የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መሰደድና «ሲ ፒ ጄይ» | ኢትዮጵያ | DW | 31.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መሰደድና «ሲ ፒ ጄይ»

ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ የሚሰደደዉ ጋዜጠኛ ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት «CPJ» ገለፀ። እንደ ድርጅቱ ዘገባ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረዉን የእስራት ዘመቻ በመፍራት ባለፉት 12 ወራቶች ብቻ ከኢትዮጵያ ከሰላሳ በላይ ጋዜጠኞች ተሰደዋል።

የ « CPJ» መግለጫን በተመለከተ የድርጅቱን የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስን አነጋግረናል።

ዛሬ በሚደመደመዉ የጎርጎሪዮሳዊ 2014 ዓ,ም ከኢትዮጵያ የተሰደደዉ የጋዜጠኛ ቁጥር በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 እና 2013 ዓ,ም በድምር ከኢትዮጵያ ከተሰደደዉ የጋዜጠኛ ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት « CPJ» ይፋ ባደረገዉ ዘገባ ገልፆአል።

ድርጅቱ ባወጣዉ መግለጫ በያዝነዉ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመት «በሕገ መንግሥቱ እና በስርዓቱ ላይ ያነጣጠረ የአመፅ ጥሪ ለመፈፀም በሕቡዕ ተደራጅተዉ ተንቀሳቅሰዋል» በሚል ክስ ዞን ዘጠኝ በሚል መጠርያ የሚታወቁት ስድስት የድረ ገጽ ጦማርያንና ሶስት ጋዜጠኞች ታስረዋል። በመንግሥት ስር በሚገኘዉ የኦሮሚያ ራድዮና ቴሌቭዥን ይሰሩ የነበሩ 20 ጋዜጠኞች ያለምንም ምክንያት ከሥራቸዉ ተባረዋል። በዚሁ የጎርጎሪዮሳዊ ዓመትም ስድስት ጋዜጦች «የተሳሳተ መረጃን በማሰራጨት ፤ ግጭት በማነሳሳትና የመንግሥትን የመረጃ ስርጭት ህግን ከቁጥር ባለማስገባት፤ እንዲሁም የተሳሳተ መረጃን በማሰራጨት» በሚል ክስ የሶስቱ ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች የሶስት ዓመት ፅኑ እስራት እንደተፈረደባቸዉና የቀድሞ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ እንዲሁ «ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳትና ሀሰተኛ መረጃን በማቀበል» በሚል ተከሶ የሶስት ዓመት ፅኑ እስራት እንደተበየነበት ያትታል። ይህን በጋዜጠኞች ላይ የተጀመረዉን ዘመቻ በመፍራትም ዛሬ በሚጠናቀቀዉ የአዉሮጳዉያኑ 2014 ዓመት ብቻ በርካታ ኢትዮጵያዉያን ጋዜጠኞች መሰደዳቸዉን የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስ ገልፀዋል፤

« አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ወደ እዚህ ወደ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ነዉ የተሰደዱት፤ ወደ ዩጋንዳ መዲና ካንፓላም የተሰደዱ ሌሎች ጋዜጠኞችም አሉ። በአንድ ዓመት ግዜ ዉስጥ እንዲህ ያህል በርካታ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ እስከዛሬ አላየንም። በዚህ ዓመት ከኢትዮጵያ የተሰደዱት ጋዜጠኞች ቁጥር ወደ 30 ደርሶአል። ሁሉም ጋዜጠኞች ሃገራቸዉን ጥለዉ የወጡት ደግሞ ክሱን በመፍራት ነዉ።»

ቶም ሮድስ እንደገለጹት አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ወደፊት ስለሚጠብቃቸዉ ሁኔታ ምንም ዓይነት እዉቀት ሳይኖራቸዉ ወደ ኬንያ ገብተዉ በመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን « UNHCR» ቢሮ በስደተኝነት ይመዘገባሉ። እንዲያም ሆኖ ጋዜጠኞቹ አስተማማኝ ባልሆነ ሁኔታ ኑሮአቸዉን እንደሚገፉ ነዉ ኬንያ የሚገኙት የCPJ የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስ የገለፁት።

«እንዳለመታደል ሆኖ ጋዜጠኞቹ በተሰደዱበት ያን ያህል አስተማማኝ ሁኔታ የለም። አንዱ ምክንያት የኬንያ መንግሥት በተለይም ደግሞ የኬንያ የፀጥታ ኃይል በፀረ-ሽብር ዘመቻዉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እጅግ በቅርበት መሥራታቸዉ ነዉ። ታድያ አንዳንዴ ይህ ስልት ከሚገባዉ አልፎ ለሌላ ጥቅም ይዉላል። እዚህ ያሉ ባለስልጣናት ጋዜጠኞችን እንዲይዙ ይከፈላቸዋል፤ አልያም በማግባባት ጋዜጠኞችን አሳደዉ እንዲይዙ ይደረጋል። በዚህም ምክንያት ለምሳሌ እዚህ ናይሮቢ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያዉያን ጋዜጠኞች በነዚህ ኃይላት ከሚደርስባቸዉ ወከባ ለመሸሽ እና ተይዘዉም ወደኢትዮጵያ በግዳጅ እንዳይመለሱ በመፍራት አብዛኛዉን ጊዜ ከተጠለሉበት ቤት ሳይወጡ ተደብቀዉ ይኖራሉ።»

ከኢትዮጵያ የተሰደዱ ጋዜጠኞች በአብዛኛዉ ናይሮቢ ኬንያ ከዝያም ካንፓላ ዩጋንዳ እንዲሁም ጥቂት ሱዳን ዉስጥ እንደሚኖሩ የገለፁት ቶም ሮድስ፤ ጋዜጠኞቹ እጅግ በችግር ሕይወታቸዉን እንደሚገፉም ሳይገልፁ አላለፉም።

«እንደስደተኝነት ኬንያ ዉስጥ የሥራ ፈቃድ ለማግኘት እጅግ ፈታኝ ነዉ። አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ስማቸዉ እንዳይታወቅ ራሳቸዉን ዝቅ አድርገዉ መኖር ነዉ የሚመርጡት። ስለዚህ በተለይ በሀገራቸዉ ጥሩ ገቢ እያገኙ ለኖሩት ጋዜጠኞች ምሥራቅ አፍሪቃ ዉስጥ ሥራ የማግኘቱ ዕድል እጅግ ከባድ ነዉ። እንደ CPJ የመሳሰሉ ድርጅቶች እነሱን በተወሰነ ደረጃ ለመርዳት እየሞከሩ ነዉ። ቢሆንም ግን ድጋፉ እጅግ እጅግ ዉሱን ነዉ።»

Symbolbild Menschenrechte Unrecht Unterdrückung

በርካታ የግል ዘጋቢዎችና ጋዜጠኞች ከኢትዮጵያ መሰደዳቸዉ ልምድ እየሆነ መምጣቱ በሃገሪቱ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እየተዳፈነ መምጣቱን አመላካች ነዉ ያሉት ቶም ሮድስ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2014 ዓመት በርካታ ጋዜጠኞች መታሰራቸዉንም ገልፀዋል።

« በ2014 ዓ,ም በርካታ ኢትዮጵያዉያን ጋዜጠኞች መሰደድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጋዜጠኞችም ታስረዋል። በአሁኑ ወቅት ወደ 17 የሚሆኑ ጋዜጠኞች እስር ቤት ናቸዉ። ይህ ቁጥር ደግሞ አፍሪቃ ዉስጥ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛዋ ሃገር መሆንዋን አሳይቶአል። ይህ ጋዜጠኞችን የማሰር አልያም የማሰደዱ ሁኔታ በጣም እየተለመደ የመጣና አሳሳቢ ጉዳይ ሆንዋል።»

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ ድርጅት «CPJ» ዛሬ በሚጠናቀቀዉ የጎርጎሪዮሳዊ 2014 ዓመት በዓለም ዙሪያ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ጦማርያንን የተመለከተ ዓመታዊ የእስረኞች ዝርዝርን ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ምርጫው ከመድረሱ አስቀድሞ ተቺዎች ድምፃቸው እንዳይሰማ እያፈናቸው መሆኑንም አስታዉቋል።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic