የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ዘላቂነት አወዛጋቢ ምዘና | ኤኮኖሚ | DW | 13.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ዘላቂነት አወዛጋቢ ምዘና

ኢትዮጵያ በምግብ ሥርዓት ዘላቂነት መለኪያ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ቻይና የተሻለ ነጥብ አግኝታለች። ባለፈው ሳምንት የብሪታኒያው ዘ-ኤኮኖሚስት መጽሔት የጥናትና ትንታኔ አሐድ ይፋ ባደረገው መለኪያ 12 ደረጃ ሰጥቷታል። የኤኮኖሚ ባለሙያዎች ግን የመመዘኛ ነጥቦቹ የኢትዮጵያን ትክክለኛ የምግብ ሥርዓት ዘላቂነት አያሳዩም ሲሉ ይተቻሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:26

ኢትዮጵያን 12ኛ ላይ ያስቀመጠው የምግብ ሥርዓት ዘላቂነት መለኪያ

የ34 አገሮች የምግብ ሥርዓት ዓመታዊ ትንታኔ ይፋ ሆኗል።  ፈረንሳይ፣ ጃፓን እና ጀርመን ተከታትለው በሚመሩት ትንታኔ ኢትዮጵያ በ12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። የዘላቂ የምግብ መለኪያው በሶስት ምሰሶዎች የተደለደሉ ስምንት የመመዘኛ ነጥቦች አሉት። ከ100 በሚሰላው የነጥብ አሰጣጥ ከፍ ያለ ውጤት የተሰጣቸው አገሮች በዘርፉ የተሻለ አፃጸም አሳይተዋል ማለት ነው። ኢትዮጵያ ታዲያ በምግብ ብክነት 75.07፣ በዘላቂ ግብርና 64.88 እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብ ፈተና  56.18 በአጠቃላይ 65.38 ተሰጥቷታል።  

እንዴት?

የዳሰሳ ጥናቱን ላከናወኑትም ሆነ ለተመለከቱት አስገራሚ የሆነው ግን ኢትዮጵያ በ12 ኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ ነው።ታዲያ ኢትዮጵያ በዳሰሳ ጥናቱ እንዴት ጥሩ ነጥብ ልታገኝ ቻለች?  ሰነዱ ላይ በሰፈረው መረጃ መሰረት በጥናቱ ከተካተቱት 34 አገራት እጅጉን ደሐ የምትባለው ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከቻይና እና እጅጉን ከናጠጠችው የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶች ጭምር ልቃ ተገኝታለች።

ማርቲን ኮሔሪንግ በዘ-ኤኮኖሚስት መፅሔት የጥናትንና ምርምር አሐድ (The Economist Intelligence Unit) ዋና አርታዒ ናቸው። ከጥናቱ ጸሐፊያን መካከል አንዱ የሆኑት ኮሔሪንግ እንደሚሉት ኢትዮጵያን ጨምሮ በጥናቱ የተካተቱ አገሮች የተፈተሹባቸው መመዘኛዎች ከተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች ጋርም የተገናኙ ናቸው።

"የተመጣጠነ ምግብ እጦት፣ ድርቅ እና ከከባቢ አየር ለውጥ ጋር የተገናኙ ችግሮች የሚፈትኗት ኢትዮጵያ በዚህ መመዘኛ የተሻለ ደረጃ አግኝታለች።" የሚሉት ኮሔሪንግ "በምግብ ብክነት ምዘና ኢትዮጵያ ጥሩ አፈፃጸም አላት። ለምሳሌ ያሕል ከዩናይትድ ስቴትስ አሊያም ከፍተኛ የምግብ ብክነት ካለባት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አኳያ በተመጋቢዎች ዘንድ ያለው የምግብ ብክነት እጅግ አነስተኛ ነው።" ሲሉ ያክላሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የምግብ ብክነት የምግብ ሥርዓት ዘላቂነትን ለመፈተሽ እንደመመዘኛ ሊያገለግል ይችላል? የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ብስራት ተሾመ የምግብ ብክነት ብቻ ሳይሆን በዳሰሳ ጥናቱ ግልጋሎት ላይ የዋሉ ሶስቱም መመዘኛዎች ከምግብ ሥርዓት ጋር ያላቸው ግንኙነት ቀጥተኛ ለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው ።

"አሁን ኢትዮጵያ የእርሻ መሬት ላይ ሲሰበሰብ፣ ሲወቃ፣ ወደ ወፍጪ ሲሔድ ነው እንጂ ብክነት ያለው አንዴ ወደ ምግብነት ከተቀየረ በኋላ የምግብ ዋስትናዋ ያልተረጋገጠ አገር ላይ ምግብ ተገኝቶ ብክነት ይኖራል ተብሎ አይገመትም" የሚሉት አቶ ብስራት ለዘላቂ የምግብ ሥርዓት እንደመገምገሚያ መቀመጡም አሳማኝ እንዳይደል ይተቻሉ።

በጥናቱ መሰረት ኢትዮጵያ በምግብ ብክነት አትታማም። የምግብ ብክነትን ለመከላከል ፖሊሲ በማዘጋጀቱ ረገድ የመጨረሻው ከፍተኛ ነጥብ፤ በሥርጭት ወቅት በሚታይ ብክነት ደግሞ 50 ተሰጥቷታል። በሥርጭት ላይ ያለውን ብክነት መፍትሔ በመሻቱ ረገድ ግን ያገኘችው ዜሮ ነው።

የዳሰሳ ጥናቱ በሶስቱ መመዘኛዎች ኢትዮጵያን ከበለጸጉት አገሮች ሲያነፃጽራት ይታያል። ማርቲን ኮሔሪንግ እንደሚሉት ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካ እና የአውሮጳ አገራት በውፍረት አትታማም። የምግብ ጥራት መጓደልም አያሳስባትም።

"የተመጣጠነ-ምግብ እጦት ፈተናዎችን ከተመለከትን በኢትዮጵያ ረሐብ አለ። አስፈላጊ የሆኑ ቪታሚኖች እጥረት እና የሕፃናት መቀንጨርን የመሳሰሉ ችግሮች ይታያሉ። አብዝቶ የመብላት፤ ያለ ቅጥ የመወፈር እና የስኳር በሽታን የመሳሰሉ ችግሮች ግን አልገጠሟትም። አንዳንድ የምዕራብ አውሮጳ እና አሜሪካ አገሮች የሚታየው እና አለ ቅጥ መወፈር የሚያስከትለው የምግብ ጥራት መጓደል ኢትዮጵያ የለባትም።  እነዚህ ነገሮች ኢትዮጵያ ጥሩ አፈፃጸም እንዲኖራት አድርገዋል። ትልቁ እና አስደናቂው ነገር ከገቢ ጋር ያለው ግንኙነት ነው።" የሚሉት ኮሔሪንግ መመዘኛው ከአገራት የሐብት መጠን ጋር ግንኙነት የለውም ብለዋል።

ኮሔሪን እንደሚሉት "ከ34ቱ አገራት በሐብት እጅግ የናጠጠችው ዩናይትድ አረብ ኤሚሬት የከፋ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከ34ቱ መጨረሻ 34ኛ ላይ ነች። አማካኝ ግለሰባዊ አመታዊ ገቢ 1830 ዶላር ያላት እጅግ ደሐ የሆነችው ኢትዮጵያ በአንፃሩ ጥሩ ደረጃ ላይ ነች።"

ያላባራው የደቡብ እና ምሥራቅ ኢትዮጵያ ድርቅ በበሽታ፣ ምግብ እና ውሐ ፍለጋ በብዛት በሚደረግ የሰዎች እንቅስቃሴ፤  ተባብሷል። የዓለም የምግብ መርኃ-ግብር እንደሚለው በዘንድሮ ዓመት  10 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ዛሬም አስቸኳይ የምግብ እገዛ ያስፈልጋቸዋል። 3.6 ሚሊዮን ጣመን የያዛቸው ሕጻናት፣ ነፍሰ-ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች የተመጣጠነ ምግብ ድጋፍ ይፈልጋሉ።

የኤኮኖሚ ባለሙያው አቶ ብስራት ከየተመጣጠነ ምግብ መብዛት ይልቅ እጦቱ ኢትዮጵያውያን ላይ መበርታቱን እያጣቀሱ ይኸኛውም እንደ ማወዳደሪያ መቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራሉ።  

ለኢትዮጵያ አጠቃላይ አገራዊ ምርት 43 በመቶ ለውጭ ንግዱ 90 በመቶ አስተዋፅዖ የሚያበረክተው ኋላ ቀር ግብርና ዛሬም ከአየር ጠባይ ለውጥ ጋር እየታገለ ይገኛል። በመስኖ ውሐ የለማው የእርሻ መሬት ከ5 በታች ነው። የተበጣጠሰ መሬት የሚያርሱት የኢትዮጵያ ገበሬዎች አመታዊ የሰብል ምርት ከቀጠናው አገራት አማካይ ላይ እንኳ መድረስ ተስኖታል። የገበያ ትሥሥሩ ደካማ ነው። የተሻሻሉ ዘሮች እና ማዳበሪያ አጠቃቀም ውስን ነው።

ይኸ ሁሉ ቢሆንም እንኳ ሥር ለሰደደው የኢትዮጵያ ድሕነት እና የምግብ ዋስትና መፍትሔ ሊሆን የሚችለው በግብርና የሚመራ ኤኮኖሚያዊ እድገት እንደሆነ ባለሙያዎች ያምናሉ። ከግብርናው ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያላቸው የውሐ እና አፈር አጠባበቅን የመሳሰሉ ጉዳዮች በዚህ የምግብ ሥርዓት ዘላቂነት ውስጥ መለኪያ ሆነው ተቀምጠዋል።

"የምግብ ዘላቂነት የምግብ ሥርዓቱ ምን ያክል ዘላቂ ነው የሚለውን መፈተሽ ነው። የምግብ ሥርዓቱ ለአስርት አመታት መቀጠል ይችላል ወይ? ብዙ የበካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ይለቃልን? የውሐ ሐብቶች፤ አፈሩ ይመናመናሉ ወይ አገሩ የከባቢ አየር ለውጥን እንዴት መቋቋም ይችላል? የሚለውን የሚመለከት ነው። የምግብ ዋስትና በአንፃሩ ሰዎች በቂ፤ ጥራቱ የተጠበቀ እና ንጥረ ይዘቱ የተሟላ ምግብ የማግኘት እድል ማለት ነው። በዚህ አመት መጀመሪያ ይፋ ባደረግንው የምግብ ዋስትና መለኪያ ወደ 130 አገሮችን ፈትሿል። ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ከ130 አገሮች በ99ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።"

እንደ አቶ ብስራት ገለፃ ግን የምግብ ሥርዓትን የፈተሸው ሰነድ የናሙና አመራረጥ እና የጥናት ሥልት ችግሮች አሉበት። የመዋዕለ ንዋይ ባለሙያው ወካይም አይደለም ሲሉ ይተቻሉ። አቶ ብስራት የተፈጥሮ ሐብቶችን በመመዘኛነት በመጠቀም መደምደሚያ ላይ መድረሱ አሳማኝ አይደለም ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic