የኢትዮ-ኤርትራ አዲስ ዉዝግብ | ኢትዮጵያ | DW | 01.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮ-ኤርትራ አዲስ ዉዝግብ

አዋሳኝ ድንበራቸዉም የጦር ሐይል ፍጥጫ፤ ጠብ እና ቁርቁስ ተለይቶት አያዉቅም።አሁን በሰዎች መታገት በተለይ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሐብት እና የሰዉ ሐይል ዋና ዋና ማዕከል ኦሮሚያን በሚንጠዉ ተቃዉሞና አመፅ ሰበብ እንዳዲስ መቀጣጠሉ «የከፋ ይከተላል» የሚል ሥጋት ማጫሩ አልቀረም-እንደ ሮንግ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:15
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:15 ደቂቃ

የኢትዮጵያ እና ኤርትራ

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ በኦሮሚያ መስተዳድር በተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞና ግጭት ምክንያት እንደ አዲስ እየተወጋገዙ ነዉ።የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያዉያንን እያገተ ወስዷል፤ በኦሮሚያ መስተዳድር የተቀሠቀሰዉን ተቃዉሞ ያባብሳል በማለት ድርጊቱን አዉግዘዋል።የኤርትራ መንግሥት ባንፃሩ የኢትዮጵያ መንግሥት የዉስጥ ችግሩን በኤርትራ ላይ ለመለጠፍ ይሞክራል በማለት ዉግዘቱን መልሶ አዉግዟል።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ሁለቱ መንግሥታት አዲስ የገጠሙት ዉዝግብ ወደ ወታደራዊ ግጭት ሊያመራ ይችላል።

ወትሮም ያልሰከነዉ የኢትዮ-ኤርትራ የቃላት «ቴኒስ ግጥሚያ» ሰሞኑን ብሶ ቀጥሏል።የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ ጠላቱን ሠማንያ ኢትዮጵያዉያንን ከትግራይ አግቶ ወስዷል በማለት ሲያወግዝ አዲሱ ዉዝግብ ተጀመረ።የኦሮሚያ መስተዳድርን የሚያብጠዉ ተቃዉሞ፤ አመፅና ግጭት ደግሞ የአዲስ አበባና የአስመራን ዉዝግብ ለማጋጋም ተጨማሪ «ቤንዚን» ነዉ-የሆነዉ።

የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር አቶ ጌታቸዉ ረዳ ሰሞኑን እንዳሉት አመፅና ግጭቱን የሚያቀጣጥለዉ የኤርትራ መንግስት ነዉ።አቶ ረዳ ለጋዜጠኞች እንደነገሩት ኢትዮጵያ በአሸባሪነት የፈረጀቻቸዉን የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦነግ)ን እና ግንቦት ሰባትን የሚደግፈዉ የኤርትራ መንግሥት የኦሮሚያዉን አመፅ እና ግጭት ለማቀጣጠሉ መንግሥታቸዉ «ተጨባጭ» ያሉት መረጃ አለዉ።

Grenzkonflikt Eritrea Äthiopien Soldaten Eritrea

የኤርትራ መንግሥት ባንፃሩ ባወጣዉ መግለጫ ዉሸት ቢደጋገም እዉነት አይሆንም ይላል።«በኦሮሚያ የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞም»፤የኤርትራ መግለጫ እንደሚለዉ፤ «የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የሚከተለዉ የከፋፍለሕ ግዛ መርሕ ዉጤት ነዉ።» ሥለ ሁለቱ መንግሥታት ጠብና ጦርነት መፅሐፍት ያሳተሙት ጋዜጠኛ ሚኬላ ሮንግ እንደሚሉት እሰጥ አገባዉ አሳሳቢ ነዉ።

«የሁለቱ ሐገራት ግንኙነት ዉጥረት የተሞላበት ነዉ።ያነጋገርኳቸዉ ሥለ አካባቢዉ የሚያዉቁ ዲፕሎማቶች እሰጥ አገባዉ እንዳሳሰባቸዉ ይገልፁልኛል።አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ አማፂያንን ኤርትራን ትደግፋለች በማለት መዉቀሷ እና ኤርትራ ወቀሳዉን የአዲስ አበባ መንግስት ፕሮፓግንዳ ነዉ እያለች መልሳ ማዉገዟ አሳሳቢ ነዉ።»

ይሁንና ሮንግ እንደሚሉት መወጋገዝ፤ መወቃቀሱ፤ አንዱ የሌላዉን ጠላት መደግፍ ማደራጀቱም አዲስ አይደለም።እና አያስደንቅም።«እንደሚመስለኝ ሑለቱም፤ ላለፉት አስራ-አምስት ዓመታት አንዳቸዉ በሌላቸዉ ሐገር የሚንቀሳቀሱ አማፂ ቡድናትንና ንቅናቄዎችን በደስታ እንደሚደግፉ፤የጦር ሠፈርና ፅሕፈት ቤት እንደሚሰጡ፤ ገንዘብም መደጎማቸዉ ምንም የማያጠያይቅ አዉነት ነዉ።ይሕን የሚያደርጉት ከንድበር ማዶ-ለማዶ ያለዉን ሥርዓት ለማዳከም መሆኑም ግልፅ ነዉ።ሥለዚሕ አዲሱ መወጋገዝ አያስደንቀኝም።»

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከቆመ አስራ-ስድተኛ ዓመቱ-ዘንድሮ።ጦርነቱ ቢቆምም ሁለቱ መንግሥታት ከቃላት ዉጊያ የታቀቡበት ጊዜ የለም።አዋሳኝ ድንበራቸዉም የጦር ሐይል ፍጥጫ፤ ጠብ እና ቁርቁስ ተለይቶት አያዉቅም።አሁን በሰዎች መታገት በተለይ የኢትዮጵያን የምጣኔ ሐብት እና የሰዉ ሐይል ዋና ዋና ማዕከል ኦሮሚያን በሚንጠዉ ተቃዉሞና አመፅ ሰበብ እንዳዲስ መቀጣጠሉ «የከፋ ይከተላል» የሚል ሥጋት ማጫሩ አልቀረም-እንደ ሮንግ።

Grenzkonflikt Eritrea Äthiopien Soldaten Eritrea

«እንደሚመስለኝ ዛቻዉ መናሩ በዲፕሎማቲዉ ዘንድ ማንም ሊያየዉ ከማይፈልገዉ ደረጃ ያደርሳል የሚል ሥጋት አሳድሯል።ምናልባትም ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ወታደራዊ እርምጃ በመዉሰድ ወደፊት የምትፈልገዉን በራሷ ጊዜ ልትፈፅም ትችል ይሆናል።»

በሁለቱ ሐገራት ጦርነት፤ ድርድር ይሁን የፍርድ ቤት ሙግት ተሳትፎዉና ተፅዕኖዉ ያልተለዉ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በተለይ የምዕራቡ ዓለም አቋም ዛሬም አንዳዲስ በጦዘዉ ዉዝግብ መሐል ማነጋገሩ አልቀረም።ሮንግ እንደሚሉት በተለይ እስካሁን ለዘለቀዉ ጠብ እንደምክንያት የሚታየዉ የባድመ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ምዕራቡ ዓለም ማድረግ ያለበትን አላደረገም።የሁለቱን ሐገራት ድንበር እንዲያካልል የተሰየመዉ ዓለም አቀፍ የድንበር ኮሚሽን ያሳለፈዉን ዉሳኔ ኢትዮጵያ እድታከብር ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ግፊት አላደረገም ተብሎ እየተወቀሰም ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic