የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር እና የወጣቶች አስተያየት | ባህል | DW | 23.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር እና የወጣቶች አስተያየት

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ንግግራቸው በማህበራዊ ድረ-ገፆች አጠቃቀም ላይ የሰጡት አስተያየት አከራካሪ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:22

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር እና የወጣቶች አስተያየት

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 71ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የታደሙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ባደረጉት ንግግር ካነሷቸው ርዕሰ-ጉዳዮች መካከል የማሕበራዊ ድረ-ገፆች አጠቃቀም አንዱ ነበር። አቶ ሐይለማርያም በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚሰራጭ መረጃ በቀላሉ እንዴት እንደሚዛመት እና ሰዎችን በተለይም ወጣቶችን እንደሚያሳስት እየታዘብን ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች እውነተኛ ጥያቄ ያላቸው ሰዎችን ለፅንፈኞች መጠቀሚያ እያደረገ ነው። ጥላቻን ለማስፋፋት እየተጠቀሙበትም ነው ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ለጦማሪው አጥናፍ ብርሐኔ ያለው ትርጉም ሌላ ነው።
ፍጹም ብርሐኔ የኮምፒውተር ሳይንስ ባለሙያ ነው። ወጣቱ እንደ አጥናፍ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተከታትሏል። ፍጹም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጊዜውን የጠበቀ ሆኖ አግኝቶታል።
እጅግ ውስን የኢንተርኔት አገልግሎት ያላት ኢትዮጵያን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀምን ከጥላቻ ጋር አሰናስለው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ማንሳታቸው አከራካሪ ይመስላል። የአዲስ አበባ እና ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በጋራ ከወራት በፊት ይፋ ያደረጉት የሁለት አመት ጥናት ውጤት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ ፉርሽ የሚያደርግ ድምዳሜ አስነብቦ ነበር። በፌስቡክ ላይ ትኩረት ባደረገው ጥናት መሠረት ጥላቻና አደገኛ ንግግር ያዘሉ የማህበራዊ ድረ-ገጾች መልዕክቶች መጠን እንደሚታሰበው ብዙ አይደሉም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ ነበር። የመቻቻል ጥናት ከሰበሰባቸው የናሙና አስተያየቶች መካከል 0.4%ብቻ የጥላቻ ንግግር ተብለው ተፈርጀዋል። እነዚህ ሌሎችን ጎሳቸውን፤ሐይማኖታቸውን እና ጾታቸውን መሰረት በማድረግ ግለሰቦች እንዲገለሉ የሚቀሰቅሱ መሆናቸውን ጥናቱ አትቷል። ከጥናቱ ናሙናዎች 0.3%ደግሞ በአንድ ቡድን ላይ ሰፊ ኹከት ለመቀስቀስ ጥሪ የሚያቀርቡ አደገኛ ንግግሮች ተብለዋል። ፍጹም በኢትዮጵያ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ውስን ቢሆንም በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የማህበራዊ ድረ-ገፆች ሚና ከፍ ያለ ሚና እንዳላቸው ያምናል።
አጥናፍ ብርሐኔ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ድረ-ገፆች ተጠቃሚዎች ጥላቻን ከማስፋፋት ይልቅ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለማጋለጥ እየተጠቀሙበት ነው ብሎ ያምናል። የመገናኛ ብዙኃን መታፈን እና ወጣቶችን ወደ ማሕበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚነት መርቷቸዋል ሲልም ይከራከራል።
የጥላቻ ንግግር ሁሉንም የሚያስማማ ቁርጥ ያለ ትርጓሜ የለውም። የጥላቻ ንግግር ተብሎ የሚፈረጀው የትኛው ነው የሚለው ክርክር አሁንም መቋጫ አላበጀም። ጥላቻ የሚሰብኩ ኹከት የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች እንዲሁ አወዛጋቢ ናቸው። በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲህ አይነት የእቀባ እርምጃዎች ሐሳብን በነፃነት ከመግለፅ ነፃነት ጋር ይቃረናሉ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። የጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም ደሳለኝ የኒውዮርክ ንግግር መንግስታቸው ወደ ፊት ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ጠቋሚ ናቸው ብለው የሚከራከሩም አልጠፉም። ፍፁም ግን በፍጹም ይላል።
በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የማሕበራዊ ድረገፆችን ሚና ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። ክርክር፤ውይይት ጦፏል። የተቃውሞ ሰልፍ እና የአድማ ጥሪ በፌስቡክ አደባባይ ይጠራል። የፀጥታ ኃይሎች እርምጃዎችን የሚያጋልጡ ምስሎችም ይበተናል። መንግስት ተቃውሞዎቹ ሞቅ ሲሉ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥ የመረጃ ልውውጡን ለመግታት ይሞክራል። ይህንን አጥናፍ ብርሐኔም ታዝቦታል።
እሸቴ በቀለ
ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic