የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ | ኢትዮጵያ | DW | 18.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ

ሰላማዊ ክርክር አስፈላጊ ነዉ።ግን ክርክሩ አይደለም ሙከራዉም የለም።እንዲያዉም ክርክር፤ ዉይይትን ማስተናገድ የሚገባቸዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቆጣጠሯቸዉ መገናኛ ዘዴዎች በዉይይት ክርክሩ ፋንታ ሐቅ-ሕቅታ ሆኖባቸዉ፤ ሐቅ ለሚዘግቡ ጋዘጠኞች የጋዜጠኝነት hሀሁን ለማስተማር ሲንተፋተፉ፤ ከእዉነት ጋር ሲጋጩ ማየት-መስማታችን ነዉ ድንቁ።

 

ባለፈዉ ሳምንት የዛሬን ዕለት የኢትዮጵያ መንግሥት ፖለቲከኞች ሥለ ተሐድሶ ለዉጥ ሲያወሩ፤ በሚቆጣጠሩት መገናኛ ዘዴ ሲያሰራጩ ነበር።የፖለቲከኞቹን ቃል ተስፋ የሰሙ የመንግሥታት፤ የድርጅቶችና የማሕበራት መሪዎች፤ ዲፕሎማት፤ተንታኞች ለዉጡን ሲጠብቁ እነሆ ሳምንት ደፈነ።የለዉጡ ትክክለኛ ዓላማ፤ የሚለወጠዉ ደንብ፤ መርሕ ወይም ሕግ የትኛዉነት በግልፅ የሚነገርበት፤ ገቢራዊነቱ የሚጀመርበት ጊዜ ሲናፈቅ ከአዲስ አበባ ባለሥልጣናት ሌላ ደንብ ወይም መመሪያ ሰማን-«የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ»። 

በኢትዮጵያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዴቪድ ሺን እንደሚሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለፈዉ ሕዳር ጀምሮ የሚካሔደዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞና አመፅ ሐገሪቱ ከ1997ቱ ምርጫ ወዲሕ ከገጠማት ተቃዉሞ ሁሉ እጅግ የከፋና ከፍተኛ ነዉ።አላበሉም።የመንግሥት ፀጥታ ሐይላት በተቃዋሚዉ ሕዝብ ላይ በወሰዱት የሐይል እርምጃ የተገደለዉ ሰዉ ቁጥርም የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት በትንሽ ግምት ከሰባት መቶ ይበልጣል። የቆሰለና የታሰረዉ ሰዉ በብዙ ሺሕ ይቆጠራል።የጠፋዉ ሐብት ንብረትን መጠን እስካሁን የገመተዉ የለም።

 

እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2006 እስከ 2010 በኢትዮጵያ  የጀርመን አምባሳደር የነበሩት ዶክተር ክላስ ክኖፕ እንደሚሉት የብዙ መቶዎችን ሕይወት ያስጠፋዉ፤ ሺዎችን ያስቆሰለ፤ ብዙ ሺዎችን እስር ቤት ያሳጎረዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞና አመፅ ባንድ ወቅት የተፈጠረ አይደለም።ለረጅም ጊዜ የተጠራቀመ ብሶት ዉጤት እንጂ።«እንደሚመስለኝ አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተፈጠረዉ ነገር እንደሚፈጠር እኔ  ኢትዮጵያ እያለሁ በሆነ ደረጃ መገመት ይቻል ነበር።

ምክንያቱም የ1997ቱን ምርጫ እና የ2002 ቱንም ስናስታዉስ፤ የማይዘነጋ ነገር አለ።ለምሳሌ አሁን በስራ ላይ ያለዉን የኢትዮጵያን የምርጫ ሕግ ስናይ በኔ አመለካከት ለዉጥ እንደሚያስፈልገዉ ሊታሰብበት የሚገባ ነዉ።»

 

ያሰበበት የለም።ወይም ማሰብ አልተፈለገም።ሕጉን አሻሽሎ ተገቢዉን የዴሞክራሲያዉ ሥርዓት ግንባታ ከመከተል ይልቅ በ2007ቱ ምርጫ ገዢዉ ፓርቲ ኢሕአዴግ የመቶ በመቶ ድል ማስመዝገቡን ነዉ የነገረን።የምርጫዉ ድል የገዢዉን ፓርቲ መሪዎች፤ አባላትና ደጋፊዎች ጮቤ አስረግጦ ሳያበቃ፤ መቶ በመቶ የተቆጣጠሩት ምክር ቤት የመሠረተዉ መንግሥት ተደላድሎ ሳይቀመጥ ያ መቶ በመቶ ድምፁን ሰጠን ያሉት ሕዝብ ሲያምፅ የፖለቲካ ታዛቢዎች ደጋግመዉ እንዳሉት የአመፁን ትክክለኛ ምክንያት ማወቅ፤ ካለወቁ መጠየቅ በርግጥ  የብልሆች መላ በሆነ ነበር።ይሕም አልሆነም።

 

ሕዝባዊዉ አመፅ የተቀሰቀሰዉ አምና ይሔኔ አዲስ መንግሥት በተመሠረተ ሁለት ወር ሳይሞላዉ ነበር።ሕዳር።ኢትዮጵያ ነፃ ምርጫ አድርጋ ከነበረ፤ አንድ ፓርቲ የመቶ በመቶ ዉጤት በማስዝገብ ገዢ ፓርቲዋ በዓለም የመጀመሪያዉ ሳይሆን አልቀረም።በአንድ ሐገር ታሪክ አዲስ መንግሥት በተመሰረተ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ሲነሳበትም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሳትሆን አትቀርም።

 

ሆነችም አልሆነች ሕዳር ላይ ለተነሳዉ ሕዝባዊ፤ ሰላማዊ ጥያቄ  ተገቢዉ መልስ ተስጥቶ ቢሆን ኖሮ እስካሁን የደረሰዉ ጥፋት ባልደረሰ ነበር።ጥፋቱ ከደረሰ በኋላም ሌላ የከፋ ጥፋት እንዳይደርስ ብዙ ተንታኞች እንደሚሉት ከጥያቄ አቅራቢዉ ሕዝብ ወይም በትክክል ከሚወክሉት ወገኖች ጋር መነጋገር የአርቆ አሳቢዎች ምግባር ነዉ።ዛሬም ሌላ ምክር አይሰማም።

በኢትዮጵያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዴቪድ ሺን እንደሚሉት ሕይወት፤ አካል፤ ሐብት ንብረት ያጠፋና የሚያጠፋዉን ቀዉስ ለማስወገድ ከእንግዲሕም አብነቱ የፖለቲካዉን ሥርዓት መክፈት ነዉ።«የኔ ምክር ምናልባት ከተፈለገ፤ የፖለቲካ ሥርዓቱን መክፈት ነዉ።የቀድሞዉ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ተንሳይ ከጥቂት ወራት በፊትን ያሰራጩትን መልዕክት እጋራለሁ። ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ እና የፖለቲካዉን ሂደት መክፈት ይገባል ነዉ ያሉት።ኢትዮጵያ ዉስጥ ይህ ሁኔታ እስኪኖር ድረስ ተቃዎሞና አመፁ ይቀጥላል።ተቃዉሞና አመፁን ለማገድ የሐይል እርምጃ መዉሰድ መፍትሔ አይሆንም።»

 

የፖለቲካዉን ሒደት መክፈት።ባለፈዉ ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት «የተሐድሶ ለዉጥ» ለማድረግ መዘጋጀታቸዉን ተናግረዉ ነበር።እስከ ዛሬ ግን የተደረገ ወይም የተጀመረ ነገር የለም።ካለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገቢራዊ የሚሆንበትን መመሪያ ማወጅ ነዉ።መገናኛ ዘዴዎችን መከታተል፤ፅሁፎችን ማንበብ፤ መያዝ ፤ ምልክት ማሳየት ሳይቀር የሚያስቀጣዉ መመሪያ ወትሮም ሕዝብ በአደባባይ የሚጮሕለትን የዜጎች መብት እና ነፃነቶችን የሚገድብ ነዉ።

መመሪያዉ

አንድ ዓመት ወደ ኋላ ተመልሶ በሥልጣን ላይ ያለዉ መንግሥት «ጥፋት» በሚለዉ እንቅስቃሴ የተሳተፈ ወይም ባለሥልጣናቱ «ተስትፏል» የሚሉትን የሚያስቀጣ ነዉ።ሥብሰብ ለሰባዊ መብት በኢትዮጵያ የተሰኘዉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ሐይለ ማርያም አዋጁ የደነጋገቸዉን ነጥቦች «አስደማሚ» ይሉታል።ጥቅል ይዘቱን ደግሞ ዓለም አቀፍ ደንቦችን የጣሰ

አቶ ያሬድ አክለዉ እንዳሉት አዋጁ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን የሚፈፅመዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚቀጥልበት የሚያረጋግጥ ነዉ።ለእስካሁኑም ሆነ ወደፊት ለሚፈፅማቸዉ የመብት ረገጣዎች ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ያለመም ነዉ።

አዋጁ የዜጎችን መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች የሚደፈልቅ እንዳይሆን ዩናይትድ ስቴትስ፤ የአዉሮጳ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት፤ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እና አቀንቃኞች በተለያየ መንገድ አሳስበዉ ነበር።ኢትዮጵያ የገጠማትን ፖለቲካዊ ቀዉስ ለማስወገድ የሐገሪቱ መንግሥት የሐገራቸዉ ጉዳይ ከሚያገባቸዉ ዜጎች ጋር እንዲነጋገር ጠቁመዉም ነበር።ማሳሰቢያ ጥቆማዉ አደባባይ እንደወጣዉ ሕዝብ ጮኸት ሁሉ የአዲስ አበባ ሾማምንቶችን ጆሮ ያገኘ አይመስልም።ለማሳሰቢያ፤ ምክሩ፤ ከሁሉም በላይ ከደቡብ-ኮንሶ እስከ ሰሜን ጎንደር የሚጮኸዉን ሕዝብ ጥያቄ ማጣጣል ወይም በአዋጅና መመሪያ ማሸማቀቅ ታዛቢዎች ደጋግመዉ እንዳሉት የፖለቲካ ቀዉሱን ለማቃለል የሚፈይደዉ የለም።

በአዋጅና መመሪያ የአገዛዝ ዘመንን ለማራዘም የሞከሩ ሐይላትን ፍፃሜ ከኢትዮጵያዉን የተሻለ የሚያዉቁ ካሉ ጥቂት ናቸዉ።ያልተሞከረዉን መሞከር፤ ለፖለቲካዊ ቀዉስ ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ጀግንነት እንጂ-በርግጥ ጅልነት ሊሆን አይችልም።በኢትዮጵያ የቀድሞዉ የጀርመን አምባሳደር ክላስ ክኖፕ እንደሚሉት ለኢትዮጵያ መፍትሔዉ ድርድር እንጂ ፍልሚያ አይደለም።

«አሁን የሚያስፈልገዉ ሁሉም (ማለት) በተቃዋሚዉ ጎራ የተደራጁ ሰዎችና በመንግስት

ወገን ያሉ ሐይላት በሙሉ ፀጥታ አስፍነዉ መነጋገር ያስፈልጋቸዋል።መፋለም የለባቸዉም።ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ዉስጥ ሊመጣ የሚችለዉ፤ ነዉጥ ይስፋፋል።ይሕ ለኢትዮጵያ ችግሮች መፍትሔ አይሆንም።ሰላማዊ ክርክር አስፈላጊ ነዉ።»

ሰላማዊ ክርክር አስፈላጊ ነዉ።ግን ክርክሩ አይደለም ሙከራዉም የለም።እንዲያዉም ክርክር፤ ዉይይትን በማስተናገድ የሚገባቸዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቆጣጠሯቸዉ መገናኛ ዘዴዎች በዉይይት ክርክሩ ፋንታ ሐቅ-ሕቅታ ሆኖባቸዉ፤ ሐቅ ለሚዘግቡ ጋዘጠኞች የጋዜጠኝነት ሐሁን ለማስተማር ሲንተፋተፉ፤ ከእዉነት ጋር ሲጋጩ ማየት-መስማታችን ነዉ ድንቁ።

አምባሳደር ዴቪድ ሺን እንደሚሉት ፖለቲካዊ ሒደቱን መክፈት አይገድም።ግን መንግሥት  እስካሁን ፈቃደኞች አይደለም።«መንግሥት ፖለቲካዊ ሂደተኞችን በመክፈት እና የተሻለ ሰላማዊ እርምጃ የመዉሰድ አፀፋ በመስጠት ችግሩን ማስወገድ ይችል ነበር።እስካሁን ድረስ በኔ አመለካከት ፈቃደኝነቱን አላሳዩም።»

ከመንግሥት እስካሁን በግልፅ የተነገረዉ መፍትሔ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ነዉ።የመብት ተሟጋቾች ችግሩን የሚያባብስ ማለታቸዉ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ። 

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

ተዛማጅ ዘገባዎች