የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ግጭትና፣ የዘንድሮው ምርጫ  | ኢትዮጵያ | DW | 01.01.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ግጭትና፣ የዘንድሮው ምርጫ 

የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎችን ትኩረት በሳቡ 2 ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ግጭት እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ያተኮሩ አስተያየቶችን ያስቃኘናል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በሰጠው መግለጫ ካለፈው አንድ ወር ወዲህ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን መሬትም መያዙን አስታውቋል።የሱዳን ባለሥልጣናትም በኃይል የተያዘውን መሬት አንለቅም  እስከ ማለት መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዚሁ መግለጫ ተናግረዋል።ኢትዮጵያም እንደ ከዚህ ቀደሙ ችግሩን በዲፕሎማሲና በሰላማዊ ድርድር ለመፍታት እንደምትጥር አስታውቀዋል። በአምባሳደር ዲና መግለጫ መሠረት በአሁኑ የሱዳን፣ ድንበር ጥሶ መሬት የመያዝ ርምጃ የሌሎች በስም ያልጠቀሷቸው ኃይሎችም እጅ አለበት።በዚህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል 
«ስንታየሁ አንለይ ኢትዮጵያ» በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረ አጭር  አስተያየት «ጉዳት ሳይደርስ መከላከል ነው እንጅ ጉዳት እየደረሰ እያዩ መግለጫ መስጠት አይጠቅምም።»ይላል። ሳሙኤል ቶማስም ፣ኢትዮጵያ ብዙ ጉዳት ሳይደርስባት በፊት ራስዋን እንድትከላከል ሲሉ በፌስቡክ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል።«ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ገብታ በርካታ ህግ ወጥ ተግባሮችን እየፈጸመች ከሆነ ተመጣጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ምን እስክታደርግ ነው የሚጠበቀው? እንኳን በርካታ ህግ ወጥ ተግባር መፈጸም አይደለም ፣ድንበሩን ለማለፍ ሲሞክሩ እርምጃ ካልተወሰደ ፣ ብዙ ጉዳት ካደረሰች በኃላ እርምጃ ለመውሰድ መሞከር ተገቢ አይመስለኝም። አስቀድሞ ነው እንጂ እራስን መከላከል! »በማለትም አሳስበዋል።ተስፋው አባይ ደግሞ «በሱዳን ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አቅጣጫ መንግስት ለሚደርስበት ጥቃት አፀፋዊ እርምጃ በመውሰድ ሉአላዊነቱን ማስጠበቁ ተገቢ ቢሆንም ቀድሞ የተጠናከረ የደህንነት ስራን በመስራት ጥቃት እንዳይደርስ ትኩረት ቢያደረግ መልካም ነው።»በማለት መክረዋል። ትዝታ ደጀን በሚል ስም በፌስቡክ የቀረበ አስተያየት ደግሞ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ያከታተለ ነው።ግድቡን እስኪነኩት ነው እየተጠበቀ ያለው?መቼ ይሆን የሰው ሕይወት የሚጨንቃችሁ? ዛሬ ነው ሱዳን መግደልዋንና ድንበር ጥሰው ገብተው መዝረፋቸውን ያወቃችሁት? ቆይ 2013ን የመቀነስ ዓመት ብላችሁ ሰይማችሁታል መሰል ? ይላል።«ሱዳን ወቅት ጠብቃ የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ ከፍ ያለ ጉዳት አድርሳለች ተብሏል። ሃገራችን ከወያኔ ጋር በነበረው ኦፕሬሽን ትንሽ ጉልበት ጨርሳለች።ታዲያ አሁን በቂ ኃይልና ትጥቅ ያዘጋጀ ክልል አለ?የመንግሥት ዲፕሎማሲ ጥረቱ ከከሸፈ ሲሉ በትዊተር የጠየቁት መሐመድ ሙክታር ናቸው 

አምባሳደር ዲና በዚህ ሳምንት መጀመሪያው መግለጫቸው ሱዳን በኃይል የያዘችው 100 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ያልተካለለው የሁለቱ ሃገራት ድንበር አካባቢ የሚገኘውን መሬት መሆኑን ተናግረዋል። መሬቱ የተያዘውም የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሱዳን ባለሥልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ ተነግገረው በተመለሱ ማግስት ነው። 
እንደ አምባሳደር ዲና በአሁኑ የሱዳን፣ ድንበር ጥሶ መሬት የመያዝ ርምጃ የሌሎች በስም ያልጠቀሷቸው ኃይሎችም እጅ አለበት ።
«ጊዜና አጋጣሚ ጠብቆ የሚቀያየር መጥፎ ጎረቤት ነው።ለሱዳን ወታደር የአማራ ሚሊሻና ልዩ ኅይል በቂ ነው። ነገር ግን ሱዳንን ከጀርባ ለዚህ እኩይ ተግባር የምትገፉፉት ግብጽ ናት የግብጽ መድኃኒት ደግሞ ቱርክ ናት የኢትዮጵያ መንግስት ቱርክ ጋር አንድ ቀን ውይይት አደረገ ቢባል ግብጽ የጥፋት እጇን ትሰበስባለች። ሲሉ የበኩላቸውን መፍትሄ በፌስቡክ የሰነዘሩት አብዱራህማን መሐመድ «የሱዳን መመናቀር ዋጋ ያስከፍላታል እንጅ የትም አያደርሳትም ከዛይድ ባሬ ከሶማሌ መማር አለባት ያኔ የአጼው ስራአት ሲገረሰስ ሀገራችን ባልተረጋጋችበት ጌዜ ሶማሌ አጋጣሚውን ጠብቃ በፈረጠመ ኃይሏ ወረራ አድርጋብን ነበር ነገር ግን እንዴት ተቀጥቅጣ እንደወጣችና ዛሬም ድረስ ራሷን ያልቻለች ሽባ ሆና ቀርታለች ሱዳን ደግማ ብታስብበት

ይሻላታል!» ሲሉ አስጠንቅቀዋል። 
ተከታዩ የላላ በቀለ ለገሠ መልዕክት ደግሞ ለሱዳናውያን ነው።«ድንበራችን ለመጠበቅ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ እንደምንችል ጥርጥር የለኝም በማለት  የሚጀመረው መልዕክቱ «ሱዳናውያን ወንድሞቼና እህቶቹ ሲል ይቀጥላል «ሱዳናውያን ወንድሞቼና እህቶቹ እኛ የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች ማንኛውም ሃገር የሌለው የረዥም ጊዜ ታሪክና የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ነን።ጉዳያችሁ ድንበር ማስጠበቅ ከሆነ ከመሪዎቻችን ጋር በትህትና ተወያዩ።ከዚያ ውጭ የሚሆን ከሆነ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ድንበራችንን የማስጠበቅ ፍርሃት የለብንም።ምክንያቱም እኛ ለዚህ የተፈጠርን ነን።ኢትዮጵያን እንድትወጉ ከውጭ ለሚጎተጉቷችሁ ትኩረት አትስጡ፤ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ለማስቆም ምንም አያደርጉላችሁም።ሲሉ ምክራቸውን ደምደዋል። አሻግሬ በትዊተር«ሱዳን ለክፉ ቀን የማትሆን በልቶ ካጅ መሆኗን አሳይታለች።ሀገር የተዳከመች መስሏት ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባልና።የውጭ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ለውስጥ መረጋጋት ያላሰለሰ ርምጃ መውሰድ ይገባል።በማለት የበኩላቸውን መፍትሄ ጠቁመዋል።

«የጠላትነት ስሜትና ዓላማ ያለው ጊዜን ጠብቆ እንዲህ ይከዳል። ለሀገራችን ሕልውና ከልብ የሚቆረቆሩ ሁሉ ይህን ዕውነት መዘንጋት የለባቸውም። በዚህ ጊዜ የሚጠበቀው ጀግንነት ከውስጥም ከውጭም ጥቃት እንዳይደርስ በንቃት መቆምና በፅናት መታገል ነው። የግንባርና የደጀን ኃይላችንን የሚያቀናጅ ቁርጠኛ አመራር በየደረጃው መፈጠሩ መረጋገጥ አለበት። ሁልጊዜ በዘመቻ ሳይሆን በዕቅድና በስልት አመራር መስጠት ይገባል። ሕዝባችንም ሐቁን በውል ተገንዝቦ ለታሪክ ሠሪነቱ መዘጋጀት ይኖርበታል። በባዶ ማቅራራት ለብርቱ ጥቃት ያጋልጠናል።» የሚለው የካሳዬ ገቢሳ አስተያየት ነው።በላይ አያሌው ደግሞ «አይ ሱዳን! ....ገልቦ ክንብንብ ሆነ።» ካሉ በኋላ በራሳችን ወታደሮች ስትጠበቅ 17ዓመት ሙሉ እየኖረች እኛን መውረሯ ይገርማል። ሲሉ ትዝብታቸውን አካፍለዋል።    
«በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል» የሚለውን አባባል ያስቀደሙት ኑር አዲስ ማርዮ ደግሞ«የኛን ሰላም ነሰተው እነሱ ሰላም ሊሆኑ?ሲሉ ይጠይቁና «አላወቁም የጀርባ አጥንታቸው ኢትዮጲያ ነበረች። ቢያውቁማ ኖሮ የክፉ ቀናቸውን ኢትዮጲያን በክፉ ባላሰቧት ነበር። አላህም የስራቸውን ይሰጣቸዋል። ከግብፅ ይልቅ ኢትዮጲያ ባለውለታዋ ነበረች ለሱዳን።ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታቱ ይሻላል።ሱዳን ለግብጽ ሥራ አስፈጻሚ መሆኑ አይጠቅማትም።ኢትዮጵያ ፈርታ አይደለም።በትዕግስት የምትጠብቃችሁ ነገሩ እንዳያቃቅር ነው።ሰላም ፍቅር ይስጠን።ብለዋል። ገነት የድንግል ማርያም ልጅ በሚል ስም በፌስቡክ በጻፉት አስተያየት ።
የኢትዮጵያን ውድቀት የሚመኙ ቀድመው ይጠፋሉ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ በማለት የሚጀመርው ደግሞ  ቅዱስ ያሬድ በሚል የፌስቡክ ስም የተጻፈ አስተያየት ነው« አይ ሱዳን መካሪ አጣሽሳ የግብፅ ምክር ገደል እንዳይሰድሽ ተጠንቀቂ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ፈላጊ ነው ዝም ማለት ፍራቻ ከመሰለሽ ተሳስተሻል የኢትዮጵያን ድንበር አልፈሽ የሰው ርስት መውሰድ አሰበሽ ከሆነ ተሸወድሽ ፣ሞኝ ነሽ ሰላም ይሻልሻል።ይላል አስተያየቱ 

ቀጣዩ የኢትዮጵያ ምርጫ በዚህ ዓመት ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓመት ምህረት እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሃሳብ ካቀረበበት ጊዜ አንስቶ ስለ ምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ኅብረተሰቡ የተለያዩ አስተያየቶች በመስጠት ላይ ናቸው። የምርጫ መስፈርት አላሟላችሁም የተባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ታዛቢዎች ነቀፋቸውን እያሰሙ ነው።ምርጫው መካሄዱን የሚደግፉ እንዳሉ ሁሉ ሃገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለምን ይካሄዳል ሲሉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የጠየቁ ሃሳባቸውን የሰነዘሩ አልጠፉም። ተክሌ ገብረ ኪዳን በፌስቡክ «ምን አይነት ምርጫ ነው ግን የሚካሄደው? ሀገር ባልተረጋጋበት ሰላም ባልሰፈነበት ነጻነት በሌለበት ሀገር?» ሲሉ ጠይቀዋል። አሰፋ ጌታብቻ ደግሞ ምርጫ እኮ በሕይወት ስንኖር ነው።ስልጣን ይዘው መሬቱን ይግዙት።ብለዋል በፌስቡክ አማራ ካሳ ደግሞ ምርጫው መካሄዱን ይደግፋሉ ነገር ግን «ትግራይን አይመለከትም የተባለው ምርጫ ወልቃይትና ራያን የማይጨምር መሆን አለበት። ትግሬ አይደለንምና አማራ ተወካዮቻችንን መምረጥ እንፈልጋለን።በማለት የራያና ወልቃይት ጉዳይ ከምርጫ በፊት ይታሰብበት ምክንያቱም ተወካዮቻችንን በታቀደው ቀን መምረጥ እፈልጋለን። ሲሉ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።ከምርጫ በፊት የህዝብ ቆጠራ መቅደም አለበት የሚሉት ጌትነት ቢምር ደግሞ እዚህ ምርጫ ላይ እንሟሟታለን በህይወት የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ነው። ያው የተለመደው የድምጽ ዘረፋውንም እንጠብቃለን ብለዋል።ብርሃን ደሳለ ምህረቱ ነፃ ምርጫ እንጠብቃለን አማራን የሚያስከብር መሆን አለበት ሲሉ
ይሄነው ብዙነህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ በምርጫ የሚያሸንፉ ፓርቲዎች ሥልጣን እንዲገድብ ሃሳብ አቅርበዋል።
«የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን ስልጣን በጊዜ መገደብ አለበት።ማለትም አንድ ፓርቲ ቢያንስ ሁለት ጊዜ /ከ10 ዓመት የበለጠ መምራት  የለበትም።ምክንያት አሁን ያለዉ የኢትዮጵያ  መንግስት ስልጣን ከያዘ 30ኣመቱ ነዉ።በዚህ ጊዜ 3 ለሀገሪቱ የሚመጥን አቅም ያላቸዉ የተለያዩ ፓርቲዎች ወደ መንበረ ሥልጣን መጥተው ህዝብን ባገለገሉ ነበር።ከአህዳዊ መንግስት በቀጥታ ስልጣንን በሀይል ይዞ 50% አምባነናዊ 50% ዲሞክራሲያዊ ብርዝ የመንግስት መዋቅር ይዞ ስለ ልማታዊ ዲሞክራሲ እያወራን ስለማንቀጥል ገዥዉ ፓርቲ በራሱ ሙሉ ፈቃድ ለሀገሪቱ ይመጥናል ለሚለዉ ተፎካካሪ ፓርቲ ቢያስረክብ ጥሩ ነዉ።በማለት የበኩላቸውን ሃሳብ ሰንዝረዋል።አራጋው ሁሴን ደግሞ ዲሞክራሲና ፍትሀዊነት፣ የፓርቲዎች ግልፅ አቋምና እንቅስቃሴ፤ ሁሉንም ማህበረሰብ አቃፊና አሳታፊነት እንዲሁም የምረጡኝ ቅስቀሳ ከኮናኝ አስኮናኝ ፖለቲካና ከውሸት ጥግ የራቀ መሆን ከዚህ ምርጫ  የምንጠብቀው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ


 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች