የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ታሰረ | ኢትዮጵያ | DW | 04.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ታሰረ

የሳምንታዊው ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ስም በቀረበበት የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ ጥፋተኛ በመባሉ ታሰረ፡፡ ጌታቸው ጥፋተኛ የተባለው በግንቦት 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ገዳምን አስመልከቶ በጋዜጣው ላይ ባሳተመው ጽሁፍ ምክንያት ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:37
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:37 ደቂቃ

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ታሰረ

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ስድስተኛ ወንጀል ችሎት ትላንት በዋለው ችሎት የኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁን ጥፋተኛ ያለው የቀረበበትን ክስ በበቂ ሁኔታ አላስተባበለም በማለት ነው፡፡ ጌታቸው ጥፋተኛ የተባለው ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በፊት በጋዜጣው በወጣ ዜና ምክንያት ነው፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር አማካኝነት የተዘጋጀው ይኸው ዜና በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ገዳም ተከናውኗል የተባለ የንብረት እና የገንዘብ ምዝበራን የሚመለከት ነበር፡፡ ጋዜጣው ሁኔታውን ከሚያውቁ እና ከሰበካ ጉባዔ አባላት አገኘሁት ባለው መረጃ እና ሰነዶች ላይ ተመስርቶ ዜናውን እንደሰራ ቢገልጽም በቤተከርስቲያኒቱ ጠበቃ ክስ ቀርቦበታል፡፡

ዋና አዘጋጁ በወንጀል ህግ በአንቀጽ 613 “ስማ ማጥፋት እና የሐሰት ሐሜት” በሚል የተቀመጠውን ተላልፏል በሚል ነበር የተከሰሰው፡፡ ሁለቱም ወገኖች የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ በጉዳዩ ላይ ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡ የግራ ቀኝ ክርክሩን ሲያስተናግድ የቆየው ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛ ጌታቸው በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሦስት የተገለጸውን እና “ጥፋተኛው ወንጀሉን የፈጸመው በመልካም ስም ላይ ከባድ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ” እንደሆነ የሚለውን ጠቅሶ የጥፋተኛነት ብይን መስጠቱን የዋና አዘጋጁ ጠበቃ አቶ በኃይሉ ተስፋዬ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡

“የተቀጠረው ለፍርድ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ከሳሾች ያቀረቡትን ማስረጃ ማስተባበል አልቻለም በማለት ጥፋተኛ ብለውታል፡፡ ከሳሾችም እንዲሁም በጌታቸው በኩል እኛም የቅጣት ማቅለያዎችን እና ማክበጃዎችን አቅርበናል፡፡ ቅጣቱን ለመወሰን ለህዳር ስድስት ተቀጥሯል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ማረሚያ ቤት ይቆይ የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶ ችሎቱ ተደምድሟል” ብለዋል ጠበቃው፡፡

ትናንት በዋለው ችሎት በከሳሽ በኩል ማክበጃ ከማቅረብ በዘለለ የቅጣት አስተያየት አለመቅረቡን ጠበቃ በኃይሉ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በጋዜጣው ላይ ታትሞ እንዲወጣ ትእዛዝ እንዲሰጥላቸው ማመልከታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ጌታቸው በተከሰሰበት አንቀጽ ጥፋተኛ የተባለ ተከሳሽ ከሦስት ወር የማያንስ ቀላል እስራትና መቀጮ እንደሚበየንበት የወንጀል ህጉ ቢደንግግም አቶ በኃይሉ ግን እስከ ሦስት ዓመት ሊፈረድበት እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ 

“ቅጣቱ ከሶስት ወር የማያንስ ቀላል እስራት ነው ይህ ማለት ከሶስት ወር እስከ ሶስት ዓመት ባለው ውስጥ ሊያርፍ ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ በቀረበለት የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ መሰረት አድርጎ ካሰላ በኋላ በዚህ  የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ቅጣቱን ሊያሳርፍ ይችላል” ይላሉ ጠበቃው፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ትናንት ከችሎት በኋላ በወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ የታሰረ ሲሆን የቅጣት ውሳኔውን በፍርድ ቤት እስከሚቀበል በእስር ወደሚቆይበት ቂሊንጦ የእስረኞች ማረሚያ ቤት ዛሬ ተዛውሯል፡፡ ከሦስት ቀናት በፊት በአሜሪካ ኤምባሲ በተዘጋጀ አንድ ዝግጅት ላይ ከጌታቸው ጋር ታድሞ የነበረው ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ዋና አዘጋጁ “እታሰራለሁ” የሚል ስጋት እንደነበረበት ይገልጻል፡፡ 

“እዚያ ላይ ረጅሙን ሰዓት ከዚህ ከክሱ ጋር በተገናኘ ነበር አሜሪካ ኤምባሲ ለነበርነው ሰዎች ሲነግረን የነበረው፡፡ ውስጡ ስጋት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጋዜጠኝነት ምን ዓይነት ውሳኔ እንደሚሰጥ መገመት ይከብዳል፡፡ አያስቀጣም ያልኸው ነገር ሰዎች ተቀጥተው፣ ተፈርዶባቸው እስር ቤት አሉ፡፡ ያስቀጣል ያልኸው ነገር ደግሞ ሰዎች ወይ ክሳቸው ሲቋረጥ ወይ በነጻ ሲወጡ ታያለህ እና ከኢህአዴግ ባህሪ አኳያ ምን ዓይነት ውሳኔ  ለጋዜጠኛው እንደሚሰጥ መገመት ይከብዳል፡፡ ከዚያ በመነሳትም ይመስለኛል ስጋት አድርበት የነበረው” ሲል በወቅቱ የነበረውን የጌታቸው ስሜት ይገልጻል፡፡

የጌታቸው መታሰር ዳፋው ለ“ኢትዮ-ምህዳር” ህልውናም እንደሚተርፍ ኤልያስ ይናገራል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ህትመቱ ሲቋረጥ የነበረው ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ አታሚ የማጣት አደጋ ተደቅኖበት እንደነበር ጌታቸው ከሁለት ሳምንት በፊት ለዶይቸ ቨለ በሰጠው ቃለ ምልልስ ገልጾ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግን ተሳክቶለት ጋዜጣውን ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከአብዛኛውን የ“ኢትዮ-ምህዳር” ስራ ጀርባ የነበረው ዋና አዘጋጁ እንደመሆኑ ከእርሱ እስር በኋላ የጋዜጣው የወደፊት ዕጣ ፈንታ አጠያያቂ እንደሆነ ኤልያስም ሆነ ጠበቃው አቶ በኃይሉ ይገልጻሉ፡፡  


ተስፋለም ወልደየስ 
አዜብ ታደሰ  

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች