የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ | ኢትዮጵያ | DW | 19.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ

የመንግሥት አፀፋ እንደ ጥያቄ አቅራቢዉ ዘር፤ሐይማኖት፤ የፖለቲካ ዝንባሌ ለየቅል ነዉ።ጠባብ፤ ትምክሕተኛ፤አሸባሪ፤ ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ መንግስታዊዉን ሥርዓት ለመናድ የሚያሴር ወዘተ የሚል ቅጣቱ ግን ተመሳሳይ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:44

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ

ኢትዮጵያን፤ ከደቡብ ምዕራብ-ኮንሶ እስከ ሰሜን ምዕራብ ወልቃይት ጠገዴ፤ የሚያብጠዉ ተቃዉሞ-ግጭት፤ውድመት-ጥፋት እንዳይከሰት የኢትዮጵያ መሪዎችን የመከሩ፤የሞገቱ፤ያስጠነቀቁም ነበሩ።የሰማቸዉ እንጂ የተቀበላቸዉ አልነበረም።ሕዝባዊ ተቃዉሞዉ፤ ግጭት፤ግድያ፤ኪሳራ-ጥፋቱ አሁን ከደረሰበት ደረጃ እንዳያልፍ የሚናገሩ፤የሚከራከሩ፤የሚያስጠነቅቁ፤ የሚማፀኑም አሉ።እስካሁን ለመፍትሔ የሚጠቅም መልስ የሰጠ የለም። የግጭት ግድያዉ መነሻ፤ መፍትሔ የማጣቱ ምክንያት እና የከፋ እንዳይመጣ ስጋት አለ።

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ መንግስት (የደርግ) ባለሥልጣናት ከ1982 ማብቂያ ጀምሮ እስከ ሥልጣናቸዉ ፍፃሜ በተደጋጋሚ ይሉ-ያስጠነቅቁት ከነበረዉ አንዱ፤ የያኔዉ አማፂ ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (የኢሕአዴግ) ጦር አዲስ አበባ ከገባ ርዕሠ ከተማይቱ ሞንሮቪያ ወይም ሞቃዲሾ ሐገሪቱ ላይቤሪያ ወይም ሶማሊያ ይሆናሉ አይነት መልዕክት ነበረዉ።

ምክንያቱን ሁሉም እንደየእምነት ፍላጎቱ፤የሕዝቡ ጨዋነት፤ፆም-ፀሎት ምሕላዉ፤ የደርግ መሪዎች ሥልጣን መልቀቅ፤ወይም የኢሕአዴግ ሥልት፤ ሌላም እያለ መዘርዘር ይችል ይሆናል።ባንዱም ሆነ በሁሉም ምክንያት የተባለዉ አለመድረሱ ግን ሐቅ ነዉ።

15ኛ ዓመቱ-1997ቱ ምርጫ ተቃዋሚዎች ማሸነፋቸዉ አይቀርም በሚባልበት ወቅት የገዢዉ ፓርት መሪዎች ተቃዋሚዎችን በሩዋንዳዉ ሕዝብ ጨፍጨፊ ሚሊሺያ መስለዋቸዉ ነበር።ኢትራሐምዌ-ብለዉ።የተቃዋሚዎቹ ዓላማ፤አቅም፤ፍላጎትንም ሥላልነበረ የጊዜ ሒደት የተሰጣቸዉን ስም ሐሰትነት አረጋግጦ አለፈ።

26ኛ ዓመቱ ዘንድሮ ደግሞ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ የ1986ቷን ሩዋንዳ ትሆናለች እያሉ ነዉ።የኢሕአዴ ከፍተኛ ባለሥልጣን አባይ ፀሐይዬ ናቸዉ።

የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ፕሮፌሰርና አሁን ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በጥብቅና ሙያ የሚሰሩት አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ የአባይ ፀሐይዬን «ማቆሚያም የለዉ» ማስጠንቀቂያን አይቀበሉትም።ይሁንና እንደ ብዙዉ ኢትዮጵያዊ ሥጋቱን ይጋራሉ።መፍትሔዉም ከመንግሥት እጅ ነዉ ባይ ናቸዉ።

ዛሬ የዘር መጠፋፋት ያስከትላል የሚበለዉ ቀዉስ ብዙዎች እንደሚሉት በምሽት የተፈጠረ አይደለም።ባለፉት ሐያ አምስት ዓመታት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤የመብት ተሟጋቾች፤ ጋዜጠኞች፤የሐይማኖት መሪዎች ሌላዉ ቀርቶ የገዢዉ ፓርቲ ባለሥልጣናት የነበሩ ዛሬ የሚባለዉን ሲሉት ነበር።መንግሥት ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዉ መብቶችን ያክብር።

የመንግሥት አፀፋ እንደ ጥያቄ አቅራቢዉ ዘር፤ሐይማኖት፤ የፖለቲካ ዝንባሌ ለየቅል ነዉ።

ጠባብ፤ ትምክሕተኛ፤አሸባሪ፤ ሕገ-መንግሥቱንና ሕገ መንግስታዊዉን ሥርዓት ለመናድ የሚያሴር ወዘተ የሚል ቅጣቱ ግን ተመሳሳይ ነዉ።መግደል፤መወንጀል፤ ማሰር፤ ማስፈረድ፤ አለያም ማሰደድ።የሕግ ምሑሩ አቶ ሙሉጌታ መሠረታዊዉን ምክንያት ባጭሩ ይገልፁታል።

የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎቹን ሕገ-መንግሥትን ጣሱ በማለት ያስፈራራል፤ ይወነጅላል፤ ያስራል፤ይፈርዳል። አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት የሕገ-መንግሥቱ ዓላማ ዜጎችን ከመንግስት ጭቆና ለመጠበቅ ነበር።በገቢር ግን «መንግሥት ዜጎችን መጨቆኚያ» ነዉ ያደረገዉ።

መንግሥት የሚወነጅላቸዉ ፖለቲከኛ፤ ጋዜጠኞች፤የመብት ተሟጋች፤ የሐይማኖት መሪዎች ይሆኑ ይሆናል፤ ሁሉም መንግሥት የራሱን ሕገ-መንግሥት አላከበረም ይላሉ።ምሑራንም ከአቶ ሙሉጌታ እንደሰማነዉ መንግሥትን ይተቻሉ።

የሕገ መንግስቱ ይዘት እንዴት ይበየናል? መከበር አለመከበሩስ? «ቀላል ነዉ» ይላሉ አቶ ሙሉጌታ።

የኢትዮጵያ መንግስት ሕገ-መንግሥቱን ጥሶ ሥልጣኑን በሙሉ ያለገደብ መቆጣጠሩ በየአካባቢዉ ቅሬታን ፈጥሯል።ቅሬታዉ ፈጣን መልስ አለማግኘቱ መለገምን አስከትሏል።ከዚያ የአደባባይ ተቃዉሞ።አቶ ሙሉጌታ ሰዉ «መተንፈሻ ሲያጣ---» እያሉ ይቀጥላሉ።

እስረኛ ወሩን ባገባደደዉ ተቃዉሞ በአብዛኛዉ የመንግሥት ፀጥታ ሐይላት በወሰዱት እርምጃ የመብት ተሟጋቾች እንደገመቱት በትንሹ ሰባት መቶ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።ብዙዎች ቆስለዋል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ታስረዋል።ወሕኒ ቤቶች፤ መስሪያና መኖሪያ ቤቶች ጋይተዋል።እስካሁን ለደረሰዉ ጥፋት በአብዛኛዉ ሐላፊነቱን መዉሰድ ያለበት አቶሙሉጌታ እንደሚሉት መንግሥት ነዉ።

መንግሥት ተጠያቂነቱን ሊቀበል ቀርቶ ከአቋሙ የመለሳለስ አዝማሚያም አላሳየም።ከአደባባይ ሠልፍ ፈተናን አሽሉኮ እስከ ማዉጣት፤ ከግብይት እስከ ቁጭታ አድማ የደረሰዉ ተቃዉሞም በየአካባቢዉ ከረር-ረገብ እያለ እንደቀጠለ ነዉ።

የሐይል- እርምጃዉም እንዲሁ።

መንግሥት የሚቆጣጠራቸዉ ወይም ለመንግሥት ቅርበት ያላቸዉ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት መንግሥት መስከረም ማብቂያ ላይ ባለሙያዎች (ቴክኖ ክራትስ) ን ያካተተ ካቢኔ ለመመስረት ሳያቅድ አልቀረም።የተባለዉ ከተደረገ ከሐይል እርምጃዉ በተጨማሪ ሁለተኛዉ የመንግሥት መፍትሔ መሆኑ ነዉ።ችግሩን ማስወገዱን ግን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።

የእስካሁኑ ችግር ሌላ ችግር እንዳይወልድ መከላከያዉ ብልሐት በርግጥ ይናፍቃል።ብዙዎች እንደሚሉት መዘግየት የለበትምም። ይሁናና ገለልተኛ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት እንደ ችግሩ መደራረብ ሁሉ መፍትሔዉም አንድ ወይም ሁለት ብቻ ተብሎ የሚታለፍ አይደለም።ብዙ ጉዳዮችን የሚያጣቅስ፤

ብዙዎችን የሚያካትት፤ ከሁሉም በላይ የብዙዎችን ፍላጎት፤ፖለቲካዊ ፍቃደኝነትና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነዉ።ግን ካንድ ቦታ መጀመር አለበት።

እስከ ዛሬ የተሰጡ ሐሳቦች፤ትችቶች፤ጥቆማ-ጥያቄዎች ባክነዋል።የዛሬና የከእንግዲሁ የእስከ ዛሬዉ እጣ እንዳይደርሳቸዉ እንመኝ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic