የኢትዮጵያ፤ ሌላ ሳምንት ሌላ ግድያ | ኢትዮጵያ | DW | 12.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ፤ ሌላ ሳምንት ሌላ ግድያ

የኢትዮጵያ መንግሥት የዩኒቨርስቲ መምሕር እና የአምደ መረብ ፀሐፊ ስዩም ተሾመን ጨምሮ ቁጥራቸዉ በዉል ያልተነገረ ወጣቶችን ማሰር የጀመረዉ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን አዲስ አበባ ዉስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብን ነፃነት መገደብ ሳይሆን ሰፊ ነፃነት እንዲሰጠዉ በጠየቁበት ዋዜማ፤ ዕለት እና ማግሥት ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:15

«ሥንት ሕዝብ ማለቅ አለበት?»- ዶ/ር ዲማ ነገዎ

ሕዝብ ለመብት ነፃነቱ መከበር ይጮኽባታል። አድማ ይመታባታል። የኃያል መንግስታት ትልቅ ዲፕሎማት ደም አፋሳሹን ተቃዉሞ ለማስቆም «ለሕዝብ ላቅ ያለ ነፃነት እንዲሰጥ» ይጠይቁላታል። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ የሚገዛበትን ሕግ የሚያፀድቀዉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ግን ድምር ይሳሳቱባታል። ቁጥር። የሕዝብን ደሕንነት የሐገርን ሠላም እንዲያስከብር ከሕዝብ ከሚሰበሰብ ቀረጥ ደሞዝ የሚከፈለዉ ጦር ሠራዊት መረጃ ይሳሳትባታል፤ ሰላማዊ ሰዎችን ይገድልባታል። ኢትዮጵያ። የተቃዉሞ-ግድያ አዙሪት ቁልቁል ይነዳታል። የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀዉስ መነሻ፤ የጥፋቱ ልክ ማጣቃሻ፤ መፍትሔዉ መድረሻችን ነዉ። 

ከምራብ ሸዋ አምቦ-እስከ ሰሜን ጎንደር ጎንደር፤ ከደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር እስከ ምሥራቅ ሸዋ ቢሾፍቱ (ወይም ደብረ ዘይት)፤ ከምዕራብ ሐረርጌ ዳሮለቡ-እስከ ባሌ ፤ ከሰሜን ወሎ ወልዲያ እስከ ጉጂ፤ ከምሥራቅ ሐረርጌ ጨለንቆ እስከ ምሥራቅ ወለጋ ነቀምት ሌሎችም በተቃዉሞ ግጭት ሲተራመሱ፤ ሟች ቁስለኛ ሥንቆጥር ከርመን ዘንድሮ አልን። ሶስትኛ ዓመት።

ቁጥር ወይም ድምር የሚያሳስታቸዉ አፈ ጉባኤ የሚመሩት ምክር ቤት ለሁለተኛ ጊዜ አፀደቀዉ የተባለዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ወዲሕ ደግሞ ነቀምት፤ ደምቢ ዶሎ፤ አምቦ እና አካባቢዎቿ የአዲሱ ዙር ግጭት፤ ግድያ ማዕከላት ሆኑ። ምዕራብ ሸዋዎች፤ ምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋዎች አልቅሰዉ፤ አርግደዉ ከሌ ሳያጥፉ-ነጌሌ ቦረናዎች አስከሬን-ቁስለኛ ይለቅሙ፤ ይቆጥሩ ገቡ። ቅዳሜ።

የዓይን ምስክሩ። የሠብአዊ መብት ተሟጋቹ። ከዚሕ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች ለደረሱ ጥፋቶች ተጠያቂ የሚባሉ ወገኖችን መንግስታቸዉ ለፍርድ እንደሚያቀርብ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተደጋጋሚ ቃል ገብተዉ ነበር። የመጨረሻዉን የሰማነዉ ባለፈዉ ታሕሳስ ነዉ።

የማጣራቱን ሒደት እና ዉጤት ሳንሰማ ቃል የገቡት ጠቅላይ ሚንስትር ሥልጣን ለቀቁ። ሁለተኛዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚያስፈፅመዉ የዕዝ ጣቢያ ወይም ኮማንድ ፖስት እንዳስታወቀዉ የሚያዘዉ ጦር ሲያንስ ዘጠኝ ሲበዛ አሥራ-አምስት የሞያሌ ነዋሪዎችን የገደለዉ ከተማይቱ ዉስጥ የኦነግ ታጣቂዎች ገብተዋል የሚል «የተሳሳተ መረጃ» ሥለደረሰዉ ነዉ። ተጠያቂ የሚባሉ የጦሩ አዛዦችና ባልደረቦች መታሰራቸዉንም ኮማንድ ፖስቱ አስታዉቋል። የሞያሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አስቻለዉ ዩሐንስ ግን ግድያዉ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ነዉ ይላሉ።

የስብሰብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ያሬድ ሐይለ ማርያም ደግሞ የኮማንድ ፖስቱን መግለጫ አጣጥለዉ ይነቅፉታል። የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ምክትል ሊቀመንበር እና የጥምረት ለኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶከተር ዲማ ነገዎም ስሕተት የሚባለዉን አይቀበሉትም። ዶከተር ዲማ እንደሚያምኑት  ሁለተኛዉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገዉ በኦሮሚያ መስተዳድር የሕዝብን ጥያቄ ለማስተናገድ ብቅ ብቅ ያሉ ባለሥልጣናትን ለመምታት፤ ሕዝቡንም ለማሸማቀቅ ነዉ።

በኪል-ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ የሕግ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አወል አሎ እንደሚሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕገ-መንግስታዊ መሠረት የለዉም። አቶ ያሬድ ሕገ-መንግስቱ የገዢዉን ግንባር በተለይም የሕወሓትን ሕልዉና ለማስከበር እየዋለ ነዉ ባይ ናቸዉ። የሞያሌዉ ግድያ፤ ዶከተር አወል እንደሚሉት ሕዝብን ከመግደል እና ተራፊዎችን ከማሸማቀቅ ዉጪ ሌላ መልዕክት የለዉም።

ዶከተር ዲማ የሞያሌዉ ዓይነት ግድያ ለኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የመጀመሪያዉ እንዳልሆነ ሁሉ-የመጨረሻዉም ሊሆን እንደማይችል ድርጅታቸዉ መረጃ አለዉ። ሞያሌ ሰላሟን ሊያስከብርላት በሚገባ ጦር ሠራዊት ነዋሪዎችዋ የተገደሉባት የገዢዉ ፓርቲ (ኢሕአዴግ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ሊቀመጥ ሲዘጋጅ፤ ተሰብሳቢዎች የሚመርጡ ጠቅላይ ሚንስትር ማንነት ሲያነጋግር ነዉ። የተቃዉሞ፤ ግድያ፤ የስብሰባ-ሹም ሽሩ ዑደት ሐገሪቱን ወዴት እያጓዛት ይሆን?-መልስ የለሽ ጥያቄ ።

የዶከተር አወል መልስ ኢትዮጵያ በጣም አጣብቂኝ ሁኔታ ዉስጥ ልትወድቅ ትችላለች የሚል ነዉ። አቶ ያሬድ ገዢዉ ፓርቲ ሠላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ቢመሽበትም አልጨለመበት ዓይነት ይላሉ። ዶክተር ዲማ ገዢዉ ግንባር ሕዝብን ለመግዛት ያለዉን አማራጭ ሁሉ ጨርሷል ባይ ናቸዉ። ዶከተር ዲማ እንደሚሉት ኢትዮጵያን ከባሰ ቀዉስ ለማዉጣት ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ብሔራዊ ጉባኤ መጠራት አለበት።ይሕን ሐሳብ ገቢራዊ ለማድረግ ፓርቲያቸዉ የሽግግር ቻርተር ያለዉን ረቂቅ ሐሳብ ማሰራጨቱንም አስታዉቀዋልም። ይሕ ካልሆነ ግን ያስጠነቅቃሉ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የዩኒቨርስቲ መምሕር እና የአምደ መረብ ፀሐፊ ስዩም ተሾመን ጨምሮ ቁጥራቸዉ በዉል ያልተነገረ ወጣቶችን ማሰር የጀመረዉ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን አዲስ አበባ ዉስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብን ነፃነት መገደብ ሳይሆን ሰፊ ነፃነት እንዲሰጠዉ በጠየቁበት ዋዜማ፤ ዕለት እና ማግሥት ነበር። የኢትዮጵያ መንግስትን የሚደግፉ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአዉሮጳ ሕብረትን የመሳሰሉ መንግሥታት ግን ደም አፋሳሹን እልቂት ለማስወገድ እስካሁን ያደረጉት ነገር የለም። ካለም ኢምንት ነዉ። ዶክተር አወል እንደሚመክሩት ኢትዮጵያዉን ከምዕራባዉያን መንግስታት ብዙ መጠበቅ የለባቸዉም።

ዶክተር ዲማ ነገዎ ግን ኃያሉ ዓለም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ መጣል እና የምጣኔ ሐብት ጫና ማድረግም ይገባዋል ይላሉ። ዩናይትድ ስቴትስ፤ የአዉሮጳ ሕብረት እና ብሪታንያ ማቅቀብ እና ጫና እንዲያደርጉ ፓርቲያቸዉ መጠየቁንም ዶክተር ዲማ አስታዉቀዋል። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

Audios and videos on the topic