1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰላማዊ ተቃውሞ ማፈን እንዲያቆሙ አምነስቲ አሳሰበ

Eshete Bekele
ሰኞ፣ የካቲት 11 2016

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም “ሰላማዊ ተቃውሞን ማፈን እንዲያቆሙ” የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቀረበ። የኢትዮጵያ መንግሥት አምስት ፖለቲከኞች እና ሦስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ በታሰሩ ሰዎች ላይ ክስ እንዲመሰርት አልያም እንዲፈታ አምነስቲ አሳስቧል።

https://p.dw.com/p/4cZec
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን እየተጠቀመበት ነው ሲል ተችቷልምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መንግሥትን የተቹ ታዋቂ ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን በማሰር የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን” እየተጠቀሙበት ነው ሲል የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰሰ። የድርጅቱ የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር ቲገረ ቻጉታህ የኢትዮጵያ መንግሥት “የአስቸኳይ ጊዜ ሕግጋትን በመጠቀም መሠረታዊ መብቶችን ወደሚነፍግ የቀድሞ ስልቶች መመለሱን ማቆም” እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል፣ የሰዓት ዕላፊ የማወጅ፣ የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት የመገደብ እና በአደባባይ መሰብሰብን የመከልከል ሥልጣን እንደሰጣቸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ የካቲት 11 ቀን 2016 ባወጣው መግለጫ አትቷል።

ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ጀምሮ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ጥር ወር ለተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሟል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እስካሁን በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አለመውጣቱን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ክፍል ዳይሬክተር ቲገረ ቻጉታህ ገልጸዋል።

“ይኸ ግልጽነት የጎደለው አሠራር መረጃ የማግኘት መብት እና የሕጋዊነትን መርኅ የሚቃረን” እንደሆነ የገለጹት ቻጉታህ ኢትዮጵያውያን ተግባራቸው የአስቸኳይ ሕጉን እንደሚጥስ ወይም በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ እየሆነ እንደሚቀጥል ለማወቅ እንደሚቸገሩ አትተዋል።

አቶ ታዬ ደንደአ
የኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአን ያለመከሰስ መብት አንስቷል። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ወዲህ አምስት ፖለቲከኞች እና ሦስት ጋዜጠኞች ክስ ሳይመሰረትባቸው መታሰራቸውን ከቤተሰቦቻቸው እንዳረጋገጠ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አስታውቋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገጉ በተገለጸበት ሐምሌ 28 ቀን 2015 የጸጥታ አስከባሪዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ካሳ ተሻገር በአዲስ አበባ ከመኖሪያ ቤቶቻቸው በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

አቶ ዮሐንስ ቧ ያለው ነሐሴ 9 ቀን 2015 እንዲሁም የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ ታኅሳስ 2 ቀን 2016 በቁጥጥር ሥር ውለዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት አቶ ታዬ ደንደዓን ያለ መከሰስ መብት በ3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛው ስብሰባው እንዳነሳ የኦሮሚያ ኮምዩንኬሽን ቢሮ ዛሬ ሰኞ አስታውቋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት ሲራዘም ሌላው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ጥር 24 ቀን 2016 ታስረዋል።  

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአምስቱ ፖለቲከኞች ቤተሰቦች ሁሉም ክስ ሳይመሰረትባቸው እና ከጠበቆቻቸው ጋር ሳይገናኙ በፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ መናገራቸውን በመግለጫው ጠቁሟል። የፖለቲከኞቹ ቤተሰቦች ከፍተኛ ቁጥጥር በሚደረግበት ጉብኝት ለአጭር ጊዜ እንዳዩዋቸው አምነስቲ ገልጿል።

አምነስቲ ያንተርናሽናል
የኢትዮጵያ መንግሥት አምስት ፖለቲከኞች እና ሦስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ በታሰሩ ሰዎች ላይ ክስ እንዲመሰርት አልያም እንዲፈታ አምነስቲ አሳስቧል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ መሠረት የአማራ ሚዲያ ማዕከል ዋና ኤዲተር አባይ ዘውዱ፣ የኢትዮ ኒውስ ባልደረቦች በቃሉ አላምረው እና በላይ ማናዬ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሠሩ ጋዜጠኞች ናቸው። ሦስቱም ጋዜጠኞች በፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙ የጠቆመው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ጠበቆቻቸው እንዳይጎበኟቸው ባለሥልጣናት መከልከላቸውን፤ ክስ እንዳልተመሠረተባቸው ጉዳያቸውን ከሚከታተል ጠበቃ መረዳቱን ገልጿል።

“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሕጋዊ አሰራርን ወደ ጎን በማለት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰዎችን በገፍ ማሰር ማቆም አለባቸው” ያሉት ቲገረ ቻጉታህ የሀገሪቱን ሕግጋት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግዴታዎች በማክበር ከፍተኛ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በታሰሩ ሰዎች ላይ ክስ እንዲመሰርቱ አልያም እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥር 28 ቀን 2016 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ “ከተያዘው አብዛኛው ሰው ተምሮ ወጥቷል። በሺ የሚቆጠር ሰው ወጥቷል” ሲሉ ተናግረዋል። “በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው አሁን እስር ቤት ያሉት” ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እነሱም እየተጣሩ፤ እየተማሩ ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል።