የኢትዮጵያ የመገናኛ ዘዴዎች ረቂቅ ደንብ | ኢትዮጵያ | DW | 17.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ የመገናኛ ዘዴዎች ረቂቅ ደንብ

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረቀቀዉ የልማታዊና የዲሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን መርሕና ሥልት ሀገሪቱ ዉስጥ ያሉትን የሚዲያ ተቋማት በልማታዊ ጋዜጠኝነት ጎራ ብቻ እንዲሰለፉ የሚያስገድድ፤ ሕገ-መንግስቱ ዉስጥ የተቀመጡትን ሐሳብን የመግለፅና የፕሬስ ነፃነትን የሚገድብ መሆኑ ተገለፀ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:17
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:17 ደቂቃ

የኢትዮጵያ የመገናኛ ዘዴዎች ረቂቅ ደንብ

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀዉና በረቂቅ ደረጃ የቀረበዉ የልማታዊና የዴሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን ፖሊስና ስትራቴጂ፤ ሀገሪቱ ዉስጥ ያሉትን የግልም ሆነ የመንግስት የሚዲያ ተቋማት በልማታዊ ጋዜጠኝነት ጎራ ብቻ እንዲሰለፉ የሚያስገድድና፤ ሕገ-መንግስቱ ዉስጥ የተቀመጡትን የተለያዩ ሀሰቦች የማያንሸራሽር የፕሬስ ነፃነትን የሚገድብ መሆኑ ተገልዖአል።

በነሃሴ ወር 2007 ዓ,ም በኢትዮጵያ የብሮድካስቲንግ ባለስልጣን የተዘጋጀዉ አዲሱ የሚዲያ ፖሊሲ ከዚህ በፊት በተለያዩ የፖሊሲ ክፍሎች ዉስጥ ተበታትኖ የነበረዉን የሚዲያ ፖሊሲ፤ አሁን ራሱን በቻለ በአንድ ፖሊስ ማዕቀፍ መያዙ ለየት እንደሚያደረገዉ የሚዲያ ባለሞያዎች ይጠቅሳሉ። በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ፈት ቤት የሚድያ ፖሊሲ ዝግጅትና ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መንግሥቱ ላምሮ፤ ፖሊሲዉ በሁለተኛዉ የእድገትና የትራንስፎርሜሸን እቅድ እንደ

አዉሮጵያኖቹ 2016 ዓ,ም ፀድቆ ሥራ ላይ እንደሚዉል ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። አዲሱ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ የሚያተኩርባቸዉን ጉዳዮች በተመለከተ አቶ መንግሥቱ ሲያስረዱ፣«ይኼ ፖሊሲ ሲዘጋጅ፣ በተለይ ከሀገሪቱ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ መዋቅሩ ምን ይመስላል፣ ይህንን መዋቅር ደግሞ የሚሸከምና ልማታዊ ሆኖ ሊቀጥል የሚችለዉ ሚዲያ ዓይነት እንዱስትሪ ሆኖ መገንባት አለበት የሚለዉ በዋናነት መነሻ ጥያቄ ሆኖ የተዘጋጃ ነዉ ማለት ነዉ። ስለዚህ ይህ የመጀመርያዉ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ራሱን ችሎ የተዘጋጀ ፖሊሲ የሚያተኩርባቸዉ ጉዳዮች አሉ፣ በዋናነት ከዚህ በፊት የነበረዉ አቅጣጫዎች የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃንን ብቻ ከግምት ያስገቡና በዛ መልኩ አቅጣጫ የተቀመጠባቸዉ ሲሆኑ፣ ያሁኑ ግን ከነዚህ በተጨማሪ የዓለም ቴክኖሎጂ የደረሰበትን የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ከግምት በማስገባት፣ በተለይ ሶሻል ሚዲያንም እንደሚዲያ አገልግሎት ላይ ማዋል ስለሚቻልበት ሁኔታ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ነዉ። ከዚህ ከማህበራዊ ሚድያ በተጨማሪ ደግሞ የዜና አገልግሎቶችን እንዲሁም የኪነ-ጥበብና የፊልም እንዱስትሪዎችን፤ እንዲሁም የዚህን ዘርፍ ምርምር ስራዎችንና የሰዉ ኃይል ልማቱን በአጠቃላይ ጠቅለል ባለ መልኩ ለመያዝ የተዘጋጀ ፖሊሲ ነዉ ብለን ልንወስድ እንችላለን ማለት ነዉ።»

የልማታዊና የዲሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን ፖሊስና ስትራቴጂ የተሰኘዉ ዓለማዉ አድርጎ የተነሳዉ ልማታዊ ጋዜጠኝነትን ማንኛዉም ሚድያ ተቀብሎ ማኅበረሰብ ዉስጥ ልዕልና እንዲያገኝ የማስራፅ ሥራ መስራት እንዳለበት ያትታል። የሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ አቶ ሚኪያስ ሰብስቤ፤ ልማታዊ ጋዜጠኛ የሚለዉ አከራካሪ ትርጉም እንዳለዉና ሆኖም ግን ያ ማለት የመንግሥትን ሥራ ሳይተቹ መደገፍ ብቻ ነዉ የሚለዉ ፖሊሲ ግልጽ እንዳልሆነ ይናገራሉ። አሁን ባለበት ደረጃም ፖሊሲዉ የሃሳብ ብዝኃነት ሳይሆን የሃሳብ አንድነትን የሚያራምድ፤ ይህም ሚዲያ የተለያዩ አሳቦችን እንዲያስተነግድ በሀገሪቱ ሕገ-መንግስት ዉስጥ የተቀመጠዉን ይፃረራል ይላሉ አቶ ሚኪያስ።

«በአገራችን እንደሚታዉቀዉ በየትኛዉም የሚዲያ ፖሊሲም በለዉ በሕግ-መንግስቱም በለዉ፣ በሌሎች የሚድያ ሕጎች የሊበራሊዝምን አቋም ይዞ ማራመድ ወንጀል አይደለም። ወይም ደግሞ ከሚዲያ ሕጉ የሚጣረስ ነገር አይደለም። ስለዚህ ከሕግ የማይጣረስ ሆኖ ሳለ፣ አንተ በዚህ መንገድ መስራትህ ከዛ በመለስ የወጣ ፖሊሲ ስትገደብ የሕጋዊነቱንም ጥያቄ ታነሳለህ ማለት ነዉ። ስለዚህ በነዚህ በተለያዩ መንገዶች አሁን ባለበት ይዘት የሚዲያዉ ፖሊሲ ቅርፅ የሚያስኬድ ነዉ ብሎ ማዉራት ይከብዳል። ወይም ደግሞ፣ እስካሁን የነበረዉን የሚዲያ ነፃነትን በተወሰነ መንገድ እንደገና ወደ ማጥበብ የሚሄድ ነዉ የሚሆነዉ ማለት ነዉ።»

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ሊቀ-መንበር አቶ መሠረት አታላይ ረቂቅ ፖሊሲዉ የሚለዉ የሀገሪቱ ሚድያ አቅጣጫ ለሠላም፤ ለልማትና ለዲሞክራሲ የሚሠራ ሚዲያ ቢሆን ይመረጣል ነዉ እንጂ ይገደዳሉ አይደለም፤ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 450 ጋዜጠኞች አባል የሆኑበት ማኅበርን የሚመሩት አቶ መሠረት ምክንያቱን ሲያብራሩ፤ <<ሀገሪቷ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ትከተል ማለት የምርመራ ጋዜጠኝነትን አትከተልም፣ ወይም ሌቦችን፣ ሙሰኞችን ሚዲያዉ ማጋለጥ የለበትም ማለት ግን አይደለም። ያም አንዱ የልማታዊ ጋዜጠኝነትን አቅጣጫ እንደሆነ ነዉ መሰመር ያለበት። ዞሮ ዞሮ ግን ሀገር ለማፍረስና ለህዝብ ጥቅም ያለመቆም ዝንባሌ ማንንም አይበጅም የሚል አቅጣጫ ወይም አንድምታ ያለዉ ነዉ መስሎ የታየኝ፣ በዛ አቅጣጫ ነዉ እኛ ያየነዉ»

አዲሱ የልማታዊና የዲሞክራሲያዊ መገናኛ ብዙኃን ፖሊሲና ስትራቴጂ ዋና ዓለማዉ ያደረገዉ የልማታዊ ጋዜጠኝነትን ለማራመድ ብቻ የተቀረፀ ከሆነ ለዘብተኛ ማለት ሊበራል የሆነ ሕገ-መንግስትን ጥያቄ ዉስጥ እንደሚከት የሚዲያ ባለሞያዎች ይናገራሉ።

መርጋ ዮናስ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic