የኢትዮ-ኤርትራን ችግር መፍታት ያልተቻለው በመሪዎች ግትርነት ነው- ኃይለማርያም ደሳለኝ | ኢትዮጵያ | DW | 28.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮ-ኤርትራን ችግር መፍታት ያልተቻለው በመሪዎች ግትርነት ነው- ኃይለማርያም ደሳለኝ

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላትን ችግር መፍታት ያልቻለችው በመሪዎች ግትርነት ነው አሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን መሪዎችንም እንደ እርሳቸው ስልጣናቸውን እንዲለቀቁ ጠይቀው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሩዋንዳ ኪጋሊ በመካሄድ ላይ ባለው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን ስብሰባ ላይ ስልጣን የለቀቁበትን ምክንያት ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አቶ ኃይለማርያም ስልጣቸውን በገዛ ፍቃዳቸው ከለቀቁ ወዲህ ለህዝብ ይፋዊ በሆነ መድረክ ተገኝተው ሰፊ ማብራሪያ ሲሰጡ የዛሬው የመጀመሪያቸው ነው።  

አቶ ኃይለማርያም በእንግድነት በተጋበዙበት የኪጋሊው ስብሰባ ከሱዳናዊው ቱጃር እና ከፋውንዴሽኑ መስራች ሞ ኢብራሂም ጋር 45 ደቂቃ የፈጀ የጥያቄ እና መልስ ቆይታ አድርገዋል፡፡ ሞ ኢብራሂም ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስለ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ስላላቸው ውዝግብ እንደዚሁም ስለ ደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ጥያቄዎች አንስተውባቸዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በመካከላቸው ሰላም ለምን ማስፈን አቃታቸው? ተብለው ለተጠየቁት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አንድ ቢሆኑም በመሪዎቹ መካከል “የአመለካከት ልዩነት አለ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“የግለሰብ ተክለ ስብዕና አምልኮ ግንባታ እና መራር ቅራኔ ካለ ህዝቡ ለምን ዓይነት ትልቅ ስቃይ እንደተጋለጠ ለማየት ሰዎች አይችሉም፡፡ በብቸኛነት የሚያተኩሩት የራሳቸው ግትር ጸባይ ላይ ነው፡፡  ያ ነው ዋናው ችግር፡፡ በተረፈ ህዝቡ ሁለቱ ሀገራት በአፋጣኝ ሰላም እንዲያመጡ እና አንድ እንዲሆኑ ይፈልጋል፡፡ እኛ የምንለው ችግሩ ትንሽ ነው ነው፡፡ ችግሩ ያለው የአመራሩ የኃይለኛነት ጸባይ ጋር ነው” ብለዋል ኃይለማርያም በምላሻቸው፡፡         

አቶ ኃይለማርያም እርሳቸው ወደ ስልጣን እንደመጡ የድንበር ችግሩን ለመፍታት አስመራ ድረስ ተጉዘው ለመነጋገር ፍቃደኝነታቸውን ቢያሳዩም ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለኤርትራ መሪዎች ውይይቱ በሸምጋይ ወይም ሶስተኛ ወገን ባለበት አሊያም በሁለቱ ሀገራት መካከል ብቻ እንዲካሄድ አማራጭ ቀርቦላቸው እንደነበር አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡ በመሪዎች ደረጃ ቀጥታ ውይይት ከመጀመሩ በፊት ባለሙያዎች ተገናኝተው እንዲመክሩም በኢትዮጵያ በኩል አማራጭ ተሰጥቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የኤርትራ ባለስልጣናት ለጥያቄዎቻቸው “ጆሮ ዳባ ልበስ” ማለታቸውን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ይፋ አድርገዋል፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን እንደተረከቡ ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸውን እና ምላሽ ያገኛሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ለስብሰባው ታዳሚዎች ገልጸዋል፡፡  ስልጣናቸውን የለቀቁበትን ምክንያት የተጠየቁት አቶ ኃይለማርያም “በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ተግባራዊ እንዲሆን ራሴን ማግለል ስለለነበረብኝ ነው” ብለዋል፡፡

“በአፍሪካ ፖለቲካ ያለው ዋናው ችግር ሰዎች ስልጣን ላይ ሙጭጭ ማለታቸው ነው፡፡ እኔ ማሳየት የፈለግሁት ስልጣን መልቀቅ እንደሚቻል እና እንደ ሀገሪቱ ዜጋ ግን ስልጣንን መጠቀም እንደምችል ነው፡፡ ስለዚህ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ማለት አያስፈልገኝም፡፡ እኔ ባለሙያ ነኝ፣ መስራት እችላለሁ፡፡ ለህዝቤም በተለያየ ዘርፍ ማገልገል እችላለሁ” ሲሉ ምላሻቸውን መልስ ሰተዋል። ታዳሚውም ምላሻቸውን በጭብጨባ አድንቋል። 

አቶ ኃይለማርያም ስልጣን እንደለቀቁ ወዲያውኑ የደቡብ ሱዳን አቻቸው ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ተመሳሳዩን እንዲያደርጉ ነግረዋቸው እንደነበር በስብሰባው ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡ ለሳልቫ ኪር “በደቡብ ሱዳን ያለውን ችግር መፍታት ስላቃተዎት ስልጣንዎትን ይልቀቁ ብዬ ነግሬያቸዋለሁ” ሲሉ አክለዋል፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ