የኢትዮጵያ ግድብና የሰወስትዮሹ ድርድር | አፍሪቃ | DW | 27.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

የኢትዮጵያ ግድብና የሰወስትዮሹ ድርድር

የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ግን ያሁኑ ስብሰባ እንደተባለዉ ከወሳኝ መፍትሔ ባይደርስ እንኳ ሰወሥቱ ሐገራት በተለይ ኢትዮጵያና ግብፅ ጦር የያሰብቅ መሠሎ የበረዉ ዉዝግባቸዉን በድርድር ለመፍታት መስማማታቸዉ ራሱ ጥሩ ጅምር ነዉ።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምታስገነባዉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ሐይል ማመንጫ ግድብ የቀሰቀሰዉን ዉዝግብ ለማስወገድ ኢትዮጵያ፤ሱዳንንና ግብፅ የሚያደርጉትን ድርድር እንዳዲስ ጀምረዋል።የሰወስቱ ሐገራት ሚንስትሮች ከዚሕ ቀደም ጀምረዉት ከነበረዉ ድርድር ግብፅ በመዉጣትዋ ድርድሩ ለበርካታ ወራት ተቋርጦ ነበር።የግብፅና የኢትዮጵያ መሪዎች ባለፈዉ ሐምሌ ማላቦ-ኢኳቶሪያል ጊኒ ዉስጥ ባደረጉት ወይይት ድርድሩ እንዲቀጥል በመስማማታቸዉ የሰወስቱ ሐገራት ሚንስትሮች ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ ካርቱም-ሱዳን ዉስጥ ተወያይተዋል።

ከዚሕ ቀደም ድርድሩን አቋርጣ የነበረችዉ ግብፅ፤ የሐገሪቱ የዉሐና የመስኖ ጉዳይ ሚንስትር-ሑሴይን መሐመድ አል-ሙጋዚ-ባለፈዉ ሰኞ እንዳሉት አሁንም ወደ ግብፅ የሚወርደዉ የዉሐ መጠን መቀነስ የለበትም ከሚለዉ ከወትሮ አቋሟ ፈቅ ያለች አትመስልም።«በድርደሩ» አሉ ሚንስትሩ-ለጋዜጠኞች-«የግብፅ ልዩ ሥፍራ ከግምት ይገባል ብዬ እጠብቃለሁ፤ ምክንያቱም ቀጠሉ ሚንስሩ ግብፅ ሙሉ በሙሉ የአባይ (የናይል) ዉሕ ጥገኛ ናት እና።»

ግብፅ ከዚሕ ቀደም እንደምትለዉ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ግብፅ የበላይ ጠባቂ ብሪታንያ እና በሱዳን ቅኝ ገዢ ብሪታንያ መካከል የተደረጉ ዉሎች መሻር፤መነካት፤ መተካት የለባቸዉም የሚል አቋሟን ግን ባለስልጣናቷ ቢያንስ በይፋ ከመናገር ቆጠብ ብለዋል።ኢትዮጵያዊዉ የአፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ካይሮዎች ያን ያክል ጅል አይደሉም።ያረጀ መከራከሪያቸዉን ዳግም ቢያነሱ-ሰሚ እንደማያገኙ ያዉቁታል።

ካርቱም ላይ እንደ አዲስ የተጀመረዉ ድርድር ሒደትና ዉጤት እስካሁን በግልፅ አልተነገረም።የድርድሩ ተሳታፊ እና አስተናጋጅ የሱዳኑ የዉሐ ሐብትና የኤሌክትሪክ ሚንስትር ሙታዝ ሙሳ አብደላሕ ሳሊም እንዳሉት ግን የሚንስትሮቹ ስብሰባ ለዉዝግቡ መፍትሔ ለመሻት ወሳኝ ነዉ።

ወሳኙ ስብሰባ በኢትዮጵያ በኩል ያለዉን ተቀባይነት ለማረጋገጥ በሥብሰባዉ የሚካፈሉትን የኢትዮጵያ የዉሐ፤ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስቴር ባለሥልጣናትን በሥልክ ለማነጋገር ያደረግነዉ ሙከራ አልተሳካልንም።

የፖለቲካ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት ግን ያሁኑ ስብሰባ እንደተባለዉ ከወሳኝ መፍትሔ ባይደርስ እንኳ ሰወሥቱ ሐገራት በተለይ ኢትዮጵያና ግብፅ ጦር የያሰብቅ መሠሎ የበረዉ ዉዝግባቸዉን በድርድር ለመፍታት መስማማታቸዉ ራሱ ጥሩ ጅምር ነዉ።ግብፅ እና ኢትዮጵያ በዉሐ አጠቃቀም ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጉዳዮች ተባብረዉ እና ተግባብተዉ ካልሰሩ-አቶ ዩሱፍ እንደሚመክሩት ጠብ፤ቁርቁሳቸዉ ለአካባቢዉም የሚተርፍ ነዉ የሚሆነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic