ኳስ የሚጫወተዉ የማኅበሩ ምክትል ተጠሪ ወጣት ዮናስ በየነ በጀርመን ሲኖር 17 ኛ ዓመቱን እንደያዘ አጫዉቶናል። ማኅበራችን ኢትዮጵያዉያን አሰባስቦ ማኅበረሰቡ ያለዉን ሞያ እዉቀት ተለዋዉጦ ችግርም ያለበት ተረድቶ በማኅበሩ ታቅፎ እንዲኖር ፍላጎታችን ነዉ ሲል ገልፆአል። ማኅበሩ ባህላዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችንም ያደርጋል።


በጀርመን ኮለኝ በተዘጋጀዉ መድረክ ላይ ትያትር ነክ መነባንብን ቀርቦ ነበር።
"አዬ፣ ምነው እመብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት? ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከ መቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት? ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀንዋን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት? አላንቺ እኮ ማንም የላት?"


"ጴጥሮስ ያችን ሰዓት" የተሰኘዉን ይህን የጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ግጥምን በመነባንብ መልክ በመድረኩ ይዞ ቀርቦ እድምተኛዉን ያስደመመዉ ወጣት እንድርያስ ተድላ በንድፍ ሞያ በጀርመን ሁለተኛ ዲግሪዉን አግኝቶ በአንድ የጀርመን ድርጅት ዉስጥ በማገልገል ላይ ይገኛል። ማሕበሩን ለማጠናከር ኢትዮጵያዉያን በሚችሉት ሁሉ መሳተፍ እንደሚችሉ ገልፀዋል።


የኢትዮ ኮለኝ የስፖርትና ባህል ማኅበርን በተቻላት ሁሉ በማገዟ የምትታወቀዉ ወጣት ማሕሌት ጌታቸዉ በበኩልዋ፤ እዚህ ሃገር ለሚወለዱት ልጆች አስበን ባህልና ቋንቋን ለማስተማር ወደ ማኅበሩ መምጣት አለብን ስትል ጥሪዋን አስተላልፋለች። በድረ- ገፅም ማኅበሩን ማግኘት እንደሚቻል ሳትገልፅ አላለፈችም።


ለጉብኝት ልጃቸዉ ጋር ወደ ጀርመን የመጡት አቶ አሰፋ በየነ የዚሁ ምሽት ባህላዊ መድረክ ተካፋይ ነበሩ። አቶ አሰፋ ድግሱን የኢትዮጵያዉያኑን መተሳሰብ አይተዉ መደነቃቸዉንና እንዲህ እንዳልጠበቁም ተናግረዋል። እንደ አባትም ፈጣሪ በሰላም በአንድነት ያቆያችሁ ሲሉ መርቀዋል።


ወጣት ኢትዮጵያዉያኑ በመደጋገፍ በመግባባት አካባቢዉ ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያዉያንን ለማሰባሰብ ሃሳብና እዉቀት ለመለዋወጥ የጀመሩት ብሩህ መድረክ ሊበረታታ የሚገባዉ ይመስለናል። ቃለ ምልልስ የሰጡንን እንዲሁም የማኅበሩን አባላትና የበዓሉን ታዳሚዎች ላደረጉልን ትብብር በዶይቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።አዜብ ታደሰ

ተክሌ የኋላ


Audios and videos on the topic