የኢትዮጵያ የባቡር ሀዲድ ፕሮጅክቶች | ኤኮኖሚ | DW | 29.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ የባቡር ሀዲድ ፕሮጅክቶች

ኣገራዊም ሆነ ኣህጉራዊ ልማት ሲታለም ኣስቀድሞ መታሰብ ያለበት ነገር ቢኖር የመሰረተ ልማት ኣውታሮች ዝርጋታ መሆኑ ኣያጠያይቅም። ኣንዱና ዋናው ደግሞ መንገድ ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሰፋፊ እና ከባህር በር ፈንጠር ብለው ለሚገኙ ኣገሮች የባቡር ሀዲድ ኣስፈላጊ ብቻም ሳይሆን ወሳኝነትም ኣለው ተብሎ ይታመናል።

ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ መንግስትም የአዲስ ኣበባ ከተማ የባቡር ኣገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ የኣገሪቱ ኮሪደሮች መጠነ ሰፊ የባቡር ሀዲድ ፕሮጀክቶችን ለመንደፍ የተገደደው። ታዋቂው የሲውዝ ባንክም ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ኣንዱ የሆነውን የአዋሽ ወልዲያ ፕሮጀክትን ለመደገፍ የ 1,4 ቢሊየን ዶላር መስጠቱን ኣስታውቐል። የብድሩ ስምምነትም ዛሬ በሲውዝ ክሬዲት እና በኢትዮጵያው የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መካከል ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።

እኛም ለዛሬው የኢኮኖሚ ዝግጅታችን ትኩረት ኣድርገነዋል፤ ጦና ይስጥልኝ የተወደዳችሁ የዶቸቬሌ ኣድማጮች ከዝግጅቱ ጋር ጃፈር ዓሊ ነኝ አብራችሁን ቆዩ።

በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሺን፤ የሚዔይሶ ደወሌ ፕሮጀክት ማኔጀር፤ ኢንጂነር መኮንን ጌታቸው ኣስፋው ማብራሪያ መሰረት በመላ ኣገሪቱ ባሉ ስምንት ኮሪደሮች በአጠቃላይ 4,744 ኪ ሜ ርዝመት ያለው የባቡር መስመር ለመዘርጋት ነው እየተሰራ ያለው።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም የአዲስ አበባው የ LRT ላይትሬል ትራንዚት ፕሮጀክት እስከ ኣሁን 50 በመቶ መጠናቀቁን የጠቀሱት ኃላፊው የአዲስ አበባ ሚዔይሶ ደወሌ እስከ ጂቡቲ የሚዘልቀውም 30 በመቶ መጠናቀቁን ኣረጋግጧል። የአዋሽ ወልዲያ ፕሮጀክትም ኣሁን ብድር የተገኘለት በመሆኑ በቀጥታ ወደ ግንባታ እንደሚገባ ኣስረድቷል። ኢንጂነር መኮንን።

ከአሮጌው የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ሀዲድ መስመር ጋር ጎን ለጎን እየተገነባ ያለው የአዲስ አበባ ሚዔይሶ ደወሌ ጂቡቲ ፕሮጀክት በኣጠቃላይ 656 ኪ ሜ ርዝመት ሲኖረው ስራውም በሁለት ተከፍሎ ነው እየተካሄደ ያለው። የመጀመሪያው ከአዲስ አበባ አዳማ ሚዔይሶ ሲሆን በተለይም ከአዲስ አበባ አዳማ ያለው መስመር ኢንጂነር መኮንን ጌታቸው እንደሚሉት ባለ ሁለት ሀዲድ መስመር ነው የሚሆነው። የዚህ መስመር ስራ 30 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን የሚዔይሶ ደወሌ ድሬደዋ ፕሮጀክትም 30,2 በመቶ ደርሷል ተብሏል።

ኣሁን ብድር የተገኘለት የአዋሽ ወልዲያ ፕሮጀክት ጠቅላላ ወጪው 1,7 ቢሊየን ዶላር ነው። ከዚህ ውስጥ የሲውዝ ክሬዲት የሰጠው 1,4 ቢሊየን ሲሆን ቀሪው 300 ሚሊየን ዶላር ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ይሆናል። የግንባታ ጨረታውንም ያሸነፈው ያፒ መርከዚ የተባለ የቱርክ ኩባኒያ መሆኑ ታውቐል። ሌላው ለኢንጂነር መኮንን ጌታቸው ያቀረብኩላቸው ጥያቄ እነዚህ ፕሮጀክቶች በእርግጥ በታለመላቸው ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቁ ኅችላሉ ወይ? የሚሊ ነበር።

ስራዎች በታለመላቸው ዚዜ ውስጥ ይጠናቀቁ ዘንድ እስከ ኣሁን ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ኢንጂነር መኮንን ጌታቸው ኣስፋው ለስራ መጉዋተት ምክኒያት ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን ችግሮችም ሳይጠቅሱ ኣላለፉም።

የባቡር ፕሮጀክቶችን ኣስመልክቶ ስራውን በባለቤትነት ከሚያካህደው የኢትዮጵያ ም/ባ/ኮርፖሬሺን በተጉዋዳኝ ከወዲሁ በስራው ላይ ያሉ ተቐራጭ እና ኣማካሪ የቻይና ኩባሊያዎችን ጨምሮ በቅርቡም የቱርክ ኩባኒያዎች እና ወደፊት ደግሞ የህንድ፣ የብራዚል እና የሩሲያ ኩባኒያዎችም በተለያዩ የኣገሪቱ ኮሪደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ብድር የማግኘቱ ዕድልም የሚያበረታታ ነው የሚሉት ኃላፍው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ድርሻውን ለመሸፈን ያለው ቁርጠኝነት ኣመርቂ መሆኑን ኣውስቷል። እናም ፕሮጀክቶቹ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከወረቀት ወርደው መሬት ላይ እንደሚነበቡ ያላቸውን እምነት ገልጿል።

ጃፈር ዓሊ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic