የኢትዮጵያ መንግሥት፧ በኦጋዴን አደጋ በመጣል የተጠረጠሩ አማጽያንን ያዝሁ ማለቱ፧ | ኢትዮጵያ | DW | 31.03.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግሥት፧ በኦጋዴን አደጋ በመጣል የተጠረጠሩ አማጽያንን ያዝሁ ማለቱ፧

ባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር፧ ቻይናውያንና ኢትዮጵያውያን፧ ነዳጅ ፍለጋ ተሠማርተውበት በነበረ ጣቢያ፧ አደጋ በመጣል፧ 74 ሰዎች፧ 9 ቻይናውያን ጭምር መገደላቸው፧ የሚታወስ ነው።

ባለፈው ዓመት በኦጋዴን ከቆሰሉት ቻይናውያን መካከል ከፊሉ ለህክምና በ «አምቡላንስ« ወደ አ.አ. ሲወሰዱ፧

ባለፈው ዓመት በኦጋዴን ከቆሰሉት ቻይናውያን መካከል ከፊሉ ለህክምና በ «አምቡላንስ« ወደ አ.አ. ሲወሰዱ፧


የኢትዮጵያ መንግሥት፧ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር አባላት ናቸው የተባሉ፧ በተጠቀሰው አደጋ የመጣል እርምጃ ሳይሳተፉ እንዳልቀሩ 8 ሰዎች መያዛቸውን አስታውቋል። በለንደን፧ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ድርጅት ቃል አቀባይ፧ የተያዙት ሰዎች የግንባሩ አባላት አይደሉም ይላሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት፧ በኦጋዴን፧ የነዳጅ ፍለጋ ይካሄድበት በነበረ ጣቢያ አደጋ ጥለው 74 ሰዎች በመግደል የተጠረጠሩ 8 ሰዎች መያዙን አስታውቋል። ተጠርጣሪዎቹ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር አባላት መሆናቸው ነው የተነገረው። ስለመግለጫው የተጠቀሰው ግንባር አስተያየት ምን እንደሆነ በለንደን የሚገኙትን የ ONLF ቃል አቀባይ አቶ አብድራህማን ማህዲን ጠይቀናቸው ነበር።
«የፈጠራ ታሪክ ነው። ከእውነት የራቀ ነው። ለጦር እርምጃዎች ኀላፊ የሆነው የኦጋዴን ነጻ አውጭ ጦር፧ ኃይሉን አስተባብሮ ነው የሚገኘው። በጥቃቱ፧ የተሳተፉ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር አባላት የሆኑ አንዳቸውም አልተያዙም። ለፕሮፖጋንዳና ለመገናኛ ብዙኃን ሲሉ የፈሩት ታሪክ ነው፧ እውን የለበትም። እውነታው፧ በሺ የሚቆጠሩ የኦጋዴን ተወላጆችን ይዘው አሥረዋል። ማንኛውም ሰው ተጠርጣሪ ነው። በጥርጣሬ የያዙትን የኦጋዴን ሰው ሁሉ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ድርጅት አባል ነው ይሉታል። ይህ ነው የሚታየው። ሐቅ። ከሶማልያ ለጉብኝት የሚመጣ ሰው ሁሉ እየተያዘ ተጠርጣሪ ነው፧ ነው የሚባለው። ባለፉት ስድስት ወራት ይህን እያደረጉ ነው።«
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚገባውን ያህል እያደረገ አለመሆኑ ይነገራል። ምንድን ነው መሆን አለበት የሚሉት?
«እንደእውነቱ ከሆነ፧ አንዳንድ የዓለም አቀፉ ማኅበረ-ሰብ አባላት፧ የሚፈጸመውን ወንጀል ሁሉ፧ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚካሄደውን ONLF ነው ያደረገው በሚል አሳሳች መግለጫ አይተባበሩም። ኦጋዴኖችና ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ በመላ 3 መንገዶች ናቸው መፍትኄ የሚያስገኙላቸው።
በመጀመሪያ ዓለም-አቀፉ ኅብረተሰብ ጣልቃ በመግባት፧ በኦጋዴንና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚካሄደውን «የጅምላ ጭፍጨፋ« ማስቆም ይኖርበታል።
ሁለተኛ፧ የኢትዮጵያ መንግሥት፧ በዓለም አቀፍ ህግ ደንብ ተደራድሮ፧ ውዝግቡን፧ በኦጋዴን ህዝብና በአሁኑ የ«ወያኔ« አገዛዝ መካከል ያለውን ቅራኔ መፍታት ይጠበቅበታል።
ሦስተኛው ነጥብ፧ የኢትዮጵያ መንግሥት ያሁኑን ተግባሩን እንዲለውጥ ማስገደድና ይበልጥ ዴሞክራቲክ አስተዳደር እንዲያሠፍን ማስደረግ ነው። በዚህ መንገድ ብቻ ነው፧ በኢትዮጵያና በአፍሪቃ ቀንድ ሰላም ሊወርድ የሚችለው። እነዚህ ሦስት የመፍትኄ ነጥቦች ተቀባይነት ካላገኙ፧ ምንም ለውጥ አይመጣም።አምናለሁ፧ በአሁኑ ጊዜ፧ ኢትዮጵያ እጅግ ብርቲቱ ሥቃይ እየደረሰ ያለው። «አማሮች«፧ «ኦሮሞዎች«፧ ሌሎችም «ህዝቦች« እየተሠቃዩ እንደሚገኙ አምናለሁ። አንድ ነገር ካልሆነ በ«ወያኔ« አገዛዝ ሳቢያ በሶማልያም፧ በአፍሪቃ ቀንድ በመላ፧ ሥቃዩ ይቀጥላል።«
አቶ አብድረህማን ማህዲ፧ የኢትዮጵያ መንግሥት፧ በኃይል እርምጃ ዓላማውን ማራማዱን ካቆመ.፧ አስታራቂ ባለበት፧ ለመደራደርም ሆነ ለመነጋገር ዝግጁ ነን ሲሉም ገልጸዋል።