የኢትዮጵያ መለያው የሙዚቃ ቅኝት | ባህል | DW | 20.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የኢትዮጵያ መለያው የሙዚቃ ቅኝት

በአንዳንዶች ዘንድ እንደ “ኢትዮጵያ መለያ”  ይወሰዳል። ሌሎች ኢትዮጵያዊነትን ገላጭ ሲሉ ያሞካሹታል። የተወሰኑ ሙዚቀኞች ሀገርኛ ቀለሙን ይበልጥ ለማጎላት “የዶሮ ወጥ ቅኝት” ይሉታል - አንቺ ሆዬ የሙዚቃ ቅኝትን። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:18

ቅኝቱ ከመዝሙሮች እስከ አስፈሪ ፊልሞች ማጀቢያ ይውላል

ኩኩ ሰብስቤ አስናቀች ወርቁ የሺ ደመላሽ። እነዚህ የሶስት ዘመን ወካይ እንስት ድምጻውያን በአንድ የሙዚቃ ስልት የተቀነቀኑ የየራሳቸውን ሙዚቃዎች አዜመዋል። ኩኩ “ጉብልዬ” እያለች ስትጣራ አስናቀች በክራሯ ታጅባ “አቤት አቤት” ጥያቄዋን ለፈጣሪዋ አሰምታለች። የሺ በበኩሏ ኮከብ ስትል ታሞግሳለች። 

ሶስቱም ድምጻውያን የተጠቀሙበት ስልት በአንዳንዶች ዘንድ እንደ “ኢትዮጵያ መለያ” ይወሰዳል። ሌሎች ኢትዮጵያዊነትን ገላጭ ሲሉ ያሞካሹታል። የተወሰኑ ሙዚቀኞች ሀገርኛ ቀለሙን ይበልጥ ለማጎላት “የዶሮ ወጥ ቅኝት” ይሉታል - አንቺ ሆዬ የሙዚቃ ቅኝትን። 

ብሌን ዮሴፍ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሩቅ እና የሙዚቃ ባለሙያ ናት። አንቺ ሆዬ ቅኝትን ታስተዋውቃለች። ስልቱ ለመንፈሳዊ አገልግሎት እንደሚውል የምትናገረው ብሌን ለዚህም በምሳሌነት ዘለሰኛን ትጠቅሳለች። ወጣቱ ፒያኒስት ሳሙኤል ይርጋ የአንቺ ሆዬ ቅኝት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሚገባ አገልግሎት ላይ መዋሉን ይስማማል።

የሙዚቃ ባለሙያዋ አንቺ ሆዬ ከመንፈሳዊ ዜማዎችና መዝሙሮች ባሻገር በዓለማዊ ዘፈኖችም ብዙ ቦታ አለው ትላለች። ከኢትዮጵያዊ ሌሎች ቅኝቶች የሚለየውንም ታብራራለች። ብሌን የቅኝቱ አካሄድ ለሙዚቀኞች ከባድ እንደሆነ የታዘበችውን ተንተርሳ ትገልጻለች። ፒያኒስቱ ሳሙኤል አንቺ ሆዬ ለምን ከባድ ነው እንደሚባል ተጨማሪ ትንታኔ አለው። 

ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ የሙዚቃ ሰዎች አንቺ ሆዬ ቅኝትን ለመጫወት ይፈተናሉ። በኢትዮጵያውያም አጨዋወት እና የቅኝት አጠቃቀም ይገረማሉ። የቅኝቱ አካሄድ ይበልጥ ምቹ የሚሆነው ለአስፈሪ ፊልሞች ማጀቢያ መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያውያን ለተቃራኒ አገልግሎቶች መዋላቸው እንደሚያስደንቃቸው ብሌንም ሆነች ሳሙኤል ታዝበዋል። የውጭዎቹ ሰዎች የሚደመሙት እነርሱ ከሚያስቡት በተቃራኒ ለመፈንሳዊ ዜማዎች እና ለሰርግ ዘፈኖች በመዋሉ ነው።

ሳሙኤል በአንቺ ሆዬ ቅኝት ሙዚቃዎች ለመጫወት እንደማይከብደው ይናገራል። ጉዞ በተሰኘው አልበሙም በዚሁ ቅኝት ስር ያለ “ፊርማ እና ወረቀት” የተሰኘ ቅንብሩን አካትቷል። 

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ
 

Audios and videos on the topic