የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞ (ዉይይት) | ኢትዮጵያ | DW | 31.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞ (ዉይይት)

የመንግሥትም ሆነ የገዢዉ ፓርቲ እርምጃዎች ግን ግጭት፤ ሁከቱን ለመፍታት አልጠቀሙምም።በየአካባቢዉ ለተቃዉሞ የሚታደመዉን ሕዝብ ጥያቄም በትክክል የመለሱ አይመስልም።እንዲያዉም  የገዢዉ ግንባር የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር መሻኮት እና መወዛገባቸዉ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነዉ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 28:46

መንግሥት እና ሕዝብ እየተግባቡ  ይሆን?

ሕዳር 2008 ጊንጪ ኦሮሚያ መስተዳድር እንደነዘበት የተጀመረዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ከዚያ በፊት ብልጭ ድርግም የሚሉ ተቃዉሞችን ሁሉ በልጦ፤ መልክ እና ባሕሪዉን እየለዋወጠ አድማሱን እያሰፋ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ።

ኢትዮጵያ ዛሬ ተቃዉሞ ሠልፈኞች እና ፀጥታ አስከባሪዎች፤ የተለያዩ ጎሳ አባላት፤ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚጋጩባት፤ ባለሐብቶች እና ነዋሪዎች የሚወዛገቡባት ሐገር ሆናለች።የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት ሁለተኛ ዓመቱን ባስቆጠረዉ ግጭት በትንሽ ግምት ከ1500 በላይ ሰዉ ተገድሏል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል።

ኢትዮጵያ ሚሊዮኖች የሚራቡባት ደግሞ በተቃራኒዉ አስደናቂ የምጣኔ ሐብት ዕድገት ማስዝገቧ የሚነገርባት፤ ሙስና አለቅጥ የተሰራፋባት ሐገርም ናት።

መንግስት ግጭት፤ ግድያ፤ ሁከቱን ለማስቆም በሚል ምክንያት የባለሥልጣናት ሹም ሽር አድርጓል።አስር ወራት የዘለቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ ነበር።ከ25ሺሕ በላይ ዜጎችን ባብዛኛዉ ወጣቶችን በየወታደራዊዉ ማሰልጠኛ ጣቢያ አስሮም ነበር።«አመፅ ቀስቃሽ» ያላቸዉን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፤ ወጣቶችን እና በሙስና የጠረጠራቸዉን ባለሥልጣናት አስሯል።ከሷልም።ገዢዉ ፓርቲ ኢሕአዴግም ጥልቅ ያለዉን ተሐድሶ ለማድረግ ቃል ገብቷል።ሐገር ዉስጥ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ከጀመረም ዓመት ሊደፍን ሳምንታት ነዉ የቀሩት።

የመንግሥትም ሆነ የገዢዉ ፓርቲ እርምጃዎች ግን ግጭት፤ ሁከቱን ለመፍታት አልጠቀሙምም።በየአካባቢዉ ለተቃዉሞ የሚታደመዉን ሕዝብ ጥያቄም በትክክል የመለሱ አይመስልም።እንዲያዉም  የገዢዉ ግንባር የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር መሻኮት እና መወዛገባቸዉ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነዉ።ለኢትዮጵያ መንግሥት ጠንካራ ድጋፍ የሚሰጡት የአዉሮጳ ሕብረት እና ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን የሚያብጠዉን ፖለቲካዊ ቀዉስ «አሳሳቢ» ማለት ከጀመሩ ሰነባብተዋል።ኢትዮጵያ ወዴት እያመረች ነዉ።መንግሥት እና ሕዝብ እየተግባቡ  ይሆን? ኢትዮጵያዉያንስ ምን ማድረግ አለባቸዉ? የዛሬዉ ዉይይታችን ትኩረት ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

 

Audios and videos on the topic