የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እና የአምነስቲ ግምገማ | ዓለም | DW | 22.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እና የአምነስቲ ግምገማ

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጎርጎሪዮሳዊዉ 2017 ዓ.ም. በዓለም የሰብዓዊ መብቶች ይዞታን በቃኘበት ዘገባ የኢትዮጵያ የመብት ይዞታ አሁንም ከችግር እንዳልተላቀቀ አመለከተ። ሀገሪቱ ዉስጥ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ተባብሶ ከቀጠለ ወዲህ መንግሥት አደርጋለሁ ያላቸዉ ማሻሻያዎች ተግባራዊ መሆናቸዉ ቀርቶ የመብት ጥሰቶች ተባብሰዉ መቀጠላቸዉን ድርጅቱ ገልጿል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:33

«የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ አልተሻሻለም»

ባለፈዉ ዓመት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ በኋላ በመንግሥት መረጃ መሠረት 26 ሺህ ገደማ ዜጎች ታሥረው እንደነበር ያመለከቱት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪቃ ተመራማሪ አቶ ፍሰሀ ተክሌ፤ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2017 ዓ.ም. የሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ብዙም አጥጋቢ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። በወቅቱ ከታሠሩት 20ሺህ ያህሉ በዚያዉ ዓመት ቢለቀቁም ቀሪዎቹ ሲንገላቱ እንደነበር ዘርዝረዋል። በመቶሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችም በዚሁ ዓመት መፈናቀላቸዉንም አብራርተዋል።

ከዚህም ሌላ አቶ ፍሰሀ በተጠቀሰዉ ዓመት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያትም ሆነ በፀረ ሽብር አዋጁ የተከሰሱ ሰዎች ማሰቃየት እንደተፈጸመባቸዉም አምነስቲ በዘገባዉ በዝርዝር ማዉጣቱንም አመልክተዋል።

ምንም እንኳን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተለያየ መልኩ መፈጸማቸዉን ተጎጂዎች አቤት ቢሉም ተገቢ የሆነ ምርመራ ተካሂዶ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በተጠያቂነት ወደ ሕግ እንዳልቀረቡ ነዉ የአምነስቲ ዘገባ የሚያመለክተዉ። አቶ ፍሰሃም ይህንኑ ያጠናክራሉ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የነበረዉን ጨምሮ የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ይዞታ እንደሚከታተል ያመለከቱት የድርጅቱ የምሥራቅ አፍሪቃ ተመራማሪ፤ አሁን በቅርቡ የሚታዩት የመብት ይዞታዎች በፊት ከነበረዉ ብዙም እንደማይለዩ ሳይገልፁ አላለፉም። እጅግ አሳሳቢ የሆነ ነው ያሉትንም እንዲህ ጠቅሰዋል።

Äthiopien Flüchtlinge vor ethnischer Gewalt

ተፈናቃይ የኦሮሞ ተወላጆች

አቶ ፍሰሀ አክለውም መንግሥት የተወሰኑ የሕሊና እስረኞችን ፈትቶ እና የተወሰኑ ማሻሻያዎችን አደርጋለሁ ባለበት ጊዜ፤ የሰብዓዊ መብትን በተለያየ መልኩ የሚገድብ የአስቸኳይ ጊዜ በሀገሪቱ ዳግም መታወጁ አምነስቲን እንደሚያሳስበው አመልክተዋል።

የአምነስቲን ዘገባ አስመልክቶ በዋትስ አፕ ከደረሰን  አስተያየት መካከል፤ «የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ ብሎም እየባሰበት ሔደ እንጅ ምንም መሻሻል አልተስተዋለም እንደ ቆሎ እየቆነጠሩ ሀያ እና ሰላሳ የህሊና እና የፓለቲካ እስረኞችን ከዕስር እየለቀቁ በሺ የሚቆጠሩ ንፁሀን ኢትዮጵያዉያን ቀን ከሌት ያግዛሉ» የሚለው አንዱ ነው። በፌስ ቡክ ገጻችን ላይ ደግሞ ፒተር በሚል ስም፤ «ይህ መንግሥት የሚፈጽመውን ዘርዝረን አንዘልቀውም የተደበቁ ብዙ ነገሮች አሉ» ሲሉ፤ ታየ ምሳሌ የተባሉ ደግሞ «አንድ ቀን መጠየቃቸዉ አይቀርም» የሚል አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። ሙሉቀን ደግሞ «ዝምታ ነው መልሴ ምን ይባላል ሆድ ይፍጀው» ብለዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic