የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሁለተኛ ምርመራ | ኢትዮጵያ | DW | 06.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሁለተኛ ምርመራ

በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሁለተኛ ዙር መመርመር መጀመሩን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:38
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:38 ደቂቃ

የብዓዊ መብት ጥሰት ሁለተኛ ዙር ምርመራ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኹከት በተቀሰቀሰባቸው የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት አስር ቡድኖች ማዋቀሩን አስታውቋል። ኮሚሽኑ ካከናወነው የመጀመሪያ ዙር ምርመራ በኋላም በሁለቱ ክልሎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ኹከት የደረሰውን ጉዳት የመፈተሽ ግዴታ እንዳለበት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ብርሐኑ አባዲ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ብርሐኑ ኮሚሽኑ ካዋቀራቸው መርማሪ ቡድኖች መካከል አራቱ በአማራ ክልል ስድስቱ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል እንደሚሰማሩ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።


ከዚህ ቀደም ኮሚሽኑ ያዘጋጀውን ምርመራ ለኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። በዘገባ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 28 የጸጥታ አስከባሪዎችን ጨምሮ 173 ሰዎች መገደላቸውን ገልጧል። ቁጥሩ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተቋማት በዘገባዎቻቸው ካስታወቁት ጋር ከፍተኛ ልዩነት ይታይበታል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ባለፈው ሰኔ ይፋ ባደረገው ዘገባ እንኳ ከኅዳር 2015 እስከ ግንቦት 2016 ዓ.ም. ድረስ ብቻ በኦሮሚያ ክልል ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገልጦ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ተቺዎችም ኮሚሽኑ በገለልተኝነት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የመመርመር ነፃነት የለውም ሲሉ ይተቻሉ። አቶ ብርሐኑ አባዲ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን «የቁጥር ጨዋታ ውስጥ የመግባት ዓላማ የለውም» ሲሉ ይናገራሉ። 


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ባወጣው ዘገባ በሰሜን ጎንደር ዞን  የቅማንት ማሕበረሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሲያነሳ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል ሲል ወቅሷል። ኮሚሽኑ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ከ95 በላይ ሰዎች መግደላቸውንም ገልጧል። አቶ ብርሐኑ መሥሪያ ቤታቸው ያቀረበውን ዘገባ መሰረት በማድረግ የክልሉ መንግሥት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ተናግረዋል።


እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic