የኢትዮጵያ መንግሥት እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች በጀርመን | ኢትዮጵያ | DW | 04.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች በጀርመን

በኢትዮጵያ ካለፉት ሥርዓቶች የተሻለ ከፍተኛ ተስፋ ሰጭ ለውጥ ቢታይም ቀላል የማይባል ተግዳሮቶችም ማጋጠማቸውን ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ገለጹ። ጀርመን መንግሥት ባቀረበው የስራ ጉብኝት ግብዣ የተካፈሉት ፕሮፌሰር መራራ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ የመንግስት ተወካዮች ያሉበት ቡድኑ አባል በመሆን በርሊን እና ፍራንክፈርት ከተሞችን ጎብኝተዋል።

በጀርመን መንግሥት የስራ ጉብኝት ግብዣ መሰረት በኢትዮጵያ ታሪካዊ የተባለ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን የመንግሥት ተወካዮችን እና ሌሎች  የልዩ ልዩ ተቋማት ባለሙያዎችን ያካተተው የጋራ የልዑካን ቡድን ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ከአገሪቱ የመንግሥት አመራሮች እና ከትላልቆቹ ፓርቲዎች ክርስቲያን ሶሻል ህብረት ክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት እና የጥምሩ መንግሥት አካል ከሆነው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ አባላት ጋር በኢትዮጵያ በሚካሄደው ለውጥ እና ተግዳሮቶቹ ዙሪያ ውይይት እና የልምድ ልውውጥ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። የልዑካን ቡድኑ ባለፉት 4 ቀናት ስለ 16ቱ የጀርመን ፌደራል ግዛት አስተዳደሮች ስልጣን እና ሃላፊነት ገለጻ የተደረገለት ሲሆን በጀርመን የተለያዩ ተቋማዊ አደረጃጀቶችንም በመጎብኘት
መንግሥታዊ የአስተዳደር ሥርዓቱ የተገነባበትን ዲሞክራሲያዊ ሂደት በሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት በመገኘት ልምድ ቀስሟል ።  ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የአርበኞች ግንቦት7 ድርጅት ዋና አመራር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ተጠሪ አቶ ሌንጮ ለታ እንዲሁም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ከመንግሥት በኩልም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የህግ ባለሙያዎች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች በስራ ጉኝቱ ተካፋይ ሆነዋል።   የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በተለይ ለ " DW " እንደገለጹት እንዲህ ዓይነቱ መንግስትንም ተፎካካሪ ፓርቲዎችንም በጋራ ያሳተፈ የስራ ጉብኝት አሁን በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የለውጥ ሂደት ለመገምገም እና ተግዳሮቶቹንም ለመቅረፍ የሚያግዙ ድጋፎችን ለማግኘት የሚረዳ ሲሆን በተለይም የጀርመን መንግሥት የዴሞክራሲያዊ ተቋሞቹን የገነባበትን ሥልት መቅሰሙ በኢትዮጵያም የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ተመሳሳይ ተቋማትን ለማጠናከር የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል ።
ፕሮፌሰር መራራ መንግሥት በእስር ላይ የሚገኙ የተፎካካሪ ድርጅቶችን አባላት መፍታቱ በውጭ የነበሩ የተቃዋሚ ኃይላትን በሰላም አገር ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በመጋበዝ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋቱ እንዲሁም የምርጫ ቦርዱን ህግ ዳግም መከለሱ እና ጽህፈት ቤቱንም በአዲስ መልክ ማዋቀሩ የጸረ ሽብር እና የሲቪክ ማህበራት ህግጋትን መሰረዙ እና ማሻሻሉን ጨምሮ ሁሉም ተፎካካሪዎች የተሳተፉበትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የአሰራር ስምምነት ቃል ኪዳን ሰነድ ማዘጋጀቱ አወዛጋቢ የነበሩት የጸረ ሽብር እና የሲቭል ማህበራት ህጎች መሻሻላቸው እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት የጀመረው ጉዞ በበጎ ጎን የሚጠቀሱ ተስፋ ሰጭ ናቸው ብለዋል። ያም ቢሆን ለውጡ ህዝቡን ካላማከለ ውሎ አድሮ ተስፋ ሊያስቆርጥ እና ዋጋም ሊያስከፍል ይችላል የሚሉት ፕሮፌሰር መራራ በአሁኑ ጉብኝታችንም በኢትዮጵያ የሚካሄደው ለውጥ ተስፋዎቹ እና ተግዳሮቶቹንም ለጀርመን መንግሥት እናስረዳለን ሲሉም ገልጸዋል ። 
የኢትዮጵያ መንግሥት በጀመረው የለውጥ ሂደት አያሌ ስኬት አስመዝግቧል የመባሉን ያህል በተለይም በውጭ የትጥቅ ትግል ያካሂዱ ከነበሩ አንዳንድ ድርጅቶች ጋር ያካሄደውን የሰላም ስምምነት የተለያዩ ወገኖች ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ለበርካታ ዜጎች መፈናቀል ግድያ በጦር መሳሪያ የተደራጀ የመንግሥት ተቋማት ዘረፋ እና ሰላም እጦት ጭምር ምክንያት በመሆናቸው የመንግሥትን አመራር አድሎአዊነት የተሞላበት በማለት ሲተቹ ቆይተዋል። ፕሮፌሰር መራራ ጉዲናም እንደገለጹት ኢትዮጵያ ካለፉት ሥርዓቶች የተሻለ በሚባል የለውጥ ሂደት ውስጥ  የምትገኝ ቢሆንም አሁንም የአገሪቱን ህልውና ፈታኝ የሆኑ ከፍተኛ ተግዳሮቶችም ገጥመዋታል ብለዋል። አንዱ በአገር ውስጥ በሚቀሰቀስ የብሄሮች ግጭት ሳቢያ መቆሚያ ያጣው የሕዝቦች መፈናቀል ሲሆን ሌላው ዛሬም ድረስ ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ያልፈቱ የተቃዋሚ ኃይላት እንቅስቃሴ በጊዜ የጋራ መግባባት ተደርጎበት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መላ ካልተበጀለት  ውሎ አድሮ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ይላሉ ፕሮፌሰር መራራ።
በኢትዮጵያ በለውጡ ሂደት ከተጋረጡት አያሌ ተግዳሮቶች ሌላ ተቃዋሚዎችም ብንሆን ሊያስማሙን የሚችሉ የጋራ አጀንዳዎችን አለመቅረጻችን ችግሩን አባብሶታል ያሉት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ለውጡን በዋናነት ያመጣው ወጣት ኃይል ተምሮና ሰርቶ ራሱን እና አገሩን ለመለወጥ የሚችልበት ሁኔታ ሊመቻች እንደሚገባ በመግለጽ በእጃችን የገባው ለውጥ ከእጃችን እንዳይወጣ ሁላችንም የቤት ስራችንን እንስራ ሲሉም አስገንዝበዋል። የልዑካን ቡድኑ በጀርመን የሚያደርገውን የ 5 ቀናት የሥራ ጉብኝት ነገ አርብ ያጠናቅቃል።

እንዳልካቸው ፈቃደ


አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሠ 
 

Audios and videos on the topic