የኢትዮጵያ የደረቅ ጭነት ማጓጓዝ ሥራ ተቀዛቅዟል | ኤኮኖሚ | DW | 14.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ የደረቅ ጭነት ማጓጓዝ ሥራ ተቀዛቅዟል

ባለፉት ስድስት ወራት ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት ማጓጓዝ ስራው እጅግ ተቀዛቅዟል። በሥራው ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎች እና የከባድ ተሽከርካሪ ባለቤቶች እንደሚሉት መኪኖቻቸው ወደ ጅቡቲ ተጉዘው ከ15 እስከ 20 ቀናት ለመጠበቅ ተገደዋል። የውጭ ምንዛሪ እጥረት የፈጠረው የገቢ ንግድ መቀዛቀዝ ዋንኛው ምክንያት ነው ተብሏል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:26

ተሽከርካሪዎች ከ15-20 ቀናት ጅቡቲ ይቆያሉ

እቃ ጫኝ ከባድ መኪኖች ቢያንስ በወር አራት ጊዜ ወደ ጅቡቲ ያደርጉት የነበረው ምልልስ ቀንሷል። "ሥራ አሁን ሞቷል። ምንም አይነት ሥራ የለንም" ይላሉ አንድ 400 ኩንታል የሚጭን ከባድ መኪና ባለቤት። የደረቅ ጭነት ማጓጓዝ ሥራ ላይ የተሰማሩት እኚህ አሽከርካሪ ሥራ ከተቀዛቀዘባቸው መካከል ናቸው። በወር ከ4-6 ጊዜ ደረቅ ጭነት ለማጓዝ ወደ ጅቡቲ ይመላለሱ እንደነበር የነበሩትት አሽከርካሪ አሁን ወደ 2 እንደቀነሰ ይናገራሉ። ሥራቸውን ፈታኝ የሚያደርገው ወደ ጅቡቲ ሲጓዙ በጭነት እጦት ሳቢያ ወደ ጅቡቲ ሲጓዙ ባዶ ኮንቴነር ጭነው ነው።

የስራ መቀዛቀዝ የገጠማቸው ግን እርሳቸው ብቻ አይደሉም። 300 ገደማ ተሽከርካሪዎች የሚያስተዳድረው ዩናይትድ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማሕበር ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ የጭነት እጦት ይፈትነው ይዟል። ድርጅቱ እቃዎችን ለማጓጓዝ ከኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር የአንድ አመት ስምምነት አለው። "አሁን ያለው የጭነት ሁኔታ ከዚህ በፊት እንደነበረው አይደለም" የሚሉት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ  አቶ ተስፋዬ ርሶም ወደ ጅቡቲ ያቀኑ ተሽከርካሪዎቻቸው በጭነት እጦት ሳቢያ ለመቆም መገደዳቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረል።

አንድ ተሽከርካሪ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ተጉዙ ጭነት ፍለጋ እስከ 15 ቀናት ለመጠበቅ መገደዱን አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ። ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት የደረቅ ጭነት የሚያመላልሱት ተሽከርካሪዎች ከዚህ ቀደም በአንድ ወር ቢያንስ እስከ አራት ጊዜ ወደ ጅቡቲ ያደርጉት የነበረው ምልልስ አሁን ቀንሷል። የሥራው መቀዛቀዝ ደግሞ ለተሽከርካሪ ባለንብረቶችም ሆነ ለማህበራቸው ፈተና ሆኗል። "ከባድ ነው። ባለንብረቱም ላይ ማሕበራችንም ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። አንድ መኪና በዛ ቢባል አንድ ወይም ሁለት ምልልስ ያደርጋል ማለት ነው። ይኸ ደግሞ ኪሳራ ነው" ሲሉ ያክላሉ።

እድዩር ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማሕበር  152 በአባልነት የተመዘገቡ ከባድ ከመኪኖች አሉት። ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከሞጆ ደረቅ ወደብ እና ከቃሊቲ ጉሙሩክ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጭነት የማጓጓዝ ሥራ ይሰራል። ከኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር በጥምረት የሚሰራው ኩባንያው አንድ ተሽከርካሪ ጅቡቲ ደርሶ ለመመለስ በአማካኝ 10 ቀናት ይወስድበታል። በዚህ ስሌት መሰረት አንድ ተሽከርካሪ በወር 3 ምልልስ መስራት ይጠበቅበታል። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሶሪ ደንደዓ እንደሚሉት የተሽከርካሪዎቻቸው ምልልስ በስድስት ወራት ብቻ ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል።

ኢትዮጵያ ከገጠማት ጠንካራ ፖለቲካዊ ቀውስ በኋላ ወትሮም መፍትሔ ያልተበጀለት  የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየከፋ መሔዱ ይነገራል። የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት ጭምር ሥራቸውን ለመከወን ይኸው እጥረት እየፈተናቸው መሆኑን በአደባባይ ከመናገር አልተቆጠቡም። ለድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት ሥራ መቀዛቀዝ ከሚቀርቡት ምክንያቶች ይኸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያስከተለው የገቢ ንግድ መዳከም  አንዱ ነው። እድዩር ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማህበር 30 ተሽከርካሪዎች ላለፉት 14 ቀናት በጅቡቲ ወደብ ወረፋ በመጠበቅ ላይ ናቸው። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሶሪ ደንደዓ በሚቀጥሉት ቀናት ጭነው ይወጣሉ የሚል ተስፋ አላቸው። "ቀድሞ ይኸ አልነበረም" የሚሉት አቶ ሶሪ መዘግየቱ በወረፋ ምክንያት እንደተፈጠረ ያስረዳሉ።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic