የኢትዮጵያ ተቃውሞ ሰልፍ እና የፖለቲካ ቀውስ | ኢትዮጵያ | DW | 08.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ተቃውሞ ሰልፍ እና የፖለቲካ ቀውስ

ኢትዮጵያ ከቃዛፊዋ ሊቢያ በተቃራኒዉ፤ ገዢዉን ፓርቲ ለመቃወም ፤ ቅሬታን ለመግለጥ፤ መብትን ለመጠየቅና ለማስከበር በአደባባይ መሰለፍ በሕገ-ንግስቷ ከተረጋገጠ 21 ዓመት ዓለፈዉ። ሕገ-መንግሥቱ ከፀደቀ እስካሁን የተደረጉ ወይም ተሞከሩ የአደባባይ የተቃዉሞ ሰልፎች ግን አብዛኞቹ ሕይወት፤አካል ባጠፋ ግጭት ነዉ የሚያበቁት።ለምን?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:14

ኢትዮጵያ፣ የተቃውሞ ሰልፍ እና የፖለቲካ ቀውስ

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና የሚቆጣጠሯቸዉ መገናኛ ዘዴዎች መዓልት ወሌት እንደሚነግሩን ኢትዮጵያ የአፍሪቃ የእድገት-ብልፅግና፣ የሐብት ልማት ቀንዲል ብቻ ከሆነች በአስር ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎችዋቀለብባልለመነች ነበር።ኢትዮጵያ በርግጥ ሶማሊያን ወይም ደቡብ ሱዳንን አይደለችም።የሰላም፤ መረጋጋት፤ የፍትሕ፤ ዲሞክራሲ ሐገር ብትሆን ኖሮ ግን የአምና እና ዘንድሮ ጥረት፤ትኩረቷ ረሐብተኞችዋን ከመቀለብ ጋር በምርጫ ዉጤት ዉዝግብ የተገደሉ ዜጎችዋን አስረኛ ዓመት መዘከሪያዋ በሆነ ነበር።አልሆነም።አለመሆኑ በርግጥ ያሳዝናል።የሆነና የሚሆነዉ የአደባባይ ሰልፍ፤ ግድያ፤ እስራት፤ ስደት መሆኑ ደግሞ ያሰቅቃል፤ያሰጋልም።ግን ለምን?

የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ ሥልጣን የያዙበትን አርባኛ ዓመት ሲያከብሩ «ሰዉ ጀነትም ዉስጥ ቢሆን ቅሬታ ማቅረቡ አይቀርም» አሉ ሕዝባቸዉ በአገዛዛቸዉ ላይ ስላለዉ ቅሬታ ለጠየቃቸዉ ጋዜጠኛ።«ሊቢያ አሁን» ቀጠሉ ጠንካራዉ ገዢ «ጀነት ናት» እያሉ።

የሊቢያ ሕዝብ ከግመል ነጂነት ወደ 4Wመኪና አሽከርካሪነት፤ ከደሳ ነዋሪነት ወደ ሕንፃ፤ ቪላ ባለቤትነት፤ ከቴምር ቃራሚነት ወደ አፍሪቃ አንደኛ ደልቃቃ ሐብታምነት የተመነደገዉ በኮሎኔሉየአገዛዝ ዘመን ነበር።እና ሰዉዬዉ ያዉ እንደ ፖለቲከኛ አጋነኑ እንጂ አላበሉም።ካበሉም ሰዉ አፉን ለመመገቢያ ብቻ ሳይሆን ለመናገሪያም፤ አዕምሮዉን ለመገዢያ (ገዢዎችን ለመቀበያ) ብቻ ሳይሆን ለማሰቢያም፤ አካሉን ለመደሰቺያ ብቻ ሳይሆን ለነፃነቱም የሚጠቀምበት፤የሚያስፈልገዉ መሆኑን በቅጡ አለማጤናቸዉ ነዉ።ቃዛፊ ያሉትን ባሉ በሁለተኛ ዓመቱ የመናገር፤ የማሰብ፤ እንደልቡ የመንቀሳቀስ ነፃነቱን ሸብበዉ ሆድ ምቾቱን የጠበቁለት ሕዝባቸዉ ያነሳዉ ዓመፅ የአርባ ሁለት ዘመን ገዢዉን፤የልጅ፤ ዘመዶቻቸዉን ሕይወት፤ ሥልጣን በጀነት የመሰሏት ሐገራቸዉንም አጥፍቷል።እያጠፋም ነዉ።

ኢትዮጵያ በምጣኔ ሐብት አቅሟ በነዳጅ ከበለፀገችዉ ከቃዛፊዋ ሊቢያ ጋር ስትወዳደር ደሐ-የድሆች ደሐ ናት።የኢሕአዲግዋ ኢትዮጵያ በሶሻሊስታዊ ርዕዮተ ዓለም ተኮድኩዳ ከነበረችዉ፤ በሐብታሙ-ሐያሉ ምዕራባዊ ዓለም ከተገለለችዉ፤ ከሁሉም በላይ በጦርነት ከወደመችዉ ከደርግ ብጤዋ ብዙ መሻልዋ አያጠያይቅም።

በምጣኔ ሐብት መሻሻሏ፤ ማደጓ ወይም ትሻሻላለች መባሉ ወይም እንድትሻሻል መታቀዱ የሕዝቧን ፍላጎት በተለይም የፍትሕ፤የዴሞክራሲ፤የሰብአዊ መብት ጥያቄዎችን ሙሉ በሙሉ መልሳለች ማለት አይደለም። ሕዝብ ወይም የማሕበረሰብ ክፍል ቅሬታዉን መግለፅ፤ ወይም መብቶቹ እንዲከበሩ መጠየቅ የለበትም ማለትም የሰሜን አፍሪቃዉን ጠንካራ መሪ ስሕተት መድገም ነዉ።

ኢትዮጵያ ከቃዛፊዋ ሊቢያ በተቃራኒዉ፤ ገዢዉን ፓርቲ ለመቃወም ፤ ቅሬታን ለመግለጥ፤ መብትን ለመጠየቅና ለማስከበር በአደባባይ መሰለፍ በሕገ-ንግስቷ ከተረጋገጠ 21 ዓመት ዓለፈዉ።ሕገ-መንግሥቱ ከፀደቀ እስካሁን የተደረጉ ወይም ተሞከሩ የአደባባይ የተቃዉሞ ሰልፎች ግን አብዛኞቹ ሕይወት፤አካል ባጠፋ ግጭት ነዉ የሚያበቁት።ለምን?

በ1997 የተደረገዉ ምርጫ ዉጤትን በመቃወም የተደረገዉ ሰልፍ ያበቃዉ በትንሽ ግምት የሁለት መቶ ሰዉ ሕይወት ጭዳ ሆኖበት።የብዙ መቶዎችን ደም ፈስሶበት፤ ሺዎች ወሕኒ ተወርዉረዉበት ነዉ።ያኔ ቀሪዎች ለምን ሲሉ የያኔዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከሰጡት ብዙ መልስ አንዱ ሰልፈኞቹ ሥራ አጥ ነዉጠኞች ሥለነበሩ-የሚል ነበር።

«ለምርጫዉ የተደረገዉ ዘመቻ በሁሉም ዘገቦች ለአሐጉሪቱ ምሳሌያዊ ነበር።ድምፅ የመስጪያዉ ቀንም በሁሉም መመዘኛ አብነታዊ ነበር።ምክንያቱም ከዘጠና በመቶ የሚበልጡት መራጮች ድምፅ ሰጥተዋልና።»

ከምርጫ ዘመቻዉ በፊት፤ በምርጫ ዘመጫዉ ወቅት፤ ከዘመቻዉ በኋላ ድምፅ ሲሰጥም ሥለነዚያ «ሥራ አጥ እና ጋጠወጥ» ሥለተባሉት ኢትዮጵያዉን ከመንግስት ምንም አልሰማንም።የምርጫዉ ዉጤት ከተነገረ በኋላ-ወይም ዉጤቱ ሲያወዛግብ ግን «ዘራፊ፤የጎዳና ላይ ነዉጠኞች» መኖራቸዉ ተነገረ።

«አምስት የእጅ ቦምቦች በፖሊስ ላይ ተጥለዉ የተወሰኑ ፖሊሶችን ገደሉ፤አቆሰሉም።እነዚሕ ሥራ ፈት ወጣቶች ሁለት ጠመንጃም ከፖሊስ ዘረፈዉ ነበር።አንዱን ባለፈዉ ሐሙስ አገኘነዉ።ከሐሙስ በኋላ ነገሮች ተረጋግተዋል።በመሐሉ ብዙ ኢትዮጵያዉያን ሞተዋል።አዝናለሁ።ይሁንና የተለመደዉ ሰልፍ አልነበረም።»

አቶ መለስ ዜናዊ። ጥቅምት 1998።ላለለት ከያኔ እስከዘንድሮ ገዳዮች ለፍርድ የሚቀርቡበት፤ የሟች ወላጅ፤ ዘመድ ወዳጆች ካሳ፤ ቁስለኞች መታከሚያና ድጎማ የሚያገኙበት፤ እርቀ-ሠላም እንዲወርድ የሚጣርበት ዘመን በሆነ ነበር። የሆነዉ ተቃራኒዉ ነዉ።የመብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ እንዳሉት ጋዜጠኞች ከፃፉ፤ ፖለቲከኞች ከጠየቁ፤ የአደባባይ ሰልፍ ከጠሩ ይታሰራሉ።በአብዛኛዉ በአሸባሪነት ይወነጀላሉ።

ሌላዉ ቀርቶ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች በሐይማኖታዊ አስተዳደራችን መንግሥት ጣልቃ አይግባ በማለታቸዉ በአሸባሪነት እየተወነጀሉ ተገድለዋል፤ ታስረዋል፤ ተሰቃይተዋል።

ዘንድሮ የ1998ቱ ግጭት ሰለቦች አስረኛ ዓመት የሚዘከርበት፤ኢሕአዴግ የመቶ በመቶ የምርጫ ድል ማስመዝገቡን ያወጀበት-አንደኛ ዓመት የሚታወስበት የቀድሞዉን የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ በ«ጥሩ ዉጤት» አጠናቅቆ አዲስ ማቀዱን ያስታወቀበት፤ ካለፈዉ የመማሪያ፤ የወደፊቱን በበጎ ማማተሪያ ዓመት በሆነ ነበር።ያልነዉን ለመድገም ተቃራኒዉ መሆኑ ነዉ ግራዉ።

ሰዎች በተለይ የኦሮሚያና የአማራ መስተዳድር ነዋሪዎች ቅሬታቸዉን ለማሰማት ይሰበሰባሉ ወይም አደባባይ ይወጣሉ።የትናንት ሳምንት ዕሁድ ጎንደር ከተደረገዉ ሰልፍ በስተቀር ለሌላዉ ተቃዉሞ ሰልፍ፤የተሰጠዉ አፀፋ ግድያ፤እስራት፤ እና ዉንጀላ ነዉ።እንደገና ለምን?

የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀጥታ መልስ እንዲሰጡን ካለፈዉ ማክሰኞ እስከ ተናንት ድረስ በተደጋጋሚ ስልክ ደዉለን ነበር።ገሚሶቹ እየቀጠሩን ጠፉ።ሌሎቹ ሥልካቸዉን አጠፉ።የተቀሩት እኛን አይመለከትም አሉን።የሰብአዊ መብት አቀንቃኝ አቶ ግዛቸዉ ኤቢሳ አጭር መልስ አላቸዉ።

ከሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) መስራቶች አንዱ የነበሩትና ባሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ሸንጎ የተባለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር አረጋዊ በርሔ ለምን ለሚለዉ ጥያቄ በሁለት ምክንያቶች ላይ የተመሠረተ መልስ አላቸዉ።ሥብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተሰኘዉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ሐይለ ማርያም ሌላ መልስ አላቸዉ።

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሑይማን ራይትስ ዋች በቅርቡ ባወጣዉ ዘገባ እንዳስታወቀዉ በኦሮሚያ መስተዳድር የተነሳዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ ለመደፍለቅ የፀጥታ ሐይሎች በወሰዱት እርምጃ ከአራት መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዉ ገድለዋል።በብዙ መቶ የሚቆጠሩ አቁስለዋል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አስረዋል።

እንደ ተቃዉሞ ሠልፉ ሁሉ ግድያ፤ እስራቱ አድማሱን ወደ አማራ መስተዳድርም አስፍቶ እንደቀጠለ ነዉ።የአማራ መስተዳድር ርዕሠ-ከተማ ባሕር ዳር እንኳ ዉጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ሥብሰባ ጉብኝት ለማስተናገድ ተሞሽራ-በተቃዋሚ ሰልፈኞች መፈክር ተጋግላ በሟች ቁስለኞች ደም ጭቅይታለች ትናንት።

እስካሁን በየሥፍራዉ ለተገደሉ፤ ለቆሰሉ፤ ለሚሰወሩት ዜጎች ተጠያቂዉን ለፍርድ ማቅረብ ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ የሚቻል አይደለም።ግድያ፤እስራት፤ እንግልቱ የሚቆምበት ጊዜና ብልሐቱን ማወቅ ደግሞ ይበልጥ ከባድ ነዉ።ዶክተር አረጋዊ በርሔ ግን አጭር መልስ አላቸዉ።የፖለቲካ ልሒቃኑ ፋንታ የሚል።

አቶ ግዛቸዉ ኤቢሳ ግድያዉ እንዲቆም «የተቃዉሞ ሰልፉ መቆም አለበት።የተቃዉሞ ሰልፉ እንዲቆም ደግሞ የሕዝቡ ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት።» ይላሉ።የሕዝቡ ጥያቄ? አቶ ግዛቸዉ ይቀጥሉ።አቶ ያሬድ እንደሚሉት መንግሥት የሚወስደዉ የሐይል እርምጃ ከዚሕ ቀደም እንደነበረዉ ተቃዉሞዉን ማስቆሙ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።እስካሁን ካየነዉ የከፋ ደም እንዳይፈስ መፍትሔ መፈለግ ያለበት ራሱ መንግሥት ነዉ።ዶክተር አረጋዊ መፍትሔ የሚሉት ግን አቶ ያሬድ ከጠቆሙት ያለፍ ነዉ።አቶ ግዛቸዉ ለየት ያለ አስተያየት አላቸዉ።ሌሎቻችሁስ? ተወያዩበት።ፃፉ፤ ደዉሉልን።

ነጋሽ መሐመድ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic