የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ይዞታ | ኤኮኖሚ | DW | 22.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ይዞታ

ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ውስጥ ቢቀር ባለፉት አምሥትና ስድሥት ዓመታት በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት የምትራመደው አገር መሆኗ ሲነገር ቆይቷል።

default

መንግሥት እንደሚለው አገሪቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያለማቋረጥ ከአሥር በመቶ በላይ ዕድገት አሳይታለች። ዕድገቱን ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ያስከተለው ተጽዕኖም እምብዛም የገታው አይመስልም። አሃዙ ለመሆኑ ምን ያህል ተጨባጭና አስተማማኝ ነው? በሕዝብ የኑሮ ሁኔታ መሻሻልስ ይንጸባረቃል ወይ?

አፍሪቃ ውስጥ ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት በነበሩት አምሥትና ስድሥት ዓመታት በአማካይ አምሥት በመቶ የሆነ ያልተቋረጠ ዕድገት ለመጀመሪያ ጊዜ መታየቱ ሲነገር ነበር የቆየው። በኢትዮጵያ እንዲያውም በመንግሥቱ አባባል አሥርና ከአሥር በመቶ በላይ የሆነ ዕድገት በየጊዜው ተመዝግቧል። አሁንም የዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ተጽዕኖ መለስ እያለ ሲሄድ ዕድገቱ ከዚያው መጠን ባላነሰ መቀጠሉ ነው የሚነገረው። እርግጥ የዕድገቱ አሃዝ ከፍተኛነት በተለይም በኢትዮጵያውያን የኤኮኖሚ ጠበብት ዘንድ ብዙ የሚያከራክር ሲሆን በአንጻሩ የአፍሪቃው ቀንድ የኤኮኖሚ ጉዳይ ተንታኝ ክሪስቶፈር ኢድስ በበኩላቸው ቢቀር በዕድገቱ አጠቃላይ ስምምነት አለ ባይ ናቸው።

“አሃዙ ተቀባይነት ያለው መሆኑን በተለይም የዕርሻ ልማት በአገሪቱ ብሄራዊ አጠቃላይ ምርት ላይ ያለውን ድርሻና የአዝመራውን መጠን ከተመለከትን እንረዳለን። ብዙዎች የኤኮኖሚ ጉዳይ ተንታኞች የሚስማሙበት ነገር ነው። አገሪቱ ከፍተኛ የአጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ዕድገት ነው ያሳየችው። መንግሥት በተለይም የተለያዩ የልማት ዘርፎችን በዕቅዱ በማካተት ጥሩ ሥራ ሰርቷል ለማለት እችላለሁ። በጥቅሉ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርቱ ከፍ ማለቱ መንግሥት በዳታው ውስጥ ብዙ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በማካተቱ ነው”

በሌላ በኩል መንግሥት ባለፉት ዓመታት በየጊዜው ያቀረባቸው የኤኮኖሚ ዕድገት አሃዞች ብዙ ሲያከራክሩ ቆይተዋል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በርካታ የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ጠበብት እጅግ አጠያያቂ ሲያደርጓቸው ለመንግሥቱ ቀረብ ያሉት የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም ራሳቸው የሚያቀርቡት ግምት እንኳ አምሥትና ስድሥት ከመቶ ዝቅ ያለ ነው። ለመሆኑ ይህን ያህሉን ልዩነት ምን አመጣው? ጉዳዩ ቢቀር የመረጃው አያያዝና ምርመራ ሂደት ግልጽ መሆኑን አጣዳፊ ያደርገዋል። ክሪስቶፈር ኢድስ ይሁንና በዕድገቱ መጠን ላይ አንድነት ባይኖርም የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ጠንካራ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።

“እንደማስበው አንድ አጠቃላይ ስምምነት ያለበት ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ዕድገት ጠንካራ መሆን ነው። እርግጥ ዕድገቱ ምን ያህል ነው በሚለው ጥያቄ ላይ ልዩነት ይኖራል። አጠቃላዩ አመለካከት ግን ኢትዮጵያ መንግሥት በሚያቀርባችው አሃዞች መጠን ባይሆንም ጥሩ ዕርምጃ ማድረጓ ነው”

እርግጥ ነው በይፋ የሚባለውን ያህል ከፍተኛ መሆኑ ያጠያይቅ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ዓመታት የኤኮኖሚ ዕድገት እየታየ መምጣቱን ተቺና ተጠራጣሪዎቹ ሳይቀር የሚቀበሉት ነው። ግን የኤኮኖሚው ዕድገት ወደ ማሕበራዊ ልማት እየተለወጠ በመሄድ የሕዝብን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻሉ ወይም ወደ ጥሩው መለወጡ እስካሁን እምብብዛም ጎልቶ አይታይም። የዕድገቱ ተጠቃሚዎች ጥቂቶች ሲሆኑ ብዙሃኑ አሁንም ከድህነት መስፈርት በታች መኖር መቀጠላቸው ቀረብና ጎላ ብሎ የሚታየው ሃቅ ነው። የምግብ ዋስትና ችግር አለ፤ ኢትዮጵያ በማሕበራዊ ልማት ረገድ ዝቅተኛ ከሚባሉት ሃገራት መካከል አንዷ እንደሆነች የተባበሩት መንግሥታት ጥናቶች በየጊዜው ያመለከቱት ጉዳይ ነው። ታዲያ ምን መለወጥ አለበት? እንደ ክሪስቶፈር ኢድስ ከሆነ መፍትሄው መንግሥት በስልታዊ የልማት ጥረቱ መቀጠሉ ነው።

“አገሪቱ አሁን ባለችበት ደረጃና መንግሥት ከያዘው የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ አንጻር የዝቅተኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ሁኔታ ለማሻሻል ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል፤ ይህን በትክክል ለመናገር ያዳግታል። ከወዲሁ አንድ ግልጽ ነገር ቢኖር ግን የምግብ ምርትን በተመለከ መሻሻል መኖሩ ነው። የተክሉም ይዞታና የማዳበሪያውም ሁኔታ እንዲሁ! እርግጥ ሁኔታውን ለማሻሻል ገና ብዙ ጥረት ያስፈልጋል። የሥራ መስኮችን መፍጠሩም ጊዜ ከሚጠይቁት ነገሮች አንዱ ነው። በዚህ ሁኔታ መንግሥት ሊያደርግ የሚችለው ጥሩ ነገር በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ባለመ ስልታዊ ጥረት መቀጠል ነው። የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል በተጨማሪ በአገር ውስጥ የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦትንም ማጠናከር ያስፈልጋል”

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የአገሪቱን ብሄራዊ ምንዛሪ የብርን ዋጋ ከዶላር አንጻር በመቶ በመቀነስ የወሰደው ዕርምጃ አንድ ግብም ይሄው የውጭ ካፒታልን መሳብ ነው። ዕርምጃው በጥቅሉ የአገሪቱን የፉክክር ብቃት ለማጠናከር፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችቷን ለማሻሻልና የንግድ ኪሣራዋን ለማለዘብ እንደሚበጅ ታምኖበታል። በሌላ በኩል የብር ዋጋ በዓመት ገደማ ጊዜ ውስጥ ሶሥት ጊዜ ማቆልቆል የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን እንደገና እያጠናከረ ነው የሄደው። ዕርምጃው አስፈላጊ ቢሆንም የሰርቶ-አደሩ ሕዝብ ገቢ በኑሮው ውድነት መጠን አለመጨመሩም የመግዛት አቅምን የሚያዳክም መሆኑ አልቀረም።

“እንዳልከው ዕርምጃው አስፈላጊ ነበር። የብር ዋጋ ከሚገባው በላይ ሆኖ ነው የቆየው። እና 17 ከመቶ እንዲቀንስ መደረጉ በመሠረቱ ለኤኮኖሚው ዕርምጃ አስፈላጊ ነገር ነው። እርግጥ ጥያቄው በወቅቱ የቅነሣ መጠን ምን ያህል ሊዘልቅ ይችላል ነው። በሌላ በኩል የብር ዋጋ መቀነስ የውጭ መዋዕለ-ነዋይን ለመሳብና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር የሚልኩትን ገንዘብ ማሳደግ መቻል አለበት። በንግዱ ልውውጥ ረገድ ደግሞ ወደ አገር የሚገባውን ምርት በመቀነስ ሚዛኑን ለማሻሻል የሚረዳ ነው። ባለፈው ዓመት ተኩል ውስጥ ሂደቱ አዝጋሚ ነበር። አሁንም ጊዜ የሚወስድ ነገር ነው። በጠቅላላው የምንዛሪዉ ዋጋ ቅነሣ ወቅት በዚህ ዓመት ብዙ አዝመራ የሚጠበቅ በመሆኑ በብልህነት የተመረጠ ነበር ለማለት ይቻላል። ይህም ከፍተኛ የሆነውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም የሚበጅ ነው”

እስካሁን የተደረገው የብር ዋጋ ቅነሣ የተፈለገውን ውጤት እንዲያስከትል ከተፈለገ በቂ አይደለም፤ ተጨማሪ አሥር በመቶ ቅነሣ ተገቢው ነበር የሚሉ የኤኮኖሚ ታዛቢዎችም አልጠፉም። ይህ ደግሞ ከሞላ-ጎደል የክሪስቶፈር ኢድስም አመለካከት ነው።

“አሁን ካለው ተጨባጭ የገበያ ሁኔታ አንጻር ቅነሣው ጥቂት በመቶዎች ከፍ ቢል ባልከፋም ነበር። ግን ይህ ያልተፈለገው የኑሮ ውድነትን ላለማባባስ ይመስለኛል። እኔ እንደሚሰበው መንግሥት የብር ዋጋ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣና በውድቀቱም እንዳይቀጥል ለማድረግ ነው የሚጥረው”

የኢትዮጵያ መንግሥት ወደፊት የበለጠ የኤኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ባለፈው ወር አዲስ የአምሥት ዓመት የልማት ዕቅዱን ማስተዋወቁም አይዘነጋም። በዚሁ ዕቅድ መሠረት በያመቱ 14,9 ከመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ነው የሚታሰበው። ይህ ሁሉ ያላንዳች መቋረጥ ቢሣካና ዕድገቱ በማሕበራዊ ልማት ቢተረጎም ድህነትን እስከዚያው በግማሽ የመቀነሱን የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ግብ ሊያሟላ ወይም በጣሙን ሊቃረብ በበቃ ማሰኘቱ አይቀርም። ሆኖም የአፍሪቃው ቀንድ የኤኮኖሚ ጉዳይ ተንታኝ ክሪስቶፈር ኢድስ ያን ያህል ዕድገት አይጠብቁም።

“እኔ እንደማምነው በቀሩት በመጪዎቹ አምሥት ዓመታት የሚሌኒየሙን ግቦች ሟሟላቱ ከዕውነት የራቀ ነገር ነው። በወቅቱ ከ 11 በመቶ ዕድገት ቢደረስ እንኳ ለሃቁ የቀረበ ይመስለኛል። መንግሥት ኤኮኖሚውን ብዙ ወጥ በሆነ መንገድ ለማስፋፋት ብዙ ዘርፎችን ዒላማ ያደርጋል። እና የሚቀርቡት የግብ አሃዞችም ከመጠን በላይ ከፍተኛ ናቸው። ያለፈውን የአምሥት ዓመት ዕቅድ ካስታወስክ የመሠረታዊው ምግብ ምርት መጠን ግቡን አልመታም። የአሁኑም እንግዲህ ያለፈው ሲታሰብ መሳካቱን ማመኑ ከባድ ነው የሚሆነው”

በኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታት አሥር በመቶና ከዚያም በላይ የሆነ ያልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ያለው ሕልም ዕውን እንዲሆን ውስጣዊውን ጥረት ከማሕበራዊ ልማት ከማጣጣሙ ባሻገር በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ሁኔታ ላይም ጥገኛ የሚሆን ነው። የዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ተጽዕኖ ምናልባት ለዘብ ብሎ እንደሆን እንጂ ገና ጨርሶ አልተወገደም። ስለዚህም ያልተቋረጠና አስተማማኝ የኤኮኖሚ ዕድገት በያመቱ ማስመዝገቡ በተለያዩ ሁኔታዎች ላይ ጥገና ሆኖ መቀጠሉ የሚቀር አይመስልም።

መሥፍን መኮንን