የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ይዞታ | ኤኮኖሚ | DW | 30.11.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ይዞታ

ኢትዮጵያ ዛሬም የሚያሳዝን ሆኖ በኤኮኖሚ ኋላ ቀርነቷ በዓለም ላይ የድሃ ድሃ ተብለው ከሚመደቡት ሃገራት አንዷ ናት።

default

አብዛኛው ሕዝቧ ከአንዲት ዶላር ባነሰች የቀን ገቢ ኑሮውን የሚገፋ ከድሀነት መስፈርት በታች የሚኖር ሲሆን የረሃብ ሰለባነቱ አሁንም አላቆመም። በአገሪቱ እስካሁን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ባለመቻሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ይራባሉ፤ ለረሃብ ሞትም ይጋለጣሉ። በዓለምአቀፍ ጥናቶች መሠረት ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ዕድገት ደረጃ በምድራችን ላይ የመጨረሻ ከሆኑት ከጥቂቶቹ የምትደመር ናት። ይህ ሁሉ የሚሆነው እርግጥ በአገሪቱ ለልማትና ራስን መግቦ ለማሳደር የሚበቃ የእርሻም ሆነ ሌላ የተፈጥሮ ጸጋ ጠፍቶ አይደለም።

በአገሪቱ በአንድ በኩል ለም መሬት በገፍ ለውጭ ባለሃብቶች እንዲከራይ እየተደረገ ሲሆን የዋጋ ግሽበት ብዙዎችን ፈታኝ ከሆነ የኑሮ ሁኔታ ላይ ጥሎ ነው የሚገኘው። መንግሥት በበኩሉ ባለፉት ዓመታት ከአሥር በመቶ በላይ የኤኮኖሚ ዕድገት ሲደረግ እንደቆየ በማመልከት በአስተዳደር ዘመኑ ታላቅ የልማት ዕርምጃ እንደተደረገ ነው በየጊዜው የሚናገረው። ኢትዮጵያን ወደ ኢንዱስትሪ ዘመን ለማሸጋገርና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ለመቀላቀል ያወጣው የአምሥት ዓመት የዕድገትና የለውጥ ሽግግር፤ የትራንስፎርሜሺን ዕቅድም ዓመት ካስቆጠረ ጥቂት ጊዜ አለፈው። ይህን ሁሉ መለስ አድርጎ ለማጤን የአፍሪቃ ቀንድ የኤኮኖሚ ጉዳይ ተንታኝ የሆኑትን ክሪስቶፈር ኢድስን ሳነጋግር ባለሙያው የአምሥት ዓመቱን የዕድገትና የለውጥ ሽግግር ዕቅድ በራስ አቅም ለማሳካት መነሣቱ ተዓምር የመጠበቅን ያህል እንደሆነ ነው የገለጹት።

በጉዳዩ ይህን መሰል አስተሳሰብ ያላቸው እርሳቸው ብቻ አይደሉም። የዓለም የገንዘብ ተቋማትና በርካታ የለጋሽ ሃገራት ባላሙያዎችም ዕቅዱን አጠያያቂ ማድረጋቸው ይታወቃል። ለነገሩ ኢትዮጵያ ከባሕር ማዶ የልማት ዕርዳታ ገንዘብ በማግኘት በዓለም ላይ ቀደምት ከሚባሉት ሃገራት አንዷ ናት። ግን ይህም ሆኖ በዚሁ ላይ ባለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት ከአሥር በመቶ በላይ ዕድገት መደረጉ ቢነገርም ድህነት በአገሪቱ በሰፊው ሕያው እንደሆነ ነው። የብዙሃኑ ተራ ዜጋ የኑሮ ሁኔታ ይብስ ከፍቶ እንደሆን እንጂ ተሻሽሏል ለማለት አይቻልም። የአፍሪቃው ቀንድ የኤኮኖሚ ጉዳይ አስተንታኝ ክሪስቶፈር ኢድስ እንደሚሉት ለዚሁ አንዱ መሠረታዊ ችግር ለልማት የሚበጅ የተጣጣመ ዕርምጃ አለመኖሩ ነው።

“አዎን፤ የወቅቱ የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ይዞታ በጣሙን አወዛጋቢ፣ አከራካሪ ነው። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ባለፈው ወር የኢትዮጵያን የአምሥት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሺን ዕቅድ አስመልክቶ ሲገልጽ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ያወጣቸው የዕድገት አሃዞች የተጋነኑ መሆናቸውን ነበር ያመለከተው። የምንዛሪው ተቋም እንግዲህ ከኢትዮጵያው መንግሥት ከሚመሳሰል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አልቻለም። እናም የራሱን የዕድገት ግምት ከሰባት እስከ ስምንት በመቶ ለዘብ አድርጎ ነው ያቀረበው። የአገሪቱን የኤኮኖሚ ሁኔታ እየተለወጠ መሄድ በተመለከተ እርግጥ ለምሳሌ በአንዳንድ ምርቶች ተክል፣ ዘይት ቡና ወዘተ. ረገድ የውጭ ንግድ መሻሻል መታየቱ አልቀረም። ይሁን እንጂ የአገሪቱ ኤኮኖሚ ሂደት የተጣጣመ ዕርምጃ በጣሙን ይጎለዋል። ከባድ የኑሮ ውድነት ነው ያለው። የዋጋው ግሽበት 40 በመቶ ገደማ ይጠጋል። ይህም መንግሥት የተጋነነ የዕድገት ዕቅዱን ለማራመድ ማዕከላዊው ባንክ ገንዘብ በብዛት እንዲያትም የማድረጉም ውጤት ነው። በዚህ ዓይነት ከሚፈለገው ግብ ለመድረስ አይቻልም”

የኑሮ ውድነት ከተነሣ በዚህ በመገባደድ ላይ ባለው በጎርጎሮሣውያኑ 2011 ዓ.ም.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ታላቅ የኤኮኖሚ ችግር ብዙዎችን የሕልውና ፈተና ላይ የጣለው የዋጋ ግሽበት ነው። ለይቶላቸው ያጡትን ትተን በፈረቃ እስከ መመገብ ወይም መቃመስ የደረሱት ቤተሰቦች ጥቂቶች አይደሉም። መደበኛው የአገሪቱ የሕዝብ ቀለብ ጤፍ ከዘጠኝ መቶ ብር በላይ ሲወጣ የሌሎች መሠረታዊ ምርቶች ዋጋም የማይደፈር ነው። መንግሥት የዛሬ ዓመት ገደማ ችግሩን ለመቋቋም በተወሰኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ተመን ቢያሰፍንም ዕርምጃው ፍቱን ሣይሆን መቅረቱና በመንፈቁ መልሶ መለወጡ አይዘነጋም። ግን ከዚያም ወዲህ በመሻሻል አቅጣጫ የጎላ ለውጥ መደረጉ ብዙም አይታይም።

“የዋጋ ግሽበቱን ከተመለከትን የገበያ ቁጥጥሩ የለወጠው አንዳች ነገር የለም። የሆነ ነገር ቢኖር ምናልባት ችግሩ ለጊዜው መሸጋሸጉ ነው። የምርት ክፍፍል ችግር፣ የአገሪቱ ነጋዴዎች ለገበያ ፉክክር የመብቃት ጉዳይ፣ የመንግሥቱ የወጪ ፖሊሲና የዕድገቱ ግብ አለመስመር እነዚህ ዋና ችግሮች ነበሩ። እንግዲህ የብዙሃኑ ሕዝብ ድሃ መሆን ምስጢር ይሄው ነው”

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ በአብዛኛው በእርሻ ልማት ላይ ጥገኛ ነው። ይሄው በአገሪቱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ላይ ያለው ድርሻ አርባ በመቶ ይሆናል። ሆኖም ኢትዮጵያ የእርሻ ምርቶቿ በዓይነት እንዲበዙ በማድረግም ሆነ በኢንዱስትሪ ሰርቶ ለገበያ በማቅረብ ለመጠቀም የደረሰች አገር አይደለችም። እንደ ብዙዎቹ የአካባቢው አገሮች የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቷን ለማሟላት ጥሬ ምርት፤ ለምሳሌ ቡናን መሸጥ አለባት። እንግዲህ የእርሻው ዘርፍ የሚገባውን ያህል እንዲለማ አለመደረጉ ሃቅ ነው።
ይህ ቢሆን ኖሮ ዛሬ በኢትዮጵያ ባለፉት አራት አሠርተ-ዓመታት ውስጥ በምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ሁለቴ ዓለም አያየ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በረሃብ ባላለቁም ነበር። ኢትዮጵያም የረሃብ መለያ ሆና ባልቀጠለች! ይህ መሪሩ ሃቅ ሲሆን አገሪቱ በሌላ በኩል አሁን ደግሞ ለም የአርሻ መሬትን በገፍ ለውጭ ባለሃብቶች በርካሽ በማከራየት ቀደምት እየሆነች ሄዳለች። የአገሬው ገበሬ መፈናቀል ወይም በውዴታም ሆነ በግድ የኖረበትን ቦታ ለቆ መውጣት ጉዳዩን እጅግ አወዛጋቢ ማድረጉም አልቀረም። በአፍሪቃ በአጠቃላይ ሂደቱን ከቅኝ አገዛዙ ዘመን የሚያመሳስሉት ታዛቢዎችም አሉ።

“መሬትን ለውጭ ባለሃብቶች የመስጠቱ ጉዳይ ዛሬ በአፍሪቃ በሰፊው አነጋጋሪ ሆኖ የሚገኝ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ብቻም አይደለችም ይህን አከራካሪ ፖሊሲ ገቢር እያደረገች ያለችው። ጥያቄው ለኢትዮጵያም ሆነ ለማንኛውም መሰል መንግሥት በረጅም ጊዜ ከውጭው የእርሻ ፕሮዤዎች የውስጥ የኤኮኖሚ ጥቅምን ማረጋገጥ ይችላል ወይ ነው። በመሠረቱ ዘመናዊው የእርሻ ፕሮዤዎች የምርት ዓይነትን ሊያበራክቱ፤ የሥራ መስኮች እንዲከፈቱ ሊያደርጉም ይችላሉ። ጉዳዩ እርግጥ የመሬት ይዞታን የተመለከተ ከባድ ቅራኔን ያዘለ ጉዳይም ነው። እናም ለአገር የኤኮኖሚ ጥቅም እንዲበጅ ሆኖ እስካልተያዘ ድረስ አስቸጋሪ ይሆናል። እንግዲህ መንግሥት ፕሮዤዎቹ ለአገር መጥቀማቸውን የማረጋገጥ ሃላፊነት አለበት ማለት ነው። በትክክል ቢካሄድ ሊጠቅምም ይችላል”

እስካሁን በዚሁ በኩል የተደረገ ይህ ነው የሚባል ዕርምጃ መኖሩ ግን ጎልቶ አይታይም።

“የመሬት ኪራዩ ዓላማ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን ወደ አገር መሳብ ነው። ዕውቀትን ለማስገባት ይበጃል፤ የሥራ መስኮችን ለአካባቢው ሕዝብ መክፈቱም ሌላው ነገር ነው። ሆኖም ይህን መሰሉ ዕርምጃ እስካሁን ጨርሶ አይታይም። እኔም ራሴ ስለነዚህ ፕሮዤዎች ሁኔታ ገና ለመስማት እፈልጋለሁ። በጥቂቱ የመንገድ ግንባታ መደረጉ፣ በዝቅተኛ ደረጃም ለአንዳንድ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ይወራል። ግን የእኔ ግንዛቤ ትልልቆቹ ፕሮዤዎች ገና ይህ ነው የሚባል ጭብት ውጤት ማሣየት እንዳለባቸው ነው። እስካሁን ዕርምጃው በጣም ቀስተኛ ነው”

የኢትዮጵያን ልማት በተመለከተ ሌላው አከራካሪ ጉዳይ መንግሥት እ.ጎ.አ. እስከፊታችን 2015 ዓ.ም. ለማሟላት ያወጣው የአምሥት ዓመት የዕድገትና የለውጥ፤ ትራንስፎርሜሺን ዕቅድ ነው። ይሄው አገሪቱን ወደ ኢንዱስትሪ ዘመን ለማሸጋገርና መካከለኛ ገቢ ካላቸው መንግሥታት ለማስተካከል የሚያልመው ዕቅድ ከወጣ ከዓመት በላይ ሲሆነው እስካሁን የዕድገቱ አዝማሚያ ብዙም ጎልቶ አይታይም። የአፍሪቃው ቀንድ የኤኮኖሚ ጉዳይ ተንታኝ ክሪስቶፈር ኢድስ በተለይ ትልቅ ችግር አድርገው የሚመለከቱትመተለይ የገንዘብ አቅምን ጉዳይ ነው።

“ይሄ መንግሥቱ ያወጣው ዕቅድ በመሠረታዊ ይዘቱ እንኳ ሊደረስበት የማይችል ጉዳይ ነው። የወቅቱ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ለምሳሌ አጠቃላዩ የኤኮኖሚ ይዞታ ዝቤት ላይ መሆኑን አጉልቶ የሚያሳይ ነው። ለተለያዩት ፕሮዤዎች ገንዘብ ማመንጨት መቻሉም አንድ አሳሳሲ ጉዳይ ይሆናል። አንዳንዴ ለጋሽ መንግሥታት ዕቅዱን ለማራመድ በቂ ገንዘብ ላይሰጡ ይችላሉ። መንግሥት እንደ ሚሌኒየሙ የግድብ ሥራ ቦንዶችን በመሸጥ አምሥት ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ የያዘው ጥረት በአገሪቱ ብዙ ገንዘብ ባለመኖሩ መሳካቱ የሚያጠያይቅ ነው። በአጭሩ ዕቅዱ እጅግ ከአቅም በላይ የተጋነነ ነው። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋምም ለዚሁ ነበር ጉዳዩን አጠያያቂ ያደረገው። ሰብዓዊና ተቋማዊ ብቃት መጉደሉ፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አነስተኝነትና የመንግሥቱ አቅም ውሱንነትም እንዲሁ ሃሣቡን የማይቻል ያደርገዋል። በኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ተዓምር እስካልተፈጠረ”

የኤኮኖሚ ዕድገት ተዓምር እንዲከሰት እርግጥ ከሙስና የጸዳ በጎ አስተዳደር፣ ሥልጡንና ሃላፊነት የሚሰማው አመራር መኖሩን አጥብቆ ይጠይቃል። ለአገር የሚጠቅም ፖሊሲ ለማራመድና ከታሰበው ውጤት ለመድረስ የሚቻለውም ይህ ሲሆን ብቻ ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic