1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሶማልያ ዉጥረት አሳሳቢ ነዉ ተባለ

ገበያው ንጉሤ
ዓርብ፣ መስከረም 3 2017

በኢትዮጵያና ሶማልያ መካከል እየተባባሰ የመጣዉ ዉጥረት አሳሳቢ ነዉ ሲል ዓለምአቀፍ የግጭት ጉዳዮች ዙርያ የሚሰራዉ ክራይስግሩፕ አስታወቀ። ቡድኑ እንዳስታወቀዉ ኬንያና ቱርክ ሁለቱን አገሮች ለማደራደርና ውጥረቱን ለመቀነስ ሲደረጉ የነበሩት ጥረቶች እስካሁን ውጤት አለማምጣታቸዉ ዉጥረቱን አሳሳቢ ያደርገዋል፤ የውጭ ኃይሎችንም የሚጋብዝ ሁኗል ብሏል።

https://p.dw.com/p/4kbmN
የኢትዮጵያ እና ሶማልያ ተደራዳሪዎች በቱርክ
የኢትዮጵያ እና ሶማልያ ተደራዳሪዎች በቱርክምስል Arda Kucukkaya/Anadolu/picture alliance

የኢትዮጵያ ሶማልያ ዉጥረት አሳሳቢ ነዉ ተባለ

የኢትዮጵያ ሶማልያ ዉጥረት አሳሳቢ ነዉ ተባለ
በኢትዮጵያ እና ሶማልያ መካከል እየተባባሰ የመጣዉ ዉጥረት አሳሳቢ ነዉ ሲል ዓለም አቀፍ የግጭት ጉዳዮች ዙርያ የሚሰራዉ ክራይስ ግሩፕ አስታወቀ። በተለይ በአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት ላይ የግጭት ጉዳዮችን የሚመረምረዉ ቡድን እንዳስታወቀዉ ኬንያ እና ቱርክ ሁለቱን አገሮች ለማደራደርና ውጥረቱን ለመቀነስ ሲደረጉ የነበሩት ጥረቶች እስካሁን ውጤት አለማምጣታቸዉ ዉጥረቱን አሳሳቢ ያደርገዋል፤ ቀደም ሲል በአፍሪቃ  ቀንድ የነበረው ውዝግብ፤ በአሁኑ ወቅት  ሌሎች የውጭ ኃይሎችንም የሚጋብዝ ሁኗል፣ ሁኔታዉ አሳሳስቢና አደገኛም ነዉ ሲል አጥኝዉ ቡድን አስታዉቋል። 
 
ከስምንት ወራት በፊት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ላንድ የባህር በር የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙ ወዲህ፤ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ በአጠቃላይ ውጥረት የሰፈበት ሁኗል። ሶማሊያ ስምምነቱን ልዑላዊ ግዛቷን የሚጥስ መሆኑን በመግለጽ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ዘመቻ የከፍተች ሲሆን፤ ካንዳንድ አገሮች ጋር የወታደራዊ ስምምነቶችን  በመፈራረም ጭምር ኢትዮጵያን በማስጠንቀቅ ላይ ነች።ኢትዮጵያ በበኩሏ፤ ስምምነቱ አስተማማኝ የወደብ አግልግሎትለማግኘት እንጂ የማንንም አገር ሉአላዊነት ለመጣስ ያለመ አይደለም በማለት ትከራከራለች።  ሁለቱን ወገኖች በማነጋገር ችግሩን ለመፍታት የተደረገው ጥረት እስካሁን ውጤት አላስገኘም። ይልቁንም  ይህንኑ ውዝግብ ተከትሎ ሶማሊያ ከግብጽ ጋር በተፈራረመችው ወታደራዊ ስምምነት መሰረት የግብጽ ወታደራዊ ቆሳቁሶች መቃድሾ መድረሳቸውና ግብጽም ወታደሩቿን በሶማሊያ ለማስፈር ዝግጁ መሆኗን ማስታወቋ የአዲአ አበባንና ሞቃዲሾን እሰጥ አገባ አንሮታል። ዲደብሊው በዚህ የሁለቱ አገሮች ውዝግብና የአፍሪቃ  ቀንድ ሁኔታ ላይ፤ በግጭትና ጦርነቶች ዙሪያ የሚሰራውን የዓለማቀፍ ክራይሥሥ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪቃ ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑትን ሚስተር ኦማር ማህሙድን ከናይሮቢ በስልክ አነጋግሯል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ምስል Office of Prime minister of Ethiopia


በሁለቱ አገሮች የተፈጠረው አለመግባባትናበአካባቢው ላይ የነገሰው  ውጥረት አሳስቢነቱ ምን ያህል ነው? የመጀመሪያው የዲደብሊው ጥያቄ ነበር፤ “ውጥረቱ አሳሳቢ ነው። ምክኒያቱም በኬንያና ቱርክ ሁለቱን አገሮች ለማደራደርና ውጥረቱን ለመቀነስ ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች እስካሁን ውጤት አላስገኙም። ከዚያ ወዲህ ሁለቱ አገሮች እንደውም ውጥረት በሚጨምሩ መግለጫዎችና የፖለቲካ እሰጣ ገባ ተጠምደው ነው የሚታዩት። ቀደም ሲል የአፍሪቃ  ቀንድ የነበረው ውዝግብ፤ ባሁኑ ወቅት  ሌሎች የውጭ ኃይሎችንም የሚጋብዝ ሁኗል” በማለት ሁኒታው አሳሳስቢና አደገኛም መሆኑን አስታውቀዋል።


ሶማሊያ በኢትዮጵያ ላይ በተለይ የተቆጣችበት ምክንያት
ቀደም ሲል ሌሎች አገሮችም ከሶማሌላንድ ጋር የወደብ ስምምነቶችን መፈራረማቸው የሚታወቅ ሆኖ ሳለ፤ ከኢትዮጵያ ጋር  የተደረሰው የባህር በር መግባቢያ ስነድ ሶማሊያን በዚህ መጠን ያስቆጣው ለምንድን ነው? ቀጣዩ ጥይቄ ነበር፤ “ ሶማሌ ላንድ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት እራሷን ነጻ አገር አድርጋ ብትቆጥርም ሶማሌ ግን ይህንን ተቀብላ አታውቅም።  አንድም ሌላ  አገርም እውቅና አልሰጣትም። የኢትዮጵው የመግባቢያ ስምምነት ግን የሶማሊያላንድን አገርነት እውቅና የሚሰጥ ይሆናል መባሉ ነው” ሶማሊያን ያስቆጣው ብለዋል ።
በሶማሊያ በኩል ስምምነቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በሁለቱ አገሮች መካከል የነበሩ የግዛት ጥያቄዎችና አለመግባባቶች ችግሩን ሳያወሳስቡት እንዳልቀሩም ሚስተር ኦማር አክለው ገልጸዋል።


የግብጽ ጣልቃ መግባት የፈጠረው ተጨማሪ ውጥረት
የሁለቱን አገሮች ውዝግብ ተክትሎ ግብጽ ኢትዮጵያን በማውገዝ ወታደሮችን በመላክ ጭምር ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም ማሳወቋ በአካባቢው ከፍተኛ ውጠረት መፍጠሩ እየተነገረ ሲሆን፤ ይህ የግብጽ በፍጥነት ከሶማሊያ ጎን መሰለፍና መቃዲሾ መገኘት አላስገረመዎትም ወይ ተብለው ተጠይቀውም ነበር ሚስተር ኦማር፤ ” ባንድ በኩል የሚያስገርም አይደለም፤ ምክኒያቱም ሶማሊያ የዲፕሎማሲ ድጋፍ ስታሰባስብ ነው የከረመችው። ግብጽም ከሶማሊያ ጋር የቆየ ግንኙነት አላት፤ በሌላ በኩል ግን ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በአባይ ጉዳይ አለመግባባት ያላት በመሆኑ ከሶማሊያ ጎን መስለፏ የሚጠበቅ ነበር ባይባልም የሚያስገርም ሊሆን አይችልም ብለዋል። የግብጽ በዚህ መጠንና ፍጥነት ከሶማሊያ ጎን መሰለፍ ግን፤  ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ከሶማሊያ ላንድ ግዛት ጋር ያላትን ልዩነትም የሚያሰፋና በሶማሊያ ውስጥም ተቃውሞ የሚቀሰቅስ ሊሆን እንደሚችል አክለው ገልጸዋል።

የሶማልያዉ ፕሬዚዳንት ከግብፅ አቻቸዉ አልሲሲ ጋር በካይሮ
የሶማልያዉ ፕሬዚዳንት ከግብፅ አቻቸዉ አልሲሲ ጋር በካይሮ ምስል Somalian Presidency/Anadolu/picture alliance


ውጥረቱ ወደ ወታደራዊ ግጭት እንዳያመራ ምን መረደግ አለበት?
ይህ ውጠረትና የፖለቲካ እሰጣ አገባ ወዴት ሊያመራ ይችላል? የተባሉት  ሚስተር ኦማር፤  “ በቀጥታም ይሁን በተዘዋሪ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል፤ እንደዚህ አይነቱ ሁኒታ ደግሞ የሚጠቅመው አንዳቸውንም አገሮች ሳይሆን  አልሸባብን የመሰሉ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ድርጅቶችን ነው” በማለት ይህ እንዳይሆን በአካባቢው ያሉ መንግስታትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ወደ እውነተኛ ውይይትና ድርድር ሊቀመጡ እንደሚገባ መክረዋል። “ በአካባቢው የውይይትና ድርድር ባህል የለም። በከፍተኛ ደረጃ የሚከሄድ ውይይትና ድርድር መኖር ይኖርበታል። የውጭ ኃይሎች ውይይትና ድርድሮችን በማዘጋጀትና በማሳለጥ ሊያግዙ ይችላሉ። ግን ችግሮቹ የአፍርሪቃ ቀንድ ችግሮች በመሆናቸው፤ መፈታት ያለባቸውም በአፍሪቃ ቀንድ መሆን ይኖርበታል ሲሉም የክራይሥሥ ግሩፕ የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪው አሳስበዋል ።


ገበያው ንጉሴ
አዜብ ታደሰ 
ነጋሽ መሐመድ