የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ ገብቶ ነበር መባሉ | ኢትዮጵያ | DW | 19.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ ገብቶ ነበር መባሉ

የኢትዮጵያ ጦር በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ከአሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን የእስልምና ሃይማኖት መምህር ፍለጋ ወደ ሰሜን ሶማሊያ ገብቶ እንደ ነበር ተሰማ። ጦሩ ከገባበት አካባቢ ወዲያው ለቆ መውጣቱ ተዘግቧል።


መጋቢት 8/2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ወታደሮች የሶማሊያን ድንበር ተሻግረው በፑንትላንድ ግዛት ጋራዌ ወደ ተባለች ከተማ ገብተው እንደነበር ተሰምቷል። ወታደሮቹ በቡሆድሌ ከተማ የሚገኙ ከአሸባብ ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ መምህር ፍለጋ ድንበር ማቋረጣቸውን በሶማሊያ የዶይቼ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ መሐመድ ኡመር ይናገራል።
«ሁኔታው የተፈጠረው ማክሰኞ ጠዋት ነበር። የኢትዮጵያ ወታደሮች በከተማዋ የሚገኙ የቁርዓን መምህር ከአሸባብ ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጃ ደርሶናል በማለት ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተናግረዋል። መምህሩ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት በማቀነባበር ላይ ነበሩ ብለዋል።»


ከአሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው ጥቃት ለመፈጸምም እያቀዱ ነበር የተባሉት መምህር የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበር መሻገራቸውን መረጃ ደርሷቸው ከአካባቢው መሰወራቸውን መሐመድ ኡመር ተናግሯል። በወቅቱ በአንዲት ሴት ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን የኢትዮጵያ ወታደሮች ወዲያው አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውን መሐመድ ይናገራል።
«ከተልዕኮው በኋላ ወዲያውኑ ወታደሮቹ የቡሆድሌ ከተማን ለቀው ወጥተዋል። የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ በተጨማሪ በህገ-ወጥ መንገድ በሶማሊያ የተለያዩ ከተሞች ይገኛሉ። ወታደሮቹ የሚገኙት በሁለቱ ሃገሮች የድንበር አካባቢዎች ነው። ለምን ተብለው ሲጠየቁ የሃገራቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ እና ወደ ኢትዮጵያ ለመሻገር የሚሞክሩ የአሸባብ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር እንደሆነ ይናገራሉ።»
የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም። በ1999 ዓ.ም የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት ተብሎ የሚጠራው የጊዜው አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር መዛቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ማዝመቷ አይዘነጋም። ከአንድ አመት በላይ በሶማሊያ በቆየው ዘመቻ በስልጣን ላይ የነበረው እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ቢሸነፍም የኢትዮጵያ ጦር ቆይታ መራዘም በሃገሪቱ ዜጎች ዘንድ የተከፋፈለ ስሜት መፍጠሩ አይዘነጋም። አሸባብ ሶማሊያን ከተቆጣጠረ እና በቀጣናው ላይ ስጋት ከፈጠረ በኃላም በታጣቂ ቡድኑ ላይ በተወሰዱ ተልዕኮዎች የኢትዮጵያ ጦር ከፍተኛ ሚና ነበረው።
እሸቴ በቀለ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic