የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ስኬትና ወጣቱ | ባህል | DW | 19.10.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ባህል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ስኬትና ወጣቱ

ከሶስት ዓስርት ዓመት በላይ መጠበቅ ግድ ብሎ ነበር። ታዲያ ብዙዎች በኳስ ፍቅር ነደው፣ በውጤቱ ግን ሲበዛ ደብነው፣ እንደዘበት ወደ አውሮፓ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ሸፍተውም ነበር። ድንገት ግን በፍቅር ተቃጣዮቹ ሸፍተው እንዳይቀሩ ሰበብ የሆነ፣ መላ ኢትዮጵያን ከዳር ዳር ያስፈነደቀ ክስተት ተፈጠረ። ከ31 ዓመታት በኋላም ቢሆን ታሪክ ተሰራ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ ዋንጫ ግጥሚያ ማለፉ እውን ሆኗል። ለመሆኑ ከዓመታት በኋላ ስኬቱ እንዴት ሊገኝ ቻለ? በዚህ ታሪካዊ ግጥሚያ ላይ ከተቆጠሩት ግቦች የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ ያዋሃደውን ወጣት እና ወጣቱ የተገኘበት የአዋሳ ከነማ ቡድን ውስጥ ተጫዋች የሆነ ሌላ ወጣትን አነጋግረናል።

ወጣት አዳነ ግርማ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በአማካይ እና አጥቂ ቦታ ተሰልፎ ነው የሚጫወተው። ተወልዶ ያደገው አዋሳ ከተማ በኳስ በሚታወቀው ኮረም ሰፈር ውስጥ ነው። ኮረም ሜዳ ላይ በልጅነቱ የተሯሯጠው ይህ ወጣት ለአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ማጣሪያ ተደጋጋሚ ግቦችን አስቆጥሯል። ወጣቱ በተለይ ቤኒን ኮቶኑ ውስጥ ከቤኒን ብሔራዊ ቡድን ጋር በነበረው ግጥሚያ ኢትዮጵያ አንድ ለአንድ የተለያየችበትን ግብ ያስቆጠረ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው። ካርቱም ውስጥ ሱዳን 5 ለ 3 ስታሸንፍም እንዲሁ ግብ አስቆጥሯል። አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የመልስ ጨዋታ ደግሞ ግብፅ ውስጥ ከሚጫወተው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አጥቂ ሳላዲን ሰኢድ ጋር በመሆን የመጀመሪያዋን ግብ ከመረብ አዋህዶዋል። ወጣቱ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሱዳንን 2 ለ ባዶ ባሸነፍንበት እና ለአፍሪቃ ዋንጫ ማለፋችንን ባረጋገጥንበት ወቅት የነበረው የደስታ ስሜት ከፍተኛ እንደሆነ ቢገልፅም ሱዳን ውስጥ ብሔራዊ ቡድኑ የደረሰበት በደል ግን መቼም የሚዘነጋው አይመስልም።

ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋ ወደ አፍሪቃ ዋንጫ

ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋ ወደ አፍሪቃ ዋንጫከወጣት አዳነ ጋር ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ ወደ በኋላ ላይ እንመለስበታለን። አሁን የአዋሳ ከነማ የእግር ኳስ ቡድን ውስጥ በመጫወት ላይ ከሚገኘው ሌላኛው ወጣት ጋር ወዳደረግነው ቃለ መጠይቅ እናልፋለን። ወጣቱ ቢንያም ታዬ፤ በቅፅል ስሙ ግስላ በሚል ነው የሚታወቀው። ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ መሳለሚያ ኳስ ሜዳ አካባቢ ነው። ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያደረገችውን ግጥሚያ በጭንቀት ተውጦ እንደተከታተለ ነው የገለጸልን።

ለወጣት አዳነ ብሔራዊ ቡድኑ ከሱዳን ጋር ካደረገው ግጥሚያ ይልቅ እጅግ አስጨናቂ የነበረው ውጤት የተጠማው የእግር ኳስ አፍቃሪ ስሜት ነበር። በተለይ ደግሞ የመጀመሪያው አጋማሽ ሲጠናቀቅ ቡድናችን ጫና ቢፈጥርም ግብ ማስቆጠር ያለመቻሉ የበለጠ ጭንቀት ፈጥሮበት እንደነበር አልሸሸገም፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ታላቅ ድል ይጠብቅ ነበረና። ወደፊት ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን ቀጣይ ጨዋታዎቹን በድል አጠናቆ ወደተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር እንመኛለን፤ ለዝግጅቱ ማንተጋፍቶት ስለሺ ነኝ፤ ጤናይስጥልኝ!

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 19.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16T7I
 • ቀን 19.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16T7I