የኢትዮጵያ ምርጫ ዉጤትና ፖለቲካዊ ጉዞ | ኢትዮጵያ | DW | 31.05.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ምርጫ ዉጤትና ፖለቲካዊ ጉዞ

የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንደሚከተለዉ አለም ተቃዋሚዎችን በምርጫ አወዳድሮ-በአሐዳዊ ፓርቲ እንደሚገዙት ኮሚንስት አንባገነኖች-በ99.6 ድምፅ ማሸነፉን አሳወጀ።አዲስ አበቦችም ተሠለፉ።

የኢትዮጵያ ምርጫ ዉጤትና ፖለቲካዊ ጉዞ

31 05 10 የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፁን ሰጥቶ በዉጤቱ በርግጥ ተገረመ።የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪ-አባላት ደነገጡ።ገዢዉ ፓርቲ በድል ፈነደቀ።አዲስ አበቦች ለድሉ ደስታ በሰልፍ ዘፈኑ።ፈከሩም።የዉጪም-የዉስጥም ወገኖች የሚሉትን አሉ።ግንቦትም ከስድስት ቀናት በሕዋላ-አዲዮስ እስካመት። ይሒድ። አስገራሚ-አስደንጋጩ፣ አስፈንዳቂ-አሰላፊ ክስተት የኢትጵያን ፖለቲካዊ ጉዞ ወደፊት ከማራመዱ ድምቀት ይልቅ የኋሊት የማሾሩ ፅልመት፣ ሽቅብ ከማሳደጉ ተስፋ ይብስ ቁልቁል የመድፈቁ ቅጭትን ማግዘፉ እንጂ ቀሪዉ ሥጋት።ኢትዮጵያ ወዴት? ለምን-እና እንዴት? ምሑር ጠይቀናል-ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ። በሳባዎች ፊደል፣ በአክሱም-ላሊበሎችች ጥበብ ስልጣኔ በአለም የመደነቋን ያሕል አለም ሲያድግ ሲሰለጥን በመጫጫት-መቆርቆዟ በአለም ተንቃለች።

Wahlkampf Äthiopien 2010

ጠሚ መለስ የምርጡኝ ዘመቻ

የሠለጠነ የናቃትን ሐያል አለም ሐይል ደቁሳ ነፃነትዋን በማስከበሯ ከመፈራት መከበሯ እኩል በድሕነት ችግር-ችጋር ለዘመናት መዳከሯ አዋርዷታል።የተለያየ እምነት፣ ቋንቋ ባሕል ተከታዮችን አቻችላ በማኖሯ ብዙዎች ያወድሷታል፣ በፖለቲካዊ ዉዝግብ ጦርነት በመጥፋት መዉደሟ ይሳለቁባታል። በተቃርኖ ልዩ ታሪክ የበለፀገችዉ ሐገር በቅርቡ ዘመንም አለም ብዙ የማያዉቃቸዉን ሁለት ታሪኮችን ሰራች።ሰሜናዊ ግዛቴ-ትለዉ ወይም ይባልላት የነበረዉን ክፍለ-ግዛት ነፃነት ፈቀደች።የዛሬ-አስራ-ዘጠኝ አመት ሥልጣን የያዘዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ኢሕአዴግ የኤርትራን ነፃነት ለመፍቀዱ ሰበብ ያደረገዉ ለኢትዮጵያ ሠላም ይበጃል-የሚል ነበር። የአረብ-እስራኤሎችን ግጭት ጦርነት ለማስወገድ አሜሪካኖች «መሬት ለሰላም» ብሎ መርሕን ሰበኩት እንጂ ገቢር አላደረጉትም።የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል ብሎ መርሕን ጆሴፍ ስታሊን ሲናገሩት የያኔዉን አለም ጉድ አሰኝተዉ ነበር።ስታሊን አሉት እንጂ አላደረጉትም።ወደ ሰማንያ የሚገመቱ ብሔር ብሔረሰቦችን አቻችላ በማኖሯ አለምን የምታስቀናዉ ኢትዮጵያ ግን ስታሊን ከማለት ባለፍ-ሊያደርጉ ያልቃጡትን በሕገ-መንግሥቷ አፀደቀች። ለኢትዮጵያ ሁለት አዳዲስ ታሪኮችን ያስመዘገበዉ ኢሕአዲግ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከመባል ባለፍ ላልተደረገባት ኢትዮጵያ አነሰም በዛ በማስተዋወቅ የመጀመሪያዉ ፓለቲካዊ ተቋም ነዉ።ዘንድሮ በአስራ-ዘጠነኛ አመቱ ደግሞ ሌላ ታሪክ ሠራ።የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንደሚከተለዉ አለም ተቃዋሚዎችን በምርጫ አወዳድሮ-በአሐዳዊ ፓርቲ እንደሚገዙት ኮሚንስት አንባገነኖች-በ99.6 ድምፅ ማሸነፉን አሳወጀ።አዲስ አበቦችም ተሠለፉ። በኮርኔል ዩኒቨርስቲ-ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪቃ ጥናትና ምርምር ማዕከል ባልደረባ ፕሮፌሰር አየለ በከሬ እንደሚሉት ምርጫ፥ ዉጤት፥ ሠልፍ መፈክሮ-ኢትዮጵያ ወደ አሐዳዊ አገዛዝ የመመለሷ ምልክት ሊሆንም-ላይሆንም ይችላል። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዞ ዛሬም አወዛጋቢ-አነጋጋሪ ሲብስ ደግሞ አሳሳቢ ነዉ።እንደ 1953ቱ፥ እንደ 1966ቱ፥ እንደ 1981ዱ፥ እንደ 1983ቱ እንደ 1997ቱ ሁሉ አቅጣጫዉ የሚያሳክረዉን ይሕን ጎዞ ወጥ መስመር ለማስያዝ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፍ የሌሎችንም አስተዋፅኦ ይጠይቃል።በፕሮፌሰር አየለ አገላለፅ ጉዳዩ ብሔራዊ ነዉ።

Äthiopien / Meles Zenawi / Wahlplakat

የወደፊቱም ጠሚ

ባለፈዉ አመት ሐምሌ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጋነን ሲጎበኙ የታሪክ ተመራማሪዉና የፖለቲካ ሐያሲዉ ፕሮፌሰር አየለ በከሬ አንድ መጣጥፍ ፅፈዉ ነበር።የጋናን ፖለቲካዊ ሥርዓት የሚነካካዉ ፅሁፋቸዉ አለማ አስተምሕሮቱ ነበር።ኢትዮጵያ ምን ትማር ይሆን? መልስ አላቸዉ። የሰወስት ሺሕ ዘመን የሥልጣኔ፥የጥበብ፥ የነፀነት ታሪክ አላት፥ ግን ደሐ ነች።-የመረዳዳት፥ አብሮ የመኖር ሥር የሰደደ ባሕል ባለቤት ናት ግን ለፖለቲካዊ መቻቻል ግን ዛሬም በርግጥ እንግዳ ናት።ኢትዮጵያ።ከሐምሳ አመት ያልበለጠ ዘመናይ የነፃነት ታሪክ ካላቸዉ አፍሪቃዉያን እንኳን መማር አልቻለችም ወይም አልፈቀደችም።ተስፋዉ ፕሮፌሰር አየለ እንዳሉት በርግጥ ጥሩ ነዉ።ግን እስከ መቼ?-ፕሮፌሰር አየለ በከሬን አመሰግናለሁ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ-ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic