የኢትዮጵያ ፖለቲካና የእስራት ዘመቻ | ኢትዮጵያ | DW | 19.09.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ፖለቲካና የእስራት ዘመቻ

ዓለም በፀረ-ሽብር ወታደራዊ ዘመቻዉ በተሳላቸበት፥ የወታደራዊ ዘመቻዉን ድል በሚያጠራጥርበት ባሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አዲስ የፀረ-ሽብር ሕግ ማፅደቋ ነዉ ግራዉ።በአዲሱ ሕግ ተጠርጥረዉ የታሰሩ፥ የተከሰሱት በሰላማዊ መንገድ እንደሚታገሉ ያስታወቁ ፖለቲካኞች፥ ወይም ወረቀት-እስኪሪብቶ «የታጠቁ» ጋዜጠኞች መሆናቸዉ ነዉ-አሳሳቢዉ ድቀት

default

ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ

19 09 11

ዶክተር ሞጋ ፊሪሳ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሊቀመንበር።አቶ ሽመልስ ከማል-የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ።
እንደገና እስራት፣ እንደገና ዉንጀላ። እንደገና ዉዝግብ።«አቶ አርጋዉ (አሽኔ) መታሰርና መወንጀልን ፈርቶ ከሐገሩ ለመዉጣት ወሰነ።»

መሐመድ ኬይታ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪዉ (CPJ-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) የአፍሪቃ ጉዳይ ምክትል ሐላፊ።እንደገና ፍርሐት፥ እና ስደት።የኢትዮጵያ ፖለቲካ።ግን ለምን? ደግሞስ እስከመቼ?
ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

አፍቃን-አሜሪካዊዉ ዲፕሎማት አምባሳደር ዛልማይ ማሞዚይ ኻሊልዛድ ከካቡል ባግዳድ በተቀየሩ በወራት እድሜ ለዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኮንደሊዛ ራይስ ፈራ-ተባ እያሉ ያቀረቡት የድርድር ሐሳብ፥ የለዘብተኛ ፖለቲከኞች እና የዲፕሎማቶችን-አስተያየት ከሚያጣጥሉት፥ ከምክትል ፕሬዝዳት ዲክ ቼኒ እና ከመከላከያ ሚንስትር ዶናልድ ራምስ ፌልድ ጆሮ ደርሶ «ከሙስሊም አሸባሪዎች ጋር እንደራደር አለ» እያሉ ያሳጡኛል ብለዉ በሚጨነቁበት ወቅት፥ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ከድል-ይልቅ ሽንፈት ያጠላበት የኢራቁ ወረራ፣ ሐገራቸዉን ለዉድቀት፣ሥልጣን ስብእናቸዉን ለዉርደት ከመዳረግ የሚወጡበትን ብልሐት ያብሰለስሉ ነበር።

ሕዳር ነዉ።የጎርጎሮሳዉያኑ ሁለት ሺሕ አምስት ሊጠናቀቅ ሁለት ወር ቀረዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ከቬትናሙ ጦርነት በሕዋላ ከዉርደት አፋፍ ካደረሳት ደም አፋሳሽ እልቂት ፍጅት የምትወጣበትን ብልሐት ባግዳድ-ዋሽንግተን ላይ ስታማትር-የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ተስፋ አዲስ አበባ ላይ በሰዉ ደም ጨቀየ።ከስድስት ወር በፊት ግንቦት ላይ የተደረገዉ ምርጫ ዉጤት ባስከተለዉ ዉዝግብ ግጭት ሁለት መቶ ያሕል ሰዎች ተገደሉ።

የዋነኛዉን የቅንጅት ለአንድነት፥ ለፍትሕና ለዲሞክራሲ መሪዎችን ጨምሮ ስልሳ ሺሕ የተገመተ ሕዝብ ታሰረ።ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ፥ የፍትሕ የመቻቻል ጅምሯን በዜጎችዋ ደም፥ አጥንት፥ በፖለቲከኞችዋ እስራት ከፈነች።

ቡሽ የኻሊልዛድን ሐሳብ ከራይስ እንደሰሙ አዲሱ የCIA ዳይሬክተር ማይክል ሐይዴ ጉዳዩን አስጠንተዉ እንዲያቀርቡላቸዉ አዘዙ።ጥናቱ እንዳበቃ ድርድሩ ቀጠለ።የዓለም አድራጊ ፈጣሪዋ ትልቅ ሐገር ለአራት ዓመታት ደም ከተቃባቻቸዉ፥ «የአናሳዎቹ የሱኒ ሐራጣቃ አሸባሪ» እያለች ከምታወግዛቸዉ ደፈጣ ተዋጊዎች ጋር ትደራደር ገባች።

የቡሽ መስተዳድር አሸባሪ ከሚላቸዉ ቡድናት ጋር መደራደሩ ብዙ ማነጋገር፣ ማጠያየቁ አልቀረም።የአሜሪካ ጦርን ወክለዉ በድርድሩ ይካፈሉ የነበሩት ሌትናንት ጄኔራል ሬይ ኦዲርኖ ግን ተቺ-ጠያቂዎችን እየጠየቁ፥ከምክንያቱ ብዙዉን መለሱት። «የኢራቃዉያን ሞት ሁላችንንም አሳስቦናል።ተሰላችተናልም። የአሜሪካዉያን ሞት ታክቶናል፣ በዚሕ መንገድ እርቀ-ሠላም ማዉረድ ከቻልንና ሠላም ካሰፈንን--- ከዚሕ የተሻለ ምን ጥሩ ነገር አለ?» ብለዉ።

ልዓለ ሐያሊቱ ሐገር የአንሳር አል-ሱና ጦር፣ የ1920 አብዮታዊ ብርጌድ፣ እና የኢራቅ እስላማዊ ጦር ለተሰኙት ደፈጣ ተዋጊ ቡድናት መሪዎች ሹመት፣ ሽልማት፣ ለተዋጊዎቹ ገንዘብና ሥራ፣ ለጎሳ መሪዎችና ለሸምጋዮቹ ገንዘብ ሰጥታ-የጠላቶችዋን ቁጥር ቀነሰች።ከትናንሾቹ ጋር በመደራድሯ ትንሽ መስላ፣ በዉጊያ ከማፈር፣ መዋረድ ዳነች።

ኢትዮጵያዉያን አዲሱን ዓመአት ሊቀበሉ ወር ነበር-የቀራቸዉ።የልዕለ-ሐያሊቱ ሐገር ትልልቅ መሪዎች አሸባባሪ ከሚሏቸዉ ትናንሽ ቡድናት ጋር እንደ«ትንሽ» ተደራድረዉ፥ የየቡድናቱን መሪዎች ሾመዉ-ሸልመዉ፥ ያነሱ መስለዉ-መተለቃቸዉን ሲያስመሰክሩ፥የኢትዮጵያ ትላልቅ መሪዎችም እድሜ ልክ እስራት የተበየነባቸዉን የቅንጅት መሪዎችን በምሕረት መልቀቃቸዉ የዘየዱ መስለዉ ነበር። ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በዚያዉ ሰሞን ያስተላለፉት መልዕክትም መንግሥታቸዉ በአዲሱ ዓመዓት ለአዲስ በጎ ተስፋ መቆሙን ጠቋሚ መስሎ ነበር።

በሁለተኛ ዓመት ከመንፈቁ በተደረገዉ ምርጫ ገዢዉ ፓርቲ በዘጠና-ዘጠኝ ነጥብ ስድስት በመቶ ድል የሐገሪቱን ሥልጣን መቆጣጠሩን ማስታወቁ ነዉ-በአዲሱ ዓመአት ዋዜማ-የመሰለዉ በጎ በመመስል የመቅረቱ ቀቢፀ-ተስፋ።የተገባደደዉ የጎርጎሮሳዉያኑ ሁለት-ሺሕ አስራ-አንድ አሜሪካኖች ከአል-ቃኢዳ ቀጥሎ በአሸባሪነት ከሚወንጅሏቸዉ፥ለአስር ዓመት ከወጓቸዉ ከታሊባኖች ጋር የፕሬዝዳት ካርዛይ መንግሥት እንዲደራደር ግፊታቸዉን ያጠናከሩበት ነዉ።

ቦኮ ሐራም የተሰኘዉ የናጄሪያ አሸባሪ ቡድን ተደጋጋሚ አደጋ የጣለበት ነዉ።ቡድኑ የተቋቋመበትና ተደጋጋሚ አደጋ የጣለባት የቦርኖ አገረ-ገዢ ካሺም ሼቲማ በዚሑ አመት እንዳሉት ግን አስተዳደራቸዉ ከዚያ ቡድን ጋር ለመደራደርን ዝግጁ ነዉ።

ባለፈዉ ሐምሌ የሶማሊያን የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን የያዙት አብዲወሊ መሐመድ ዓሊ እንኳን መንግሥታቸዉ ዓለም በሸባሪነት ከወጀለዉ ከአ-ሸባብ ጋር ለመደራደር እንደሚሻ አስታዉቀዋል። የዋሽንግተን-ካቡሎች፥የአቡጃ-ሞቃዲሾዎች ቃል-ጅምር ገቢር መሆን አለመሆኑ ወይም ዳር መዝለቅ አለመዝለቁ አንድም አጠያያቂ አለያም ወደፊት የሚታይ ጉዳይ ነዉ-የሚሆን።ያሉ-የጀመሩት ግን ቦምብ ጠመንጃ ከታጠቁ፥ ደም ከተቃቡ ጠላቶቻቸዉ ጋር እንደራደራለን ነዉ።

ዓለም በፀረ-ሽብር ወታደራዊ ዘመቻዉ በተሳላቸበት፥ የወታደራዊ ዘመቻዉን ድል በሚያጠራጥርበት ባሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አዲስ የፀረ-ሽብር ሕግ ማፅደቋ ነዉ ግራዉ።በአዲሱ ሕግ ተጠርጥረዉ የታሰሩ፥ የተከሰሱት በሰላማዊ መንገድ እንደሚታገሉ ያስታወቁ ፖለቲካኞች፥ ወይም ወረቀት-እስኪሪብቶ «የታጠቁ» ጋዜጠኞች መሆናቸዉ ነዉ-አሳሳቢዉ ድቀት።የመድረክ መሪ ዶክተር ሞጋ ፈሪሳ እንደሚሉት እርምጃዉ ለቀሩትም ተቃዋሚ ፖለቲከኞች አስጊ ነዉ።

Dr. Negasso Gidada

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአንድነት ሊቀመንበር


ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ግብፅና ቱኒዚያን ለዘመናት የገዙ አምባገነኖች በሕዝባዊ አመፅ ከየሥልጣናቸዉ የተወገዱበት፥ ሊቢያን ከአርባ አንድ አመት በላይ የገዙት ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ በአማፂያን እና በኔቶ ዉጊያ የተሸነፉበት ዓመትም ነዉ።የየመን የሠላሳ ሁለት አመት ገዢ ዓሊ አብደላ ሳሌሕ፥ የሶሪያ የግማሽ ምዓተ-ዓመት ገዢ-የባዓዝ ፓርቲ አገዛዝ በሕዝብ ተቃዉሞ የተንገዳገዱበትም ነዉ።

ባለፈዉ ሳምንት ምክትል መሪዉን አንዱ ዓለም አራጌን ጨምሮ ሰወስት አባላቱ የታሰሩበት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ሊቀመንበር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኞችንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የሚያስረዉ የአረቦች አይነቱ ሕዝባዊ አመፅ ኢትጵያም ይነሳል ብሎ ሥለ ፈራ ነዉ።

የፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል የዶክተር ሞጋን ሥጋትም፥ የዶክተር ነጋሶን ምክንያትም አይቀበሉትም።አለም አቀፉ የሠብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል እንዳስታወቀዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለፈዉ መጋቢት እስካሁን ድረስ አንድ መቶ አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፥ እና የግል ጋዜጠኞች ታስረዋል።በድርጅቱ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ አጥኚ ክሌር ቤስተን እስከመቼ ይላሉ።

«የአሁኑ እስራት በዚሕ አመት ተቃዋሚ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ለማሰር በተከታታይ የሚደረገዉ ዘመቻ አካል ነዉ ብለን ነዉ የምንቆጥረዉ።በእኔ ስሌት መሠረት ካለፈዉ መጋቢት ጀምሮ አንድ መቶ አንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና አምስት ጋዜጠኞች ታስረዋል።እኔ የኢትዮጵያ መንግሥትን የምጠይቀዉ ይሕ እርምጃ መቼ ነዉ የሚቆመዉ እያልኩ ነዉ።የተቃዉሞ ድምፅ የሚያሰሙ በሙሉ እስኪታሰሩ ድረስ ይቀጥል ይሆን?»

የመንግሥት ባለሥልጣናት መልስ እንዲሰጡን ካለፈዉ ሐሙስ ጀምረን በተደጋጋሚ ሞክረን ነበር።አልተሰካልንም።

የቅንጅት መሪዎች ከተፈቱ ወዲሕ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን እና የፖለቲከኛ ብርቱካን ሚዴቅሳ መታሰር ብዙ አነጋግሯል።አሁንም እንደገና ከጋዘጠኛ ዉብሸት ታዬ እስከ ርዕዮት ዓለሙ፥ ከስለሺ ሐጎስ እስከ እስክንድር ነጋ፥ ከመምሕር በቀለ ገርባ እስከ ከያኒ ደበበ እሸቱ፥ ከፖለቲከኛ ኦልባና ሌሌሳ እስከ አንዱ ዓለም አራጌ እና የሌሎች ብዙዎች መታሰር እንደገና ያነጋግራል።ግን ለምን?ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላAudios and videos on the topic