የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ይዞታ | ኤኮኖሚ | DW | 29.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ይዞታ

ኢትዮጵያ በዓለም ዙሪያ በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት በመራመድ ላይ ከሚገኙት ሃገራት አንዷ መሆኗ ሲነገር ቆይቷል። መንግሥት በተደጋጋሚ እንዳስታወቀውም የአገሪቱ ዕድገት ባለፉት ዓመታት በተከታታይ አሥር በመቶና ከዚያም በላይ የዘለቀ ነበር።

ይሁንና አሁን ሰሞኑን ዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም IMF እንዳመለከተው የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላው አሃዝ ክልል ወረድ ቢልም አጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት ግን ዘንድሮ ካለፈው 2011/12 ዓ-ም 8,5 ከመቶ አንጻር ማቆልቆሉ የማይቀር ነው።

በምንዛሪው ተቋም አባባል የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ዕድገት በያዝነው 2013/14 ወደ 6,5 ከመቶ እንደሚወርድ ይጠበቃል። ይህም ግዙፍ የዕድገት ዕቅድ ያለውን መንግሥት ወጪ የሚያሰፋና የግሉን ዘርፍም የሚጫን ነው የሚሆነው። በዚያ ላይ የወጣቱ ስራ አጥ ብዛትና ሰፊ እንደሆነ የቀጠለው ድህነት ታክሎ ችግሩን ያከብደዋል። ዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ታዲያ በየጊዜው በሚንረው የዋጋ ግሽበት፣ በገቢ-ወጪ ሚዛን ላይ ባለው ግፊትና በግሉ ዘርፍ ከባድ ሁኔታ የተነሣ ኢትዮጵያ በተፋጠነ ዕድገት በመራመድ መቀጠሏን አጠያያቂ አድርጓል። በተቋሙ ዕምነት የውጭ መዋይለ-ነዋይን የበለጠ ለመሳብ ለውጦች አሰፈላጊ ናቸው።

አፍሪቃ ውስጥ ከናይጄሪያ ቀጥላ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛዋ የሆነችው ኢትዮጵያ ለውጭ መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ማራኪ ገበያና ርካሽ የሥራ ጉልበትም ያላት ሆና ነው የምትታየው። ሆኖም በግንቢያና በአገልግሎቱ ዘርፍ አንዳንድ ዕርምጃ ቢታይም አምራች የኤኮኖሚ ዘርፍ በማስፋፋቱ ረገድ ገና ብዙ ነው የሚቀረው። የግንቢያውን ዘርፍ ካነሣን ግዙፉ የኤነርጂና የትራንስፖርት መዋቅር ግንቢያ ዕቅዶች ብዙ ገንዘብ ነው የሚፈጁት። በምንዛሪው ተቋም የኢትዮጵያ ተጠሪ በያን ሚከልሰን አባባል ወጪው አገሪቱ በዓመት በግምት ከምታደርገው በ 33 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ምርት 15 በመቶውን ድርሻ የሚይዝ ነው።

የመንግሥቱ የልማት ወጪ ግዙፍነት እንግዲህ የግል ዘርፎችን ብድርና የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ሁኔታ ሲያከብድ በግሉና በመንግሥቱ የኤኮኖሚ ዘርፍ መካከል ያለውን ሚዛን ያልተጣጣመ እያደረገ መሄዱ አልቀረም። ይህም በረጅም ጊዜ የኤኮኖሚ ዕድገትን እንደሚጎዳ ሲሆን መዋዕለ-ነዋይ መሳቡንም ከባድ ያደርገዋል። ሂደቱ በዚህ ከቀጠለ የኤኮኖሚው ዕደገት መልሶ ከፍ ማለቱም የማይጠበቅ ነው።

በኤኮኖሚው ዕድገት ትንበያ ረገድ በመንግሥትና በዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋማት መካከል በየጊዜው የግምት ልዩነት ሲንጸባረቅ ቆይቷል። መንግሥት ባለፈው አሠርተ-ዓመት ከአሥር በመቶ ያላነሰ ዕድገት ማስመዝገቡን ሲናገር ይህም በአንዳንድ የኤኮኖሚ ጠበብት የተጋነነ ሆኖ መተቸቱ አልቀረም። ለማንኛውም የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ዕድገት ነጸብራቆች እየተስፋፋ የመጣው የአገልግሎት ዘርፍና የዕርሻ ልማት ሆነው ቆይተዋል።

ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡት የዕርሻ ልማት ውጤቶች መካከል ዋነኞቹ የአገሪቱ ምርቶች ቡና፣ ሌሎች ተክሎችና ከብቶች ናቸው። ያለቁ ዕቃዎችን ሰርቶ ለገበያ የሚያቀርብ አምራች የኢንዱስትሪ ዘርፍ በአንጻሩ ያን ያህል አልተስፋፋም። የምንዛሪው ተቋም ወኪል ሚከልሰን እንደሚሉት የአገሪቱን ሁለንተናዊ የኤኮኖሚ ዕርምጃ በተመለከተ ስጋትን ከፍ የሚያደርገው ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ጊዚ ውስጥ የምንዛሪው ፖሊሲ እየጠበቀ መምጣት ነው።

እርግጥ የዋጋ ግሽበት ወደ 6,1 ከመቶ ሲቀንስ ምናልባትም በያዝነውና በሚቀጥለው ዓመት ከአሥር በመቶ በታች ሆኖ እንደሚቀጥል ይታመናል። ለማስታወስ ያህል የዋጋው ግሽበት በዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ዓመት 2008 ዓ-ም 60 ከመቶ ተጠግቶ እንደነበር አይዘነጋም። እርግጥ የዋጋው ግሽበት የቀነሰው የአገሪቱን የምንዛሪ ክምችት በማፍሰስ ነው። ይሄው ባለፉት 2010/11 እና በተከታዩ 2011/12 የበጀት ዓመታት አንድ ቢሊዮን ዶላር ይሆን እንደነበር IMF ያመለክታል።

መረጃዎችን ለመጥቀስ ያህል በዚህ በያዝነው በፊታችን ሐምሌ ወር በሚጠቃለለው የበጀት ዓመት መጀመሪያ ተቀማጩ 2,3 ቢሊዮን ዶላር ይደርስ ነበር። ይህም በግምት የሁለት ወር ምርት ወደ አገር ማስገቢያ ወጪን ሊሸፍን የሚችል ነው። ሚከለሰን እንዳስረዱት መንግሥት ምናልባትም ይህንኑ የወጪ መጠን ጠብቆ ዓመቱን የሚጨርስ ሲሆን ነገር ግን ጥያቄው የዋጋ ግሽበትን ከአሥር በመቶ በታች ዝቅ እንዳለ ማቆየቱ ምን ያህል ይቻላል የሚለው ይሆናል።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በመሠረቱ ኢትዮጵያ ተጨማሪ መንገዶችንና ግድቦችን ለመስራት የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል። ሆኖም የተቋሙ የኢትዮጵያ ተጠሪ ላን ሚከልሰን እንደሚያስረዱት መንግሥት የግል ዘርፎችን ሚና ለማሳደግ የራሱን የመዋይለ-ነዋይ ፍጥነት ለዘብ ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ይህ ደግሞ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን በመሳብ የአገር ውስጥ የገንዘብ እጥረትን ለማለዘብ ይበጃል።

በወቅቱ ከጠቅላላው ዘርፍ ገንዘብ ሁለት-ሶሥተኛውን የሚቆጣጠረው የመንግሥት ይዞታ የሆነው የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ ነው። እንግዲህ የውጭ ገንዘብን ለማግኘት በሚከልሰን አባባል ኢትዮጵያ ለፊናንስ አገልግሎት ሰጪዎች አግባብን ማቃለል፣ የተሻለ የንግድ ሁኔታን ማመቻቸትና የግሉን ዘርፍ ጠቃሚ የልማት ሃይል አድርጋ ማየት ይኖርባታል። የምንዛሪው ተቋም ወኪል ኢትዮጵያ በትክክለኛ ፖሊሲ ከምናየው ፍላጎትና ምንጭ አንጻር ወደ አሥር በመቶው ዕድገት የቀረበ ዕርምጃ ልታደርግ እንደምትችል ያምናሉ።

ዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የታላቅ ግድብ ግንባታ ፍጥነቷን ለዘብ በማድረግ የተቀረው የኤኮኖሚ ዘርፍ እንዳይዳከም ወጪዋን እንዳታጣጥም ባለፈው መስከረም አስጠንቅቆ እንደነበር ይታወሳል። 4,5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈጅ የተገመተው ታላቅ የአባይ ግድብ ግንቢያ ከሁለት ዓመት በፊት ሲጀመር ዓላማውም ከእንግዲህ ከአምሥት ዓመታት በኋላ ተጠናቆ 6 ሺህ ሜጋዋት ሃይል ማመንጨት ነው። ከዚህም ከፊሉን ወደ ውጭ በመሸጥ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ይታሰባል።

ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም ላይ አምሥተኛዋ ቡና አምራች ሃገር ስትሆን ኤኮኖሚዋም ከአርባ በመቶ በላይ በእርሻ ምርቶች ላይ ጥገኛ ሆኖ ነው የቆየው። አሁን ግን ኤኮኖሚውን ሁል-ገብ በማድረግ ዕድገትን ለማፋጠን ይታሰባል። የምንዛሪው ተቋም ስጋት እንግዲህ በዚህ በተፋጠነና ግዙፍ በሆነ የግንቢያ ሂደት ውስጥ የግሉ ዘርፍ እንዳይዳከም ነው። ተቋሙ መንግሥት የግዙፍ ፕሮዤዎቹን ፍጥነት ለዘብ በማድረግና ከዚሁ ጎን የውጭ መዋዕለ-ነዋይን ይበልጥ ለመሳብ አመቺ ሁኔታን በመፍጠር ችግሩን ሊያቃልል እንደሚችል ያምናል።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች