የኢትዮጵያ ፖለቲካና የኦዴግ አቋም | ኢትዮጵያ | DW | 27.02.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ፖለቲካና የኦዴግ አቋም

በኦሮሚያ እና በአማራ መስተዳድሮች፤  የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞና አመፅ ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተቃዋሚ ሆኑ ገዢ የሕዝቡን የልብ ትርታ በቅጡ እንደማያዳምጡ ጉሉሕ አብነት ነዉ-የሆነዉ።አቶ ሌንጮ ለታ ደግሞ ተቃዉሞዉን የሕዝቡን ብስለት ጠቋሚ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት መሠረት ጣይ፤ ለፖለቲከኞች አስተማሪም ይሉታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:59

የኢትዮጵያ ፖለቲካና የኦዴግ አቋም

በ1965 የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦነግ) በሕቡዕ ሲመሠረት ከመስራቾቹ አንዱ ነበሩ። በ1983 የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ሲመሠረት ስማቸዉ ከገነነ ፖለቲከኞች አንዱ ነበሩ። ዛሬም ንቁ ፖለቲከኛ ናቸዉ። አሁንም ሥለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ይናገራሉ።ሥለ ፖለቲከኞችዋ ይጠይቃሉ።   አቶ ሌንጮ ለታ። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር መሥራችና ፕሬዝደንት።
                     
የ1965ቷ ኢትዮጵያ ተማሪዎቿ፤ወጣት ምሁራንዋ፤ባለሙያዎችዋ፤  ወታደሮችዋ ሌሎችም ለለዉጥ የተነሳሱባት፤ በለዉጥ ማዕበል የምትነዳ ሐገር ነበረች። የያኔዉ ወጣት ሙሕርም ከብዙ የዕድሜ አቻዎቹ የተለየ አልነበረም።
                               
ተመኘ።ጀመረዉ።እነሱ ይሮጣሉ። ጊዜ ግን ይከንፋል። 18 ዓመት። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ፖለቲካም ተቀየረ። 1983። አዲስ አበባ አዲስ ሥርዓት ተመሰረተ። የሽግግር መንግስት። ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ቀጥሎ የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር ከሽግግር

መንግሥቱ  መሥራች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለተኛዉ ትልቅ ፓርቲ ነበር።
የፓርቲዉ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ሌንጮ ለታም ከአቶ መለስ ዜናዊ ቀጥሎ ሁለተኛዉ ትልቅ ፖለቲከኛ ሆኑ።ዳር አልዘለቀም።አቶ ሌንጮ ዛሬ እንደሚሉት ግን ነገሩ ሁሉ መጀመሪያም የሆነዉ በፍላጎት ሳይሆን በግፊት ነበር። 
                              
ጊዜዉ መክነፉን አላቆመም። ፖለቲካዊዉ ለዉጥም እንደቀጠለ ነዉ።በጠመንጃ፤ በራዲዮ-ጋዜጣ  ይደረግ በነበረዉ ትግል ላይ የኮምፒዉተር በተለይም ኢንተርኔት እና የተንቀሳቃሽ ሥልክ አገልግሎት ታከለበትም። አቶ ሌንጮ  ዛሬም ይታገላሉ።አስተሳሰብ፤ የትግል ሥልታቸዉ ግን ተለዉጧል።
                         
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) በተመሠረተ በዓመት ከመንፈቁ ኢትዮጵያ በሕዝባዊ ተቃዉሞ «ትንፈቀፈቅ» ገባች።በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ መስተዳድሮች፤  የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞና አመፅ ታዛቢዎች እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተቃዋሚ ሆኑ ገዢ የሕዝቡን የልብ ትርታ በቅጡ እንደማያዳምጡ ጉሉሕ አብነት ነዉ-የሆነዉ።አቶ ሌንጮ ለታ ደግሞ ተቃዉሞዉን

የሕዝቡን ብስለት ጠቋሚ፤ ለኢትዮጵያ አንድነት መሠረት ጣይ፤ ለፖለቲከኞች አስተማሪም ይሉታል።
                                  
የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የኢሕአዴግ እና የተቃዋሚዎቹ ተወካዮች በቅርቡ ድርድር ጀምረዋል።ተደራዳሪዎቹ ባለፈዉ አርብ  «የመደራደሪያ ረቂቅ ሐሳብ» ያሉትን ሰነድ አጥንተዉ ዳግም ለመሰብሰብ ቀጠሮ ይዘዋል። አቶ ሌንጮ የሚመሩት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በድርድሩ እንዲካፈል አልተጋበዘም። የድርድሩን ሒደት ግን ከሩቅም ቢሆን እየተከታተለ ነዉ።
                              
ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ እስከወጣበት እስከ 1984 ድረስ የኦነግ እና የኢሕአዴግ፤ የኦነግና የሻዕቢያ፤ ግንኙነት ጥብቅ እንደነበር በሰፊዉ ይታመናል። የሰወስቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ግንኙነት ደግሞ በሌንጮ-መለስ-ኢሳያስ ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ ነበር።
                           
ዛሬ አብዛኛዉ በርግጥ ትዝታ ነዉ። የከእንግዲሁ አጓጊ። አቶ ሌንጮ ለታን በጣም አመሰግናለሁ።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ


 

Audios and videos on the topic