1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ክስ ቀረበበት

ዓርብ፣ መስከረም 3 2017

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ላይ ደግሞ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ችሎት ክስ ቀረበባቸው። ክሶቹ፣ ያልተገባ ጠቅላላ ጉባዔን ማድረግ፣ ውሳኔዎችን ማሳለፍ፣ ከፓሪስ ኦሊምፒክ ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሀብት ብክነት ተፈጽሟል የሚሉትን ያካትታል።

https://p.dw.com/p/4kaom
ፎቶ ማህደር፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ክስ ቀረበበት
ፎቶ ማህደር፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ክስ ቀረበበትምስል Haimanot Tiruneh/DW

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ክስ ቀረበበት

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ክስ ቀረበበት

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ላይ ደግሞ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ችሎት ክስ ቀረበባቸው። አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ እና ቴኒስ ፌዴሬሽኖች በጠበቆቻቸው በኩል 

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ የመሠረቷቸው ክሶች፣ ያልተገባ ጠቅላላ ጉባዔን ማድረግ፣ ውሳኔዎችን ማሳለፍ፣ ከፓሪስ ኦሊምፒክ ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ከፍተኛ የሀብት ብክነት ተፈጽሟል የሚሉትን ያካትታል።

የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ደግሞ ይህንን መከላከል ሲገባው ባለማድረጉና ውሳኔም ባለመስጠቱ ክሱ እንደቀረበበት ከከሳሽ ጠበቆች አንደኛው ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ የስፖርት ነክ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማይታዩ ጠቅሶ በሚደረገው ነገር ሀገር እንዳትቀጣ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲል አሳስቧል። 

የክሱ ዝርዝር እና ከሳሾች 

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 26 የብሔራዊ ፌደሬሽኖችን የያዘ ማዕቀፍ ነው። በተለይም ከፓሪስ ኦሎምፒክ ማግስት ከፍተኛ ትችት ሲሰነዘርበት የነበረው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቲ እና አመራሮቹ ላይ ክስ ያቀረቡት አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ሲሆኑ ከከሳሽ ጠበቆች አንዱ የሆኑት የሕግ አማካሪ እና ጠበቃ ጳውሎስ ተሰማ ናቸው። 

"ከደንቦቹ፣ ከሕጎቹ ውጪ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራቱ - ግንቦት 5፣ እንዲሁም ደግሞ በሰኔ 4 ውሳኔዎች ማሳለፉ እነዚህም ሕገ ወጥ ናቸው"።

 

ይህን ከጣሩ በኋላ ለኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር "የአስተዳደር አቤቱታ" ማቅረበቸውን የገለፁት ጠበቃው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስልጣኑን በትክክል ባለመጠቀሙና ምርመራ ሳያደርግ በመቆየቱ ብሎም ውሳኔም ሊሰጥ ባለመቻሉ በሕግ ተገዶ ውሳኔ እንዲሰጥ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ችሎት ላይ ክስ እንዳቀረቡበት ገልፀዋል። ለክስ ያበቃቸው ማስረጃ ምን እንደሆነም ጠይቀናቸዋል።

"አቤቱታውን ስንመረምር እንዲያውም እነሱ [አቤቱታ አቅራቢዎች] ከቀረቡልን ቅሬታዎች እጅግ በጣም የገዘፉ ማስረጃዎችን ነው ያገኘነው"።  ክሱ የቀረበለት ፍርድ ቤት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን የባንክ ሒሳቦች ማገዱንም ጠበቃው ተናግረዋል። "የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ ከቀረበለት በኋላ ግንቦት 5ቱም ሆነ ሰኔ 4 2016 ዓ.ም የተደረገው ጠቅላላ ጉባኤዎች እና ውሳኔዎች ሁሉ እንዲታገዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ታግደዋል"።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምላሽ 

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ በዚህ ክስ ላይ ምላሽ እንዲሰጡበት ለማግኘት በተደጋጋሚ ብንደውልም፣ በጽሑም ብንጠይቅ ልናገኛቸው አልቻልንም። ኮሚቴው ትናንት በሰጠው መግለጫ ግን "የስፖርት ነክ ጉዳዮች በመደበኛ ፍርድ ቤት እንደማይታዩ" በመግለጽ "የውሸት ቃለ- መሃላ በማቅረብ እና ተረኛ ችሎቱን በማሳሳት እግድ ያወጡበት መንገድ ከሳሽ ነን የሚሉት ግለሰቦች ተከራክረው ማሸነፍ የሚችሉበት እውነተኛ የሕግ መሰረት የሌላቸው መሆኑን ያሳያል" ብሏል። እንቅስቃሴው በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ያለው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሚደረገው ነገር "ሀገር እንዳትቀጣ" ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲልም አሳስቧል።

ከከሳሽ ጠበቆች አንዱ የሆኑት ጠበቃ ጳውሎስ ተሰማ ግን የኦሎምፒክ ኮሚቴው ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ጀምሮ ከገንዘብ ሚኒስቴር 200፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች 100 ሚሊዮን ገቢ እንደተደረገለት በመጥቀስ መንግሥት ሀብቱ የት ደረሰ የሚለውን የመመርመር ሥልጣን አለው በማለት የኮሚቴውን መቃወሚያ ውድቅ አድርገውታል።  ክስ የቀረበበት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እየተካሄደ ነው ያለውን "ግልፅ ሕገወጥ ተግባር" የስፖርት ቤተሰቡ ግራ ቀኙን አገናዝቦ እንዲመለከተው ሲል ጥሪ አድርጓል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ