የኢትዮጵያ የጉንዳን ሠራዊት የዓለም ሥጋት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 07.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የኢትዮጵያ የጉንዳን ሠራዊት የዓለም ሥጋት

በአካላዊ አወቃቀሩ እና ፈጣን ሥርጭቱ ልዩ የሆነ የጉንዳን ሠራዊት ከኢትዮጵያ ተነስቶ ለዓለም ስጋት ሊሆን ይችላል የሚል ዘገባ ሰሞኑ በወጣ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ተገልጧል። የጉንዳር ሠራዊቱ ከባሕር ዳር አንስቶ እስከ ደብረታቦር ድረስ በአፈር ቅጠሉ ይርመሰመሳል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:58
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:58 ደቂቃ

አደገኛ የጉንዳን ሠራዊት በኢትዮጵያ

በሳይንሳዊ መጠሪያው ሌፒዚዮታ ካንሴንስ (Lepisiota canescens) ይሰኛል። በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል ከባሕር ዳር አንስቶ እስከ ደብረታቦር ድረስ በአፈር ቅጠሉ ይርመሰመሳል። በአይነቱ፣ በብዛቱ እና በአካላዊ መዋቅሩ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ሌሎች ዝርያዎች ለየት ያለ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው ተብሎለታል። ተመራማሪዎች  ይኽ የጉንዳን ሠራዊት ከአንዱ ግዛት ወደ ሌላኛው የጉንዳኖች ግዛት ያለ እክል መሰራጨት በመቻሉ መጠነ-ሰፊ የጉንዳን ሠራዊት ግዛት(supercolony) ሲሉ ሰይመውታል። በአንዳች አጋጣሚ ጉንዳኑ ከኢትዮጵያ ውጪ መሻገር ከቻለ ዓለምን በፍጥነት የማዳረስ አቅሙ ጠንካራ እንደሆነ ተመራማሪዎች ስጋታቸውን ገልጠዋል።

ለወትሮው አንድ ጉንዳን ከግዛቱ አልፎ የሌላ ጉንዳን ግዛት ውስጥ መኖር አይችልም። ያ ግዛቱም በአራት ኪሎ ሜትሮች ግፋ ቢልም በአምስት የተወሰነ ነው። መንገድ ስቶ ወይ ደግሞ ንፋስ አንገዋሎት የሌሎች ጉንዳኖች ግዛት የደረሰ ከልታዋ ጉንዳን ግዛቴ ብለው ከሚርመሰመሱ ጉንዳኖች መልካም ነገር አይጠብቀውም። ያለማወላወል በግዛቱ ነዋሪ ጉንዳኖች ይገደላል።  መጠነ-ሰፊ የጉንዳን ሠራዊት ግዛት የሚል ስያሜ ያገኙት ጉንዳኖችን ግን ከግዛት ግዛት ለመንሸራሸር የሚያግዳቸው የለም።  

«ጉንዳኖች ማኅበራዊ እንስሳት ናቸው። በቡድን በቡድን ነው የሚኖሩት። በአንዲት ንግሥት የሚመራ አንድ ቡድን እንደ ሁኔታው ከአራት ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ጉንዳኖች ሲኖሩት የሚኖረውም በአንድ አካባቢ ነው። ሌላ የጉንዳን ሠራዊት ደግሞ በዛው መጠን ሌላ ቦታ ይኖራል። አሁን ያገኘነው የጉንዳን አይነት የሚኖረው ከባሕርዳር ከተማ ወጣ ብሎ ከሚገኝ አንድ ቤተ-ክርስቲያን ደን ጀምሮ  ደብረታቦር እስከሚባለው ከተማ ድረስ ነው። የጉንዳኖቹ ቡድኖች በአንድ እዝ ስር የሚመሩ መጠነ-ሰፊ የጉንዳን ሠራዊት ግዛት የመሰረቱ ናቸው። ይኽ በጉንዳን ብዙ አልተለመደም። በተለይ ደግሞ ይኼ እኛ የምናጠናው  ሌፒዚዮታ ካንሴንስ የተባለው የጉንዳን ዝርያ በባሕሪው አደገኛ እና ወራሪ ነው።»

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር አለማየሁ ዋሴ  ይኽ በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ክፍል ተገኘ የተባለው የጉንዳን ዝርያ ብዝኃ ሕይወት ላይ አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።

ዶክተር ማግደሌና ሶርገር ከዶክተር አለማየሁ ጋር በመሆን በአካባቢው ብዝኃ ሕይወት ላይ ዘርፈ-ብዙ ጥናት ከሚያከናውኑ አምስት ተመራማሪዎች መካከል አንዷ ናቸው። ዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ቤተ-መዘክር ውስጥም ምርምር ያከናውናሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኙት ጉንዳኖች ሰዎች ላይ በቀጥታ ጉዳት የሚያደርሱ ባይሆኑም ለብዝኃ ሕይወት ግን ጠንቅ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

«ለሰው ልጆች አደገኛ አይደሉም። ግን  ችግሩ ጉንዳኖቹ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ብዝኃ ሕይወት ላይ ጣጣ ማስከተላቸው ነው። ለምሳሌ ጉንዳኖቹ ወደ ሚገኙባቸው አንድ ቤተ-ክርስቲያን ደን ስናቀና ያገኘነው የነዚህ ጉንዳኖችን ዝርያዎች ብቻ ነው። ሌላ የጉንዳን ዝርያ ፈጽሞ የለም ማለት ይቻላል። ያ የሆነው ደግሞ በነዚህ ጉንዳኖች የተነሳ ሊሆን ይችላል።  ምክንያቱም በጣም አደገኛ እና ጠበኛ በመሆናቸው ሌሎች የጉንዳን ዝርያዎችን በቀላሉ አጥፍተዋቸዋል። ችግሩ ይኼ ነው። ወደ ሌላው የዓለም ክፍል መሠራጨት ከቻሉ ሌሎች  ነባር የጉንዳን ዝርያዎችን ሊያጠፉ ይችላሉ።»

ስለ እነዚህ ጉንዳኖች ምንነት እና ግኝት ሰሞኑን በዓለም ዙሪያ ይፋ ቢደረግም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኙት ግን ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት መሆኑን  ዶክተር አለማየሁ ዋሴ  ተናግረዋል።  እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ግኝቱ በቤተ-ሙከራ ምርምር እየተደረገበት መቆየቱንም አክለዋል። ዶክተር ማግደሌና ሶርገር ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኙት አደገኛ ጉንዳኖች ዝርያ ከሌሎች የጉንዳን ዝርያዎች የሚለዩባቸውን ነጥቦች ያብራራሉ።

«ጉንዳኖችን በአጠቃላይ ስናጠና የምንመለከተው አንዱ ነገር አራት የአካል ክፍሎች ያላቸው መሆኑን ነው። ራስ አላቸው። ደረት እና የሆድ ክፍል አላቸው። በሆድ ክፍሉ እና በደረቱ መካከል አነስ ያለ ማገናኛ ጉበን አላቸው። ይህ ማገናኛ አካል ከጉንዳን ጉንዳን የተለያየ ነው። ከጉንዳን ውጪ ሌላ አይነት ነፍሳት እንዲህ አይነት አካላዊ መዋቅር የለውም። ኢትዮጵያ ያገኘነው የጉንዳን ዝርያ ደረት እና ሆድ ማገናኛ ክፍሉ አንድ ነው። የሌሎች ዝርያዎች ማገናኛ ሁለት ነው።»

የጉንዳን  ዝርያዎች በአጠቃላይ አራት ግዙፍ ቤተሰብ እንዳላቸው የተናገሩት ዶክተር ማግደሌና ሶርገር ባሕር ዳር አካባቢ የተገኙት ጉንዳኖች ከግዙፍ ቤተሰቦቹ አንደኛው ውስጥ የሚመደቡ ናቸው ብለዋል። እነዚህ ጉንዳኖች ከሌሎቹ የጉንዳን አይነቶች የሚለዩትም ጠላታቸውን የሚያጠቁበት ከበስተኋላቸው የሾለ መንደፊያ የሌላቸው በመሆኑ ነው። እንደ ዶክተር ማግደሌና ማብራሪያ ይልቁንስ ጉንዳኖቹ ከበስተኋላቸው አሲድ የሚረጩበት አነስተኛ  አካል ያላቸው ናቸው።  የሾለ መንደፊያ ግን የላቸውም። ሌሎች ጉንዳኖችን እየጨረሱ በፍጥነት የሚሰራጩት እነዚህ ጉንዳኖች እንዳይስፋፉ ለማድረግ ጥናት እየተከናወነ መሆኑንም ዶክተር ማግደሌና ሶርገር ተናግረዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic