የኢትዮጵያ የብድር ዩሮ ቦንድ እንዴት ሰነበተ? | ኤኮኖሚ | DW | 11.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ የብድር ዩሮ ቦንድ እንዴት ሰነበተ?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸውን ባሳወቁ ማግሥት ዋጋው አሽቆልቁሎ የነበረው የኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ አገግሟል። በተቃውሞ ወቅት በንብረቶች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች እና በገዢው ግንባር አባል ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረው የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ በዩሮ ቦንድ ግብይት ላይ ብቻ ሳይሆን ባለወረቶች ባላቸው አመኔታ ላይም ተፅዕኖ አሳድሯል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:29

የዋጋ መዋዠቁ በኢትዮጵያ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የለውም

የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን ሊለቁ መሆኑን ካሳወቁበት የካቲት 8 2010 ዓ.ም. ኢሕአዴግ አብይ አሕመድን ሊቀ-መንበር አድርጎ እስከ መረጠበት መጋቢት 18 2010 ዓ.ም. ያሉት ቀናት በዓለም ገበያ ለሚሸጠው የኢትዮጵያ የብድር ቦንድ መልካም ቀናት አልነበሩም። አይኤችኤስ ማርኪት በተባለው ኩባንያ የኤኮኖሚ እና የአገሮች የሥጋት ትንታኔ ባለሙያው ክሪስቶፈር ሰኪሊንግ "አብይ አሕመድ 180 አባላት ባሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ሆነው  ሲመረጡ የኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ ትርፍ  ወደ 22 በሚሆኑ  መሠረታዊ ነጥቦች  ቀንሶ ወደ 6.31 በመቶ  ዝቅ ብሎ ነበር" ሲሉ ይናገራሉ። 

የብድር ቦንዱ ግብይት የቀነሰው ግን እንዲያው በድንገት አልነበረም። ኢትዮጵያን የናጧት ተቃውሞዎች ቦንዱን በገዙ ባለወረቶች ዘንድ ጥርጣሬ መፍጠር ከጀመሩ ከራርመዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ "ሥልጣን እስኪለቁ ድረስ አገሪቱ በተቃውሞ ስትናጥ ስለነበረ የተወሰነ የዋጋ የመውረድ ነገር ነበር። ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ አገሪቱ እርግጠኝነት የጎደለው የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ገባች። የአገሪቱ የወደፊት ሁኔታ ምንድነው የሚለው በቦንድ ዋጋ ላይ ተፅዕኖ አለው። ኃይለ ማርያም ስልጣን ለቀው አብይ እስሚመረጡ ድረስ ገበያው ስለ ፖለቲካው እና ኤኮኖሚው የሚሰጠው ግምት ጥሩ አልነበረም" ሲሉ ያስረዳሉ።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ኤኮኖሚ ተመራማሪው አቶ ቢኒያም በዳሶ የቦንዱ ዋጋ እጅጉን አሽቆልቆሉ የነበረው በጎርጎሮሳዊው 2016 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት እንደነበር ያስታውሳሉ። የመንግሥት ቦንድ በዓለም አቀፍ ገበያ ከሚሸጡ አክሲዮኖች ጭምር አኳያ አስተማማኝ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቢኒያም መንግሥታት በቦንዱ አማካኝነት የሚበደሩትን ገንዘብ የመክፈል ዕድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ዋጋው እንደማይለዋወጥ ያስረዳሉ። አቶ ቢኒያም "የጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ከሥልጣን መውረድ አልተጠበቀም። ስለዚህ ያ ሲከሰት በጥር 2018 ከነበረው ዋጋ በፍጥነት ወረደ" ሲሉ የሥልጣን መልቀቂያው የፈጠረው ተጽዕኖ ያስረዳሉ። "መንግሥት ተረጋግቶ ይቆያል ወይ? አዲስ ጠቅላይ ምኒስትር መቼ ይመረጣል? የመምረጡስ ሒደት ምን ያህል ኤኮኖሚውን ያናጋዋል?" የሚሉ ጥያቄዎች ቦንዱን በገዙ ዘንድ መፈጠሩን የሚናገሩት አቶ ቢኒያም "መንግሥት ብድሩን መክፈል ይችላል የሚለው ጥያቄ እንዳላስተማመናቸው ያሳያል" ሲሉ ያክላሉ።  

የኢትዮጵያ መንግሥት ለቦንድ ገዢዎቹ አገሪቱ ሊገጥማት ይችላሉ ያላቸውን ቀውሶች በዝርዝር አስቀምጧል። በ108 ገፆች የተቀነበበው ሰነድ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ በቀጣናው የሚቀሰቀስ ፖለቲካዊ አሊያም ወታደራዊ አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ላይ ጫና ሊያሳድሩ ከሚችሉ አደጋዎች መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃል። ወደ ፊት የሚካሔዱ ምርጫዎች ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አሊያም የፖሊሲ ለውጥ ሊያስከትሉ እንደሚችሉም ያትታል። ክሪስፈር ሰኪሊንግ በኢትዮጵያ የታዩ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች፣ በንብረቶች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች እና በገዢው ግንባር ልኂቃን መካከል የተፈጠረው ውጥረት የአገሪቱን ቦንድ ለሸመቱ ሁሉ የሥጋት ምንጮች እንደነበሩ ይናገራሉ።

"የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በገዢው ግንባር አራት አባል ፓርቲዎች መካከል ቁልፍ አሸማጋይ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። የርሳቸው በድንገት ከሥልጣን መልቀቅ አሊያም ሥልጣን መልቀቃቸው የተተረጎመበት መንገድ ለባለወረቶች እምነት አሉታዊ ጫና አሳድሯል። ምክንያቱም ኢሕአዴግ መበታተን ሊጀምር ይችላል የሚለውን ጥርጣሬ አሳድጎት ነበር። በዚህ ውስጥ ቁልፍ የነበረው የኢሕአዴግ አባል በሆኑት በኦሕዴድ እና በብአዴን ልኂቃን መካከል ትብብር ሊኖር ይችላል የሚሉ ምልክቶች መታየታቸው ነው። ምክንያቱም ሕገ-መንግሥታዊ ለውጦች እንዲደረጉ የሚያስችል 2/3ኛ አብላጫ ድምፅ ወይም ተቀራራቢ የድምፅ ብልጫ ይኖራቸዋል። ያ ከተፈጠረ ደግሞ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ወይም ሕወሓት ያለውን ጫና ያሳሳል።  በባለወረቶች ባላቸው እምነት ላይ ድንጋጤ የፈጠሩት ጉዳዮች እነዚህ ናቸው" 

የኢትዮጵያ መንግሥት ቦንድ ገዝተው ላበደሩት በሰነዱ ውል በገባው መሰረት ከጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ.ም ጀምሮ መክፈል ይጀምራል። በፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ሳቢያ በቦንድ ግብይቱ ላይ የተፈጠረው የዋጋ መዋዠቅ ግን በአገሪቱ ኤኮኖሚም ሆነ በመንግሥቱ ላይ በቀጥታ አሁን የሚያሳድረው ጫና እንደማይኖር አቶ ቢኒያም ይናገራሉ።

የዋጋ መዋዠቁ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አይኑር እንጂ አቶ አብዱልመናን እንደሚሉት የአገሪቱ የኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ሁኔታ ግን በግብይቱ ላይ ጫና ያሳድራል። የቦንዱ ግብይት በቀጥታ ከኢትዮጵያ መረጋጋት ጋር የተቆራኘ ነው የሚሉት አቶ አብዱልመናን ገዢዎቹ ስለ ኢትዮጵያ የወደፊት እጣ-ፈንታ ያላቸው ትንበያ ዋጋውን እንደሚወስነው ይናገራሉ።

ዶይቼ ባንክ እና ጄፔ ሞርጋን የተባሉት የፋይናንስ ተቋማት የሚያስተዳድሩት የኢትዮጵያ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ለገበያ ሲቀርብ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት መጠኑ ባይታወቅም ተመሳሳይ የብድር ቦንድ ለሁለተኛ ጊዜ ይፋ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቆ የነበረ ቢሆንም እስካሁን የደረሰበት አልታወቀም። አቶ ቢኒያም የአሁኑ የቦንድ ዋጋ ያገገመበትን ፍጥነት እየጠቀሱ ገዢዎች በኢትዮጵያ ብድር የመክፈል አቅም ላይ ያላቸው እምነት አለመሸርሸሩን ይናገራሉ።

አቶ አብዱልመናን ግን በዓለም አቀፉ ገበያ የኢትዮጵያ ቦንድ ዋጋ መዋዠቅ የሚያስተላልፈው መልዕክት ቀጣዩን ሊጎዳ እንደሚችል ይናገራሉ። አቶ አብዱልመናን ጫናው ከቦንድ ግብይት ተሻግሮ ወደ ኢትዮጵያ አምርተው መሥራት በሚሹ ባለወረቶች ላይ ጭምር ሊሆን እንደሚችል እምነታቸው ነው። በጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ ያቀረበችው ዩሮ ቦንድ ከስድስት አመታት በኋላ 6.625 በመቶ ወለድ ይከፈልበታል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

 

 

Audios and videos on the topic