የኢትዮጵያ ኢንተርኔት አገልግሎትና የRSF ዘገባ | ኢትዮጵያ | DW | 08.06.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ኢንተርኔት አገልግሎትና የRSF ዘገባ

ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋጅ ድርጅት - RSF ትናንት ባወጣው ዘገባ፤ የኢትትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት- ኢትዮ ቴሌኮም- ተጠቃሚዎች እንደልባቸው በኢንተርኔት መረጃ እንዳያገኙ አፈናውን ቀጥሏል ሲል ገለፀ።

RSF ኢትዮ ቴሌኮም አንዳንድ ድረገፆችን መክፈት የማያስችሉ ያላቸዉን መንገዶችን እየሞከረ መሆኑን አመልክቷል። ጽሕፈት ቤቱ ፓሪስ ፈረንሳይ የሚገኘዉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋጅ ድርጅት - /Reporters without borders / የኢትዮጵያ መንግስት ዜና እና መረጃዎችን ለመቆጣጠር አንዳንድ የእገዳ መንገዶችን መጠቀም መጀመሩን በዘገባዉ አመልክቷል። የመንግስት የሆነዉ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ተቋም፤ ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ሰዓት ድረገፆች እና የማህበረሰብ መገናኛዎች ላይ ስለሚፈፅመው እገዳ አይነት እና መጠን የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ኃላፊ አምብሮስ ፒየርን ሲያብራሩ « አሁን የሆነዉ የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ማንኛቸውንም ዓይነት የኢንተርኔት ግንኙነት እያገደ ሳይሆን የኢንተርኔቱንና የግለሰብ ግንኝነቶችን በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ ለመከታተል የሚችልበትን መንገድ በመሞከር ላይ ነው። ያ ማለት እስካይፕ እና የማህበረሰብ መገናኛ መንገዶች በጠቅላላው ታግደዋል ማለት አይደለም። ሆኖም የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮም ማንነት ሳይገለፅ በኢንተርኔት የሚደረጉ ግንኝነቶች እንደማይካሄዱ እየታገለ ነው»

ትናንት የወጣዉ የRSF ዘገባ TOR NETEWORK የተባለውን ፤ ማለትም የተጠቃሚዎች ማንነት ሳይገለፅ የታገዱ ድረገፆችን ለመክፈት የሚያስችል የኢንተርኔት ስልት ኢትዮ ቴሌኮም እንደዘጋ ያመለክታል። ድርጅቱ እገዳዉን ስለማድረጉ መረጃ ከየት አገኘ?

« ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫውን ያወጣነው ላለፉት ሁለት ሳምንታት የ TOR NETWORK እገዳ እንዳለ ማስረጃ ስላገኘን ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አንዳንድ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ከዚህ ቀደም ያደርጉት እንደነበረዉ አሁን የተዘጉ ድረገፆችን ሊከፍቱ አልቻሉም። ይህ በኢትዮ ቴሌኮም የተወሰደ ርምጃ ያን አዳጋች አድርጎታል።»

ይህን ጉዳይ አስመልክቶ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋጅ ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትን ወይንም ኢትዮ ቴሌኮምን ጠይቆ እንደሁ፤ ከጠየቀስ ያገኘው ምላሽ ምንድነዉ ብያቸዉ ነበር አምብሮስ ፒየርን « ከነሱ ጋ በቀጥታ አልተገናኘንም። ምክንያቱም እስካሁን ግንኙነት ያለን ከኢትዮጵያ ህዝብና ስለዚህ ጉዳይ ከሚነግሩን ኢንተርኔት ከሚጠቀሙ ኢትዮጵያዉያን። በዚህ መግለጫ ማመልከት የፈለግነዉ መንግስት ጉዳዩ እንዳሳሰበን እንዲገነዘብ እና ስለሁኔታዉም እንደምናዉቅ፤ እና ለውይይትም ሆነ ሁኔታን ለመረዳት በሩ ሁሌም ክፍት እንደሆነ ለማሳወቅ ነው።»

ከዚህም ሌላ ፒየር ሳልጠቅስ ማለፍ አልፈልግም ያሉት ከዚህ ቀደም ከሚመለከተው አካል ጋ ለመወያየት መሞከራቸውን ነው። « በጥር ወር አዲስ አበባ በነበርኩበት ወቅት አቶ በረከት ስምኦንን ለማግኘት ሞክሬ ነበር። ግን ከኔጋ ለመገናኘት ዝግጁ አልነበሩም። በአሁኑ ሰዓት ከዚህ መንግስት ጋ ያለን ግንኙነት ቀንሷል። ሆኖም ልናሳያቸዉ የምንፈልገው ለኢትዮጵያ የነፃ መረጃ ልውውጥ በቁርጠኝነት እንደምንከራከር ብቻ ነው። ይሄው ነው»

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic