የኢትዮጵያ መንግስት የእስር ርምጃዎች | አፍሪቃ | DW | 02.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የኢትዮጵያ መንግስት የእስር ርምጃዎች

ካለፈዉ ሳምንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሌሎችንም ግለሰቦች መታሰራቸው ተዘግቧል። የፌዴራል ፖሊስ ከህብረተሰቡ ደርሶኛል ካለው 260 የሙስና ጥቆማዎች ጋር በተያያዘ 130 የመንግሥት አመራር እና ሌሎች ሠራተኞችን ማሰሩን ይፋ አደርጓል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:22
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:22 ደቂቃ

የእስር ርምጃዎች

በተመሰሳይ  በደቡብ ክልል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን «በሙስና ወንጀል መሳተፋቸው የተረጋገጠ 198 ግለሰቦች በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ» ተደርገዋል ማለቱን የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል። ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት)ም «ችግር ፈጥረዋል በተባሉ ከ640 በላይ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዱም» ዘገባዎቹ አስነብበዋል።

 
በፌደራልና በክልል መንግሥታት በመወሰድ ላይ ስላሉት ስለነዚህ እርምጃዎች ከመንግስት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት በስልክ ማብራርያ ጠይቀን፣ ቀጠሮም ተሰጥቶን ነበር። ሆኖም በቀጠሮ ሰዓት ደጋግመን ብንደውልም ሊገኙልን አልቻሉም። የአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተያየት ግን አግኝተናል።

 
የሰበታ ነዋሪ ፣ አቶ ዩሱፍ ኑርዬ መንግስት ጥልቅ ተሃድሶ አደረግኩ ካለ በኋላ የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠሩ አመራሮችንና «በሙስና የተዘፈቁ» ያላቸው ግለሰቦች ላይ ርምጃ እየወሰደ መሆኑን የሚያመለከቱ ዘገባዎችን ስከታተል ነበር ይላሉ። ተወሰደ የተባለዉ ርምጃ ግን መገናኛ ብዙሀን «እንደሚያጮሁት አይደለም» ብለዋል።

የመልካም አስተዳደር ጉድለትንና ሙስናን በመንግስት አመራሮችና ሌሎች ግለሰቦች ላይ ማሳበብ ትክክለኛዉ መፍትሄ አይደለም የሚሉት ደግሞ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉት ሌላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸዉ።

ስለ እርምጃው በተመለከተ በዶቼ ቬለ የፌስቡክ  ድረ -ገጽ ላይ አስተያየታቸዉን ከሰጡት ዉስጥ «የስርዓቱ ቁንጮ ህውሀት እና  የዘረፋ ድርጅቶች እስካሉ ድረስ የሚሻሻል ነገር የለም። አሁን ተያዙ የሚባሉት እኮ ትናንሽ አሳዎች ናቸው፣ ዋናዎቹ ቱባ ሌቦች አይነኩም» ሲሉ አስተያየታቸዉን የሰነዘሩ አሉ። ሌሎች ደግሞ «ያንድ ሠሞን ወሬ ሆኖ እንዳይቀር ጠንከር ያለ ህጋዊ እርምጃ ሊወሠድባቸዉ ይገባል፣ ሌሎች ከዚህ መማር አለባቸዉ» ያሉም ይገኙበታል።

መርጋ ዮናስ

ሕሩት መለሰ   
      


 

Audios and videos on the topic