የኢትዮጵያ ስደተኞች በሶማሊላንድ | ኢትዮጵያ | DW | 04.09.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ስደተኞች በሶማሊላንድ

የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት ባለፈዉ አርብ ብቻ አንድ መቶ ኢትዮጵያዉን ስደተኞችን አስገድደዉ ወደ ኢትዮጵያ መልሰዋል። በሌላ በኩል የጀርመን መንግሥት በሊቢያዉ ጦርነት ምክንያት ዳግም ከተሰደዱ አፍሪቃዉያን መካካል ለ195 ጥገኝነት ሰጥቶአል። ኢትዮጵያዉን እና ኢርትራዉያን ይገኙበታል።

Foto DW/Richard Lough

በዘገባዉ መሠረት ተገደዉ ወደ ኢትዮጵያ ከተጋዙት ስደተኞች አብዛኞቹ ሴቶች እና ህፃናት ናቸዉ። የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን አስገድደዉ ወደ ኢትዮጵያ ማባረራቸዉን እንዲያቆሙ አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ ጠይቋል።

እንደ ዘገባው፤ ባለፈው አርብ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከሶማሌላንድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን ብቻ ሳይሆን ፤ ሀሙስ ዕለት ኢትዮጵያውያኑ የሚኖሩበትን ጣቢያ ለቀው እንዲወጡ በተጠየቁበት ጊዜ ብጥብጥ በመነሳቱ ፖሊስ ወደ ጣቢያው መጥቶ 56 ኢትዮጵያውያንን ማሰሩን፣ እንዲሁም ስድስት ኢትዮጵያውያን እና አራት ፖሊሶች መቁሰላቸውንም ተንትኗል። በናይሮቢ HRW ቢሮ ተመራማሪ የሆኑት ሊቲሺያ ቤደርን ስለ ስደተኞቹ ማንነት ሲናገሩ፤

«የነሱን ማንነት ለማረጋገጥ ከባድ ነው። ምክንያቱም ከ2008 ዓም ጀምሮ የሶማሌላንድ ባለስልጣናት አዲስ የሚመጡ ስደተኞችን መመዝገቡን አቁመዋል። ግን እንደእኛ እምነት ወደ አገራቸው ያለፈው አርብ ከተመለሱት ውስጥ በርካታዎቹ በስደተኝነት የተመዘገቡ ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህፃናት ናቸው።»

AFRICA,SOMALIA - Marketplace in Hargeisa, Somaliland. (Photo by: Africa 24 Media / Tim Freccia)ALL RIGHTS RESERVED

በሀርጌሳ ከተማ፤ ሶማሌላንድ

ምን ያህል ስደተኞች ድንበር እንዲሻገሩ መገደዳቸውን የሚገልፅ ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ አዳጋች እንደሆነ ቤደር ጠቅሰው የአይን እማኞች እንደገለፁላቸው ግን ቢያንስ 100 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ተናግረዋል። የሰብዓዊ ተሟጋቹ ዛሬ ባወጣው ዘገባ ላይ ከሶማሌላንድ ባለስልጣናት ስለሚጠብቀው እና ስለሙከራው ቤደር የሚከተለውን ብለዋል።

«ዛሬ ልናገኛቸው ሞክረን ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ይህ ጉዳይ ይመለከታቸዋል ብለን የምናምነው የአገር ውስጥ ጉዳይ ባለስልጣናቱን ለማግኘት አልቻልንም። ዋና ትኩረታችን ምንም እንኳን ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም የሶማሌላንድ ባለስልጣናት የኃይል ርምጃ መውሰድ የለባቸውም። ማንኛውም ሰው፤ ችግር አለብኝ፣ አደጋ ላይ ነኝ ፣ ስደተኛ ነኝ የሚልን ሰው ወደ አገሩ መመለስ የለባቸውም። የሶማሌላንድ ባለስልጣናት ስደት ጠያቂዎች ወደ ኢትዮጲያ ሲመልስ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም። በ2001 ታህሳስ ወርም ወደ 20 የሚጠጉ ኢትዮጵያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ሞክረዋል።»

Hargeisa Skyline. Foto: DW/Richard Lough

የሀርጌሳ ከተማ

ስደተኞቹ በተለያዩ የጭነት መኪናዎች ተሳፍረው በድንበሩ ወደምትገኝ ዋጃሬ ከተማ ተወስደዋል። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ተሽከርካሪዎች ወንዶቹን ብቻ የጫኑ እና የተቀሩት ሴቶች እና ህፃናት እንደነበሩ ዘገባው ይገልፃል። ተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ለ HRW እንደገለፀው ከሆነ የUNHCR ሰራተኞች 72 ስደተኞች እና አንዲት ሴትን ጨምሮ በዋጀሌ ከተማ አግኝቷል። እነዚህንም ስደተኞች ወደ ሀርጌሳ ከተማ መመለሱን አሳውቋል። UNHCR ለስደተኞቹ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት ነው ቤደር የተናገሩት።

«ርግጥ UNHCR እነዚህን ሰዎች ማግኘት የሚችልበት መንገድ ያስፈልገዋል። ይህም ያለፈው ሳምንት አንዱ ትኩረት ነበር። UNHCR ከሶማሌላንድ ባለስልጣናት ጋ በመሆን እንዲወያይ እንፈልጋለን። ከነዚህ ስደተኞች ጋ መገናኘት የሚችሉበትን መንገድ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ከማንኛውም ጭራሽ ካልተመዘገቡ እና ጥገኝነት ከሚሹ ኢትዮጵያን ጋም ቢሆን። UNHCR የሰዎቹን ጉዳይ ለማጥናት እና ስጋታቸውን ትክክለኛ መሆኑን ለመመልከት ማጣራት የሚችልበት መንገድ ያስፈልገዋል።»

ልደት አበበ

ይልማ ሃይለሚካኤል

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic