የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እስር እና «ሲ ፒ ጄይ» | ኢትዮጵያ | DW | 18.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እስር እና «ሲ ፒ ጄይ»

ኢትዮጵያ ውስጥ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የአምደ መረብ ጸሓፍት ቁጥር ከአምናው በእጥፍ ማደጉን CPJ በሚል ምኅፃረ-ቃል የሚጠራዉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ገለጠ። የCPJ የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስ ኢትዮጵያ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ምርጫው ከመድረሱ አስቀድሞ ተቺዎች ድምፃቸው እንዳይሰማ እያፈናቸው መሆኑን ተናግረዋል።

CPJ በተገባደደው የጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓም በዓለም ዙሪያ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና የአምደመረብ ጸሓፍትን የተመለከተ ዓመታዊ የእስረኞች ዝርዝርን ይፋ አደረገ። እንደ CPJ ዘገባ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከዓለማችን ጨቋኝ መንግሥታት መኻከል ዋነኛዋ ነች። የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ ረቡዕ ታኅሣሥ 8 ቀን፣ 2007 ዓም ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ ወህኒ በተወረወሩ ጋዜጠኞች ብዛት ኢትዮጵያን ከአፍሪቃ ኹለተኛ አድርጓታል፤ ከዓለማችን ደግሞ አራተኛ ናት ብሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዓመት የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር 17 መድረሱን ድርጅቱ ተናግሯል። የCPJ የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስ።

የCPJ የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮሕዴስ

የCPJ የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስ

«በአሁኑ ወቅት 17 ጋዜጠኞች እስር ቤት ይገኛሉ። ፕሬስን የመደፍለቅ ከፍተኛ ዘመቻ ከተከፈተበት ከ1997ቱ ድኅረ-ምርጫ ወዲህ የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር መሆኑ ነው»።

ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያን በአፍሪቃ የምትቀድማት ኤርትራ ብቻ እንደሆነች ተገልጧል። ኤርታራ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 23 ጋዜጠኞች ወህኒ ይገኛሉ ተብሏል። ምናልባትም ቁጥሩ በኤርትራ ከፍ ሊል አለያም በሞት የተነሳ ሊቀንስ እንደሚችል፣ CPJ ጠቅሷል። ሆኖም ሙሉ መረጃ ከኤርትራ ማግኘት እንዳልቻለ ተናግሯል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከአዲስ አበባ ውጪ እንደ ዝዋይ ባሉ አደገኛ እስር ቤቶች ቢያንስ 2 ጋዜጠኞች ተወስደው እንግልት ደርሶባቸዋል ሲል CPJ ይፋ አድርጓል። ይኽ እንግልት እና ስቃይ በቃሊቲም እንደሚፈፀም የCPJው ተጠሪ ቶም ሮድስ ተናግረዋል።

«በርካታ የፖለቲካ እስረኞች በሚገኙበት የቃሊቲ እስር ቤትም ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። የሥራ ባልደረቦቻችን እንደነገሩን ከሆነ፦ በእስር ቤት ሳሉ፤ ይገረፉ፣ ጥፋተኞች ነን ብለው እንዲናገሩ ይገደዱ፣ ቤተስብ እንዳያያቸውም ክልከላ ይደረግባቸው ነበር። ሌላም ሌላም።»

ዘንድሮ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ቻይና ከዓለማችን ቀዳሚ ሆናለች ተብሏል። በቻይና 44 ጋዜጠኞች እስር ቤት እንደሚገኙ ተጠቅሷል። ኢራን 30 ጋዜጠኞችን እስር ቤት በመወርወር ከዓለም ኹለተኛ ሆናለች። ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ኢራንን ይከተላሉ። ከኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ብቻ ቁጥራቸው ከ30 በላይ ጋዜጠኞች ከገዢው ፓርቲ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመፍራት ተሰደዋል ሲል CPJአስታውቋል። ጋዜጠኞችን እና የአምደ መረብ ጸሓፍትን በሽብርተኝነት ስም ማዋከቡ ቀጥሏል ብሏል ለጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቱ።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዓርማ CPJ

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ዓርማ CPJ

«በኢትዮጵያ በ2004 ዓም የታሰሩ ጋዜጠኞችን ቅጽ ብትመለከት፤ በተጨማሪም በተለይ በዚህ ዓመት ሚያዝያ ላይ የታሰሩት ዞን 9 የተባሉትን ወጣት ባለሙያ አምደመረበኞች ክስ ብትቃኝ አንዳችም የአሸባሪነት እንቅስቃሴ አታይባቸውም። ሌላው ቀርቶ ከተቃዋሚ ፓርቲ ጋር እንኳ የሚያገናኛቸው ነገር የለም።»

ይልቁንስ በኢትዮጵያ ገዢው ፓርቲ የ2007 ዓም ሀገር አቀፍ ምርጫ ከመድረሱ አስቀድሞ ያለምንም ችግር አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ሥራውን እየሠራ ነው ሲሉ ቶም ሮድስ ተናግረዋል። ገዢው ፓርቲ እንቅፋት የመሰሉትን በሙሉ በእስር እና በስደት ገለል እያደረገ መሆኑንም CPJ አስገንዝቧል።

ዘንድሮ በዓለማችን 220 ጋዜጠኞች እስር ቤት እንደሚገኙ ይኽም ቁጥር ካለፈው የጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም በ9 እንደጨመረ CPJ ጠቅሷል። ከ14 ዓመት ወዲህም ከፍተኛው ቁጥር ሆኖ መመዝገቡ ይፋ ሆኗል። ቁጥሩንም ከፍ ያደረጉት እንደ ቻይና፣ ኢትዮጵያ፣ በርማ እና ግብፅ ያሉ አምባገነን መንግሥታት ናቸው ሲል ለጋዜጠኞችመብት የሚከራከረው ድርጅት CPJ ተናግሯል። የCPJን ዘገባ ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚመለከታቸውን የተለያዩ የመንግሥት አካላት ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic