የኢትዮጵያ ማምረቻ ዘርፍ ካለፈው ምን ይማራል? | ኤኮኖሚ | DW | 22.04.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያ ማምረቻ ዘርፍ ካለፈው ምን ይማራል?

ለአስር አመታት በተነደፈው የኢትዮጵያ መንግሥት የልማት ዕቅድ መሠረት እስከ 2017 ባሉት አመታት የግብርና ምርቶችን በጥሬ ዕቃነት ለሚጠቀሙ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ትኩረት ይሰጣል። ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም ባለው የዕቅዱ ሁለተኛ የትግበራ ዘመን "ከፍተኛ ካፒታልና የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደሚጠይቁ የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፎች" ፊቱን ያዞራል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:25

ከኤኮኖሚውዓለም፦የማምረቻው ዘርፍ ካለፈው ምን ይማራል?

በኢትዮጵያ መንግሥት የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ መሠረት የማምረቻው ዘርፍ እስከ 2017 ዓ.ም. በተለይ በአስራ ሁለት ዘርፎች ላይ ያተኩራል። ዕቅዱ እንደሚያሳየው በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ይኸው ዘርፍ "የግብርና ምርቶችን በጥሬ ዕቃነት በሚጠቀም ማኑፋክቸሪንግ ላይ በማተኮር አስተማማኝ የኢንዱስትሪ መሠረት ለመገንባት የሚሰራ ይሆናል።" የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ ቆዳ እና የቆዳ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት፣ መሠረታዊ ኬሚካል እና የኬሚካል ውጤቶች በእነዚሁ አመታት ትኩረት ከሚደረግባቸው ዘርፎች መካከል ይገኙበታል።

ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም ባለው የዕቅዱ ሁለተኛ የትግበራ ዘመን "ከፍተኛ ካፒታልና የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደሚጠይቁ የማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፎች በመሸጋገር ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚን ለመገንባት ጥረት" እንደሚደረግ በሰነዱ ሰፍሯል። የትራንስፖርት መሣሪያዎች፣ የማምረቻ ማሽኖች፣ የሕክምና ዕቃዎች ማምረትን ጨምሮ ዘጠኝ ዘርፎች ለሁለተኛው ምዕራፍ የተለዩ ናቸው።

ኢትዮጵያ ከኋላ ቀር የግብርና ዘርፍ በመላቀቅ ለኤኮኖሚው መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተስፋ በተጣለበት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከ2003 እስከ 2012 ዓ.ም. ተመርታለች። በጀርመን የዕድገት ኢንስቲትዩት (German Development Institute) የኤኮኖሚ ተመራማሪው ዶክተር ካስፐር ፍሮህሊክ ዕቅዱ የኢትዮጵያ መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ከድህነት ቅነሳ ወደ መዋቅራዊ ሽግግር ፊቱን ያዞረበት እንደነበር ያስታውሳሉ።

Äthiopien Omo Kuraz Zuckerfabrik

በዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሊገነቡ ከተጀመሩ መካከል የስኳር እና የማዳበሪያ ማምረቻዎች ይገኙበታል። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት ማምረቻዎቹን በታቀደላቸው ጊዜ እና በጀት ለማጠናቀቅ ተቸግሮ ታይቷል።

ዶክተር ካስፐር ፍሮህሊክ "ከዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ በፊት ተግባራዊ ይደረግ የነበረው ፖሊሲ በዋናነት በድሕነት ቅነሳ ላይ ያተኮረ ነበር። የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መዋቅራዊ የኤኮኖሚ ሽግግርን ያስተዋወቀ ነው። ዓላማው መሠረቱን በእርሻው ላይ ያደረገውን በማምረቻው ዘርፍ ወደ ሚመራ ኤኮኖሚ ለመቀየር ነበር" ሲሉ ያስረዳሉ።

ለኢትዮጵያ ልሒቃን ኤኮኖሚያቸውን ከእርሻ ጥገኝነት አላቀው ዛሬ ያደገ የሚባል ኤኮኖሚያዊ መዋቅር የገነቡት የደቡብ እስያ አገራት አርአያ ነበሩ። የልማታዊ መንግሥትን መንገድ ይከተል በነበረው የቀድሞው ኢሕአዴግ ሰነዶች እና በባለሥልጣናቱ አንደበት እነደቡብ ኮሪያ ለዚህ በተደጋጋሚ በምሳሌነት ሲጠቀሱ ቆይተዋል።

የኤኮኖሚ "መዋቅራዊ ሽግግር ሰዎች እና ካፒታልን ከግብርና ወደ ማምረቻው ዘርፍ ወይም በበለጸጉት አገራት እንደታየው ወደ አገልግሎት ዘርፍ ማንቀሳቀስ ማለት ነው። የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተወሰነውን በማሳካት ረገድ ጥሩ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ግን ስኬታማ አልነበረም" የሚሉት ዶክተር ካስፐር ፍሮህሊክ መዋቅራዊ ሽግግር ሲደረግ ሰዎች የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። ባለሙያው "ሰዎች እና ካፒታልን ማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን በአንድ ጎኑ የበለጠ ምርታማ ማድርግ ማለት ጭምር ነው። ሌላው እጅግ ጠቃሚ ነጥብ የማምረቻውን ዘርፍ ስኬታማ ማድረግ ካስፈለገ ከግብርናው ዘርፍ ጋር አንዳች ትሥሥር ሊኖረው ይገባል" ሲሉ ያክላሉ።  

ከ2003 እስከ  2012 ዓ.ም ባሉት አመታት የማምረቻው ዘርፍ ከ13 እስከ 15 በመቶ የሚደርስ ዕድገት ነበረው። የኢትዮጵያ መንግሥት የአስር አመታት የልማት ዕቅድ "የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ከማሳካት አንጻር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለፉት ዓመታት ዕድገት ያስመዘገበ ቢሆንም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ እምብዛም ለውጥ ሳያሳይ በ2003 በጀት ዓመት ከነበረበት 4.5 በመቶ በ2012 በጀት ዓመት 6.9 በመቶ" ሆኖ መዝለቁን ያትታል።

Äthiopien Der Industriepark Adama

የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻው ዘርፍ የውጭ ባለወረቶችን ትኩረት በመሳብ ረገድ ስኬታማ ሆኗል። በተለይ አዳማን በመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሥራ የጀመሩ የውጭ ኩባንያዎች በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።

"ፖሊሲው በተወሰነ መንገድ ስኬታማ ነው። የኢትዮጵያ ዕድገት በአፍሪካም ሆነ ከሌሎች የዓለም አገሮች ሲወዳደር አስደናቂ ነበር። ነገር ግን ያ ዕድገት ጊዜያዊ እና በተወሰነ መልኩ በብቁ የተረጋገጠ አልነበረም። ፖሊሲው ለኢኖቬሽን ትኩረት ሳይሰጥ ቀርቷል። ምርታማነትን ለማሳደግ እና ከግብርና ውጤቶች ኮምፒውተርን ወደ መሳሰሉት ውስብስብ ምርቶች ለመሸጋገር የሚያስፈልገው ደግሞ ይኸ ነው። ይኸን ፖሊሲው በበቂ ኹኔታ ትኩረት የሰጠው አይመስለኝም" ሲሉ በቀደመው የኢትዮጵያ ፖሊሲ ላይ ጠለቅ ያለ ትንታኔ የሠሩት የኤኮኖሚ ጥናት ባለሙያው አተያያቸውን አስረድተዋል።   

የኢትዮጵያ መንግሥት የልማት ዕቅድ በቀረበበት ሰነድ መሠረት ባለፉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው በየዓመቱ በአማካይ 357 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ አግኝታለች። "ምንም እንኳ ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ያለው ድርሻ ዝቅተኛ ቢሆንም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ ገቢ ከሌሎች ዘርፎች አንጻር ሲታይ ፈጠን ያለ ዕድገት አሳይቷል"ይላል ይኸው የኢትዮጵያ መንግሥት የ10 አመታት የልማት ዕቅድ የቀረበበት ሰነድ። ለዚህ  ለዘርፉ ከተሰጡ የፖሊሲ ድጋፎች በተጨማሪ የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ያሳዩት አንጻራዊ ተወዳዳሪነት እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ያሳየው መነቃቃት አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው ተገልጿል።

Äthiopien Der Industriepark Adama

ካስፐር ፍሮህሊክ "ለአመታት የሥራ ዕድል ብቻ ሲፈጥር ቆይቶ ያ የውጭ ኩባንያ ጥሎ ቢወጣ ምን ይፈጠራል?  እነዚህ ኩባንያዎች ለተቀጣሪዎቻቸው ሊያጋሩት የሚችሉት ከፍተኛ የምርታማነት ደረጃ እና እውቀት አላቸው። ያ እውቀት ካልተሸጋገረ ወይም የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በማናቸውም መንገድ ያን መፍጠር ካልቻሉ ፖሊሲው በረዥም ጊዜ ይኸ ነው የሚባል ነገር አላመጣም ማለት ነው" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ስኬታማ ከሆነችባቸው መካከል ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ኢንዱስትሪዎችን ቀልብ መሳብ ይገኝበታል። የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻው ዘርፍ ከፍተኛ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ስቧል። ይኸ ደግሞ ለሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ ደሞዝ ያገኛሉ፤ አዳዲስ ክህሎቶች ለመማር የተወሰነ ችሎታ አላቸው" የሚሉት የኤኮኖሚ ጥናት ባለሙያ መልሰው "በረዥም ጊዜ ምን ይፈጠራል?" የሚለው ጥያቄ ያነሳሉ።  "ለአመታት የሥራ ዕድል ብቻ ሲፈጥር ቆይቶ ያ የውጭ ኩባንያ ጥሎ ቢወጣ ምን ይፈጠራል?  እነዚህ ኩባንያዎች ለተቀጣሪዎቻቸው ሊያጋሩት የሚችሉት ከፍተኛ የምርታማነት ደረጃ እና እውቀት አላቸው። ያ እውቀት ካልተሸጋገረ ወይም የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በማናቸውም መንገድ ያን መፍጠር ካልቻሉ ፖሊሲው በረዥም ጊዜ ይኸ ነው የሚባል ነገር አላመጣም ማለት ነው"ብለዋል።

ዶክተር ካስፐር ፍሮህሊክ እንደሚሉት "ከውጪዎቹ ወደ አገር ውስጥ ኩባንያዎች የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግበት፣ የውጪ ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን በምርት ሒደታቸው ላይ የሚያግዙበት መንገድ ቢመቻች ኖሮ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረው ነበር።"

"በርካታ የፖሊሲ አውጪዎች የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዴት መደገፍ እንዳለባቸው በመለየት ረገድ ችግሮች እንደነበሩባቸው ተረድቻለሁ።  በዓለም ባንክ ሪፖርቶች የሚጠቀሱ ፋይናንስ እና ብድር ማግኘትን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመመለስ ፈታኝ ቢሆኑም እንኳ ለመረዳት ቀላል ናቸው። የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዴት ማበረታታት ይቻላል? የሚሉ ጉዳዮች ግን ከባድ ናቸው። ከዘርፍ ዘርፍ ጭምር ይለያያሉ። የኢትዮጵያ ፖሊሲ አውጪዎችን ለመርዳት ቻይና እና ሕንድን ከመሳሰሉ በማደግ ላይ ከሚገኙ ኤኮኖሚዎች እና ከሌሎችም እውቀትን ማሸጋገር የሚቻልበት ዕድል አለ ብዬ አስባለሁ።" የሚሉት ዶክተር ካስፐር ፍሮህሊክ የግሉ ዘርፍ በተለይ በእውቀት እና ቴክኖሊጂ ረገድ ሊጫወተው የሚገባ ከፍ ያለ ሚና መኖሩንም ጠቅሰዋል። በባለሙያው አባባል የኢትዮጵያ ተቋማት የበለጠ ምርታማ የሚያደርጋቸውን እና በርከት ላሉ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያግዛቸውን ከፍ ያለ እውቀት ከውጪ ኩባንያዎች መጋራት አለባቸው።

እሸቴ በቀለ

 

Audios and videos on the topic