የኢትዮጵያ ዕድገትና የዓለም ባንክ | ኤኮኖሚ | DW | 01.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ ዕድገትና የዓለም ባንክ

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት እያሳዩ መጥተዋል ተብለው ከሚቆጠሩት የአፍሪቃ ሃገራት መካከል አንዷ ሆና ቆይታለች። መንግሥት በበኩሉ የኤኮኖሚ ግንባታውን በማፋጠን በጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ-ም ገደማ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው

ሃገራት ደረጃ ለማድረስ መነሣቱ ይታወቃል። እርግጥ ለዚህ ያለፉትን ዓመታት የኤኮኖሚ ዕድገት ቀጣይ ማድረግ መቻሉ ግድ ነው።

በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ቢሮ ሃላፊ ጉዋንግ ቼንም የዕድገቱን መጠን ከፍ አድርጎ ለመቀጠል የግሉ የኢንዱስትሪና የንግድ ዘርፍ በቂ የፊናንስ ድርሻ ዕድል ሊኖረው እንደሚገባና አገሪቱ በእርሻ ላይ ካላት ከባድ ጥገኙነት መላቀቅ እንዳለባት ነው ያስገነዘቡት። በወቅቱ የፊናንሱ ዘርፍ በመንግሥት ፖሊሲ ተጽዕኖ ስር የሚገኝ መሆኑም ነው የሚነገረው። የአገሪቱን የኤኮኖሚ ዕድገት በተመለከተ ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋሟት ዝቅ ያለ ግምት ቢኖራቸውም መንግሥት አሁን በቅርቡ በሚገባደደው የኢትዮጵያ ዓመት በእርሻ ምርት መጨመር የተነሣ የ 10 በመቶ ዕድገት ነው የሚጠብቀው። ባለፉት ዓመታትም ከአሥር በመቶ በላይ ዕድገት ሲጠቀስ ቆይቷል። ነገር ግን የዓለም ባንኩ የኤኮኖሚ ባለሙያ ላርስ ሞለር እንደሚሉት የተቋማቱን የተለያየ ግምት አቀራርቦ መስራት የማይቻል ነገር አይሆንም።

«እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በጣም በፍጥነት የሚያድግ ኤኮኖሚ ነው ያላት። ለምሳሌ በ 2011/12 ዓመታት የ8,5 ከመቶ ዕድገት ታይቶ ነበር። ይህም በዓለም ላይ 12ኛዋ በፍጥነት የምታድግ አገር እንድትሆን አድርጓታል። ዕድገቱ ያለፈውን አሠርተ-ዓመት አብዛኛውን ጊዜ በ 10,6 ከመቶ ሲገመት ይህም ይፋው የመንግሥቱ አሃዝ መሆኑ ነው። በአጭሩ ግን የተለያዩ ተቋማት የሚቀርቡትን አሃዝ አቀራርቦና አጣጥሞ መስራት ይቻላል»

የዓለም ባንክ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ድርሻ በ 10 ከመቶ የተወሰነ ነው። የእርሻውና የአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ ድርሻ እጅጉን ያመዝናል። ከዚሁ ሌላ ስራ አጥነት ሰፊ ነው፤ ድህነትም በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

«እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ባለ ዝቅተኛ ገቢ አገር ናት። ድህነት ገና በሰፊው አለ። ሶሦው የአገሪቱ ሕዝብ ድሃ ነው። ግን ደግሞ ድህነቱ ባለፈው አሠርተ ዓመት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት የተነሣ ብዙ መቀነሱም አልቀረም። እኛ በቅርቡ የኤኮኖሚ ዘገባ ስናቀርብ እንደጠቀስነው ምንም እንኳ አብዛኛው የሥራ ጉልበት በእርሻ ላይ የተሰማራ ቢሆንም ምርትን በተመለከተ እርሻ ታላቁ ዘርፍ አይደለም። የአገልግሎቱ ዘርፍ ነው ትልቁ። በ 2011/12 ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት አንጻር ከእርሻው በመጠኑም ቢሆን በልጦ ታይቷል»

ኢትዮጵያ እንግዲህ ባለፉት ዓመታት በታየው ዕድገት ወደፊት መግፋቷ ይጠበቃል። ጥያቄው እንዴት ነው። «ኢትዮጵያ በዕድገቷ እንዴት ልትቀጥል ትችላለች? አገልግሎቱ ከእርሻው ዘርፍ መላቁ ሃቅ ነው። ሁለቱ ዘርፎች 90 በመቶውን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ይጠቀልላሉ። የኢንዱስትሪው ድርሻ 10 በመቶ ሲሆን ባለፈው አሠርተ-ዓመት በነበረበት ቦታ ነው የቆየው። እርግጥ መንግሥትም ተከታታይ የኤኮኖሚ ዕድገት በማግኘት ኢንዱስትሪን የማሳደጉን አስፈላጊነት ተረድቶታል። የአገልግሎት ዘርፍ ብቻውን አይበቃም። አምራች ኢንዱስትሪ መፍጠሩና የስራ መስክ መክፈቱ በጣም አስፈላጊ ነው የሚሆነው»

የዓለም ባንኩ ባለሥልጣን ጉዋንግ ቼን እንደሚሉት ኢትዮጵያ በ 2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ደረጃ ለመድረስ ፖሊሲዋን የግሉን ዘርፍ ለማስፋፋት በሚበጅ መንገድ ማጣጣሟ ግድ ነው። በባንኩ አገላለጽ አንድ አገር ባለ መካከለኛ ገቢ የሚባለው የዜጋው ዓመታዊ ነፍስ-ወከፍ ገቢ ከ 1,025 ዶላር በላይ ሲሆን ነው። በኢትዮጵያ ነፍስ-ወከፉ የዓመት ገቢ ከሁለት ዓመት በፊት በቀረበ መረጃ መሠረት 370 ዶላር ገደማ የሚጠጋ ነበር።እንግዲህ ኢትዮጵያ በዕድገቷ እንድትቀጥል ከተፈለገ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሚና ከፍ ማለቱ ግድ ይሆናል። በልምድ በተፈጥሮ ጸጋ የታደለ ካልሆነ በስተቀር የቱም አገር ለዚያውም የአጠቃላይ ብሄራዊ ምርቱ ግማሽ በእርሻ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ከመካከለኛ ገቢ ሃገራት ደረጃ መድረሱ እስካሁን አልታየም።በሌላ በኩል በመንግሥት የሚደገፉ የኤነርጂና የትራንስፖርት ፕሮዤዎች ባለፈው ዓመት በ 33 ቢሊዮን ዶላር ከሚገመተው ከአገሪቱ ዓመታዊ ብሄራዊ ምርት 19 በመቶ በሚሆን መጠን የፊናንስ ወጪ ተደርጎበታል። እንደ ዓለም ባንክ ደግሞ ይሄው የግሉን የንግድ ዘርፍ መጫኑ አልቀረም። የግሉ ዘርፍ ያገኘው ብድር በ 14 ከመቶ የሚገመት ነበር። ይህም ከአካባቢው አማካይ የ 23 ከመቶ ብድር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑ ነው። በመሆኑም የግሉ ዘርፍ ብድር በቀላሉ እንዲያገኝ መንግሥት የበለጠ ቢጥር እንደሚጠቅም ነው ቼን የሚናገሩት።የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ የግል ፍጆት እስከ 2012 በነበሩት አምሥት ዓመታት ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አንጻር ከ 85 ወደ 77 በመቶ ዝቅ ብሏል። በተመሳሳይ ጊዜ አጠቃላዩ የመዋዕለ ነዋይ መጠን ከ 16,4 ወደ 25,5 ከመቶ ሲጨምር የግሉ መዋዕለ ነዋይ ግን ማቆልቆሉ ነው የታየው።

የመንግሥቱ መዋይለ-ነዋይ ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት አንጻር ሲጨምር የግሉ ዘርፍ በአንጻሩ ማቆልቆሉ አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም። ከዚህ አንጻር በ 2025 የመካከለኛ ገቢ ደረጃ ላይ ለመድረስ የተጣለው ተሥፋ ዕውን ሊሆን መቻሉን የሚጠራጠሩት ጥቂቶች አይደሉም። የዓለም ባንኩ የኤኮኖሚ ባለሙያ ላርስ ሞለር በበኩላቸው ከዚያ ግብ ለመድረስ ከአሃዙ ይልቅ ስልቱ ወሣኝ ነው ባይ ናቸው።
«ኢትዮጵያ በ 2025 ባለ መካከለኛ ገቢ አገር መሆን እንድትበቃ ምን ያህል የዕድገት መጠን ያስፈልጋታል ብለን ስሌት አድርገናል። እንበል 10,6 /10,7 ከመቶ ዓመታዊ ዕድገት! ይህ መንግሥት በይፋ ሰንጠረዦቹ የደረሰበት ዕድገት ነው። ከዚህ ተነስቶ እንግዲህ ከአሁን በኋላ ምን ያህል ዕድገት ያስፈልጋል ማለት ይቻላል። እና ያለፈውን ዕርምጃ መድገም ቢቻል በ 2025 ከመካከለኛው ገቢ ደረጃ ተደረሰ ማለት ነው። ግን አሃዙ አይደለም ጠቃሚው። ጠቃሚው ምን ዓይነቱ ስልት ከዚያ ያደርሳል ነው» ኢትዮጵያ የአውራ ጎዳና መረቧን እስከ 2015 ወደ 136 ሺህ ኪሎሜትር ለማስፋት ታስባለች። ይሄው ከሶሥት ዓመታት በፊት ከ 50 ሺህ ኪሎሜትር ያነሰ ነበር። ከዚሁ ሌላ እስከ 2020 5 ሺህ ኪሎሜትር የባቡር ሃዲድ ለመዘርጋትም ዕቅድ አለ። መንግሥት ይህን ውጥኑን ገቢር ለማድረግ የብሪክስ ሃገራትን መዋዕለ ነዋይ ለማግኘት እንደሚጥርም ተጠቅሷል። ሆኖም ቼን በአብዛኛው መንግሥት በሚቆጣጠረው በዚህ ዘርፍ ፉክክር እንዲሰፍን ማድረጉ እንደሚጠቅም ያሳስባሉ። እስካሁን የአገሪቱ ዕድገት መንኮራኩር የአገልግሎቱ ዘርፍ መስፋፋትና እርሻ ሆነው ቆይተዋል። እርግጥ ኢትዮጵያ ዋና የልማት ዕርዳታ ተቀባይ አገር መሆኗም መዘንጋት የለበትም።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic