የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች አስተዋፅኦ | ኢትዮጵያ | DW | 30.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች አስተዋፅኦ

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከ1,000 እስከ 1,600 ወታደሮችን ለማዋጣት ተስማማች። የሰላም አስከባሪ ወታደሮቹ ተልዕኮ ለጊዜው አልታወቀም። በኒው ዮርክ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ 50 አገሮች ተመሳሳይ ቃል ገብተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:34

የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች አስተዋፅኦ

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወታደሮች ለማዋጣት ቃል ገባች። በዩናይትድ ስቴትስ የኒውዮርክ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመታዊ ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 50 አገሮች ባጠቃላይ 40,000 ወታደሮች ለማዋጣት ቃል ገብተዋል። ከአመታዊ ጉባዔው ጎን ለጎን በተካሄደው የሰላም ማስከበር ጉባዔ የታደሙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ በአፍሪቃ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በኩል ከአህጉሪቱ የሚውጣጡ ወታደሮችን ብዛት ይፋ አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ማዳጋስካር፤ ሴራሊዮን፤ ብሩንዲ፤ ዩጋንዳ፣ ካሜሩንና ላይቤሪያ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ለማዋጣት መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ ሁለት ባታሊዮን ማለትም ከ1,000 እስከ 1,600 ወታደሮችን የማዋጣት ፈቃደኝነቷንም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል አስታውቃለች።

«ጉባዔው ለአዲስና ነባር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስበር ተልዕኮዎች ወታደሮች የሚዋጡበትን መንገድ ፈትሿል። ይህ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ወታደሮች ማዋጣት ለሚፈልጉ አዲስና ነባር አገሮች መልካም እድል ነው። በዚህ መሠረት አገሬ ተጨማሪ ሁለት ባታሊዮን ወታደሮች ለማዋጣት፤ ስልጠና ለመስጠትና አስቸኳይ ዘመቻን ጨምሮ ልምድ ለማካፈል ቃል ገብታለች።»

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ተወልደ ሙሉጌታ አገሪቱ 12,000 ወታደሮችን በአስር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ማሰማራቷን ለዶይቼ ቨሌ ተናግረዋል።

50ዎቹ አገሮች በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከሚሳተፉ ወታደሮችና ፖሊሶች በተጨማሪ ሄሊኮፕተሮች፤ ባለሙያዎች፤ የመስክ ሆስፒታሎች፣ የቦምብ ማክሸፍ ስልጡኖችን ጨምረዉ ያዋጣሉ ተብሏል። ይህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አቅም ያሳድጋል ነዉ በተባለው።

በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከ120 አገሮች የተውጣጡ 125,000ወታደሮች፤ ፖሊሶች እና ባለሙያዎች አሉት። በጉባዔው ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ባንኪ ሙን ተልዕኮዎቹ 350 የህክም አገልግሎት መልጫዎች፤ 167 ሄሊኮፕተሮች፤ 70 አውሮፕላኖች፤ 7 መርከቦችና 13,000ተሽከርካሪዎች እንደሚያንቀሳቅሱ ተናግረዋል።

ለዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች አንድ አራተኛውን በጀት የምትሸፍነው ዩናይትድ ስቴትስ እግረኛ ወታደሮችን ስለማዋጣቷ ግን የተባለ ነገር የለም። ቻይና 8,000 ወታደሮችን ለማዋጣት ቃል ስትገባ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ልትሳተፍ የተዘጋጀችው ካሞቦዲያ 5,000 ወታደሮች አዋጣለሁ ብላለች።

አለም አቀፉን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሲያምስ የከረመው የወሲብ ቅሌት ካሁን በኋላ ሊደገም እንደማይገባም በጉባዔው ተገልጧል። ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመው ለሚገኙ የዓለም አቀፋዊው ድርጅት የሰላም አስከባሪ ወታደሮችም ይሁን ሠራተኞች ይቅርታ ሊደረግ እንደማይገባ ዩናይትድ ስቴትስ አሳስባለች።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic