የኢትዮጵያ ለውጥ በጀርመን መንግሥት ዕይታ  | ኢትዮጵያ | DW | 20.07.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ለውጥ በጀርመን መንግሥት ዕይታ 

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በኢትዮጵያ አስገራሚ እና ፈጣን ለውጦችን እውን አድርገዋል። ይህን መነሻ በማድረግ የጀርመን መንግሥት ስልታዊ ጠቃሚ አጋር ከሆነችው ከኢትዮጵያ ጋር በቅርብ ትብብር ለመሥራት አቅዷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:48

ለጀርመን ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ ቀንድ እጅግ አስፈላጊዋ ሀገር ናት

ለጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ በጣም ጥሩ ነው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ባለፈው ግንቦት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር መነጋገር ፈልገው ነበር። የጀርመን መንግሥት በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ለተወሰደው ለአዲሱ ተስፋ ሰጭ እርምጃ በይፋ ድጋፉን ማሳየት ይችል ነበር። ሆኖም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በውጭ ሀገር ጉብኝት ላይ ስለነበሩ ማስ ከርሳቸው ጋር አልተገናኙም። ያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሥልጣን ከያዙ ልክ አንድ ወራቸው ቢሆንም በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ለውጦች ተካሂደው ነበር። የተናገሯቸውን በፍጥነት ተግባራዊ አድርገዋል። ይህም ሀገሪቱን በቅርብ የሚያውቁትን አስገርሟል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነሳ፣ የፖለቲካ እሥረኞች ተፈቱ ለዓመታት በጠላትነት ትታይ ከነበረችው ከኤርትራ ጋር የሰላም ስምምነት ላይ ደረሱ። ጉንተር ኖከ የጀርመን መራሂተ መንግሥት የአንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ ጉዳዮች ተጠሪ ናቸው። ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ለውጡን አድንቀዋል።
« አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉንም ያስገረሙና ፣እያከታታተሉ በጎ እርምጃዎችን የወሰዱ ሰው ናቸው። በኔ እምነት የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስቴር እና የጀርመን መንግሥት ፣ሁላችንም በኢትዮጵያ ሁኔታዎች ሁሉ ወደ በጎ እየተቀየሩ መሆናቸው አስደስቶናል።»
የጀርመን መንግሥት ስለ ኢትዮጵያ አሁንም ይፋ መግለጫ ከመስጠት ይቆጠባል። ከጥቂት ቀናት በፊት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው አጭር መግለጫ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ስምምነት ላይ መድረሷን ተስፋ ሰጭ ብሎታል «በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ያጠፋው እና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያሰደደው ግጭት አሁን በዘላቂነት ሊፈታ ይችላል» ባይ ነው። 

Abiy Ahmed Äthiopien (picture-alliance/AA)

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ


ዶክተር ዐብይ በመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ጊዜያት በመንግሥታቸው ውስጥ  ጎልተው መውጣታቸው አስቀድሞ ግልጽ አልነበረም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በራሳቸው ፓርቲ በኢህአዴግ ውስጥ ሳይቀር ጠንካራ ተቃዋሚዎች ነበሯቸው።  ሰኔ 16፣2010 ዓም ህዝቡ ለለውጥ እርምጃቸው ድጋፉን ለመግለጽ በአዲስ አበባ ባካሄደው ሰልፍ ላይ የሁለት ሰዎች ህይወት የጠፋበት የቦምብ ጥቃት መድረሱ ይህን ግልጽ አድርጎታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መፍትሄ ሊፈልጉላቸው የሚገቡ በርካታ ችግሮችም አሉ። ከመካከላቸው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱት የጎሳ ግጭቶች ይገኙበታል። ከነዚህ ውስጥ የተመድ እንዳለው 800 ሺህ ህዝብ ያፈናቀለው የደቡብ ኢትዮጵያው ግጭት አንዱ ነው። 

SWP Dr. Annette Weber (SWP)

ዶ/ር አኔተ ቬበር


ጀርመን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በይፋ ቁጥብነት ብታሳይም ይህ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት አትፈልግም ማለት አይደለም። ጉንተር ኖከ እንዳሉት በጀርመን እይታ ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ ቀንድ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ሀገራት አንዷ ናት። በጀርመን እይታ በጂኦፖለቲካ  ረገድ በአፍሪቃ ቀንድ የኢትዮጵያ ሚና  ከሌሎች የአፍሪቃ አካባቢዎች እጅግ አስፈላጊው ነው። የጀርመን የልማት ተራድኦ መስሪያ ቤት እና የመንግሥታዊው የልማት ድርጅት የGIZ ትኩረት ከሚሰጣቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ጦርነት የሚካሄድባቸው ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ኢትዮጵያ አጠገብ ናቸው። ኢትዮጵያ በግጭት በሚታመሰው በዚህ አካባቢ ፀጥታ ለማስከበር ጥረት የምታደርግ አገር ናት። ይሁን እና ይህን እንቅስቃሴ በገዥው ፓርቲ በኢህአዴግ ላይ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በተካሄዱት ተቃውሞዎች ምክንያት እየቀነሰ ነበር። በጀርመን የሳይንስ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ጥናት ተቋም በምህጻሩ SWP የኢትዮጵያ ጉዳዮች አዋቂ አኔተ ቬበር እንዲህ እንደ አሁኑ ሁኔታዎች መለወጣቸው ከቀጠለ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪቃ የሚኖራት ሚና እስካሁን ከነበረው ከፍ ሊል ይችላል ብለዋል። 
« የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ  እና የፖለቲካው ሁኔታ ከተሻሻለ በሀገሪቱ መረጋጋት የመስፈኑ ግምት በጣም ያመዝናል። ሀገሪቱም ሙሉ በሙሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስታደርገው እንደነበረው በሀገር ውስጥ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ብቻ ማተኮሯን ትታ ኢትዮጵያ የጎላ አካባቢያዊ ሚና ልትጫወት ትችላለች። ይህን በቅርብ ዓመታት በትክክል ስታደርግ አልነበረም።»

Günter Nooke (picture-alliance/dpa/K. Nietfled)

ጉንተር ኖከ

 
ኢትዮጵኢ እና ጎረቤቷ ኤርትራ ከፍልሰት ፖሊቲካ እይታ ጠቃሚ ናቸው። ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚተላለፉባት ሀገር ናት። ኤርትራውያን ከዓለማችን ስደተኞች አራተኛ ደረጃን ይይዛሉ። ከሚሰደዱባቸው ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛው የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርናን መሸሽ ነው። ኤርትራ ብሔራዊ ውትድርናን ለመቀጧሏ ምክንያት የምታደርገው የጦርነት ስጋትን ነው። ይህ ከተቀየረ እንደ ኖከ ኤርትራውያን ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል። የጀርመን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ትብብሩን የማጠናከር ሥራ ጀምሯል። የከዚህ ቀደሙ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈላጭ ቆራጭ ስለነበረ እና ሰብዓዊ መብት በመጣሱ  የኢትዮጵያ እና ጋር የጀርመን  ግንኙነት አወዛጋቢ ነበር። ዶክተር ዐብይ ባስተዋወቁት የሃድሶ ምክንያት ይሄ ክርክር ጎልቶ ሊነሳ አይችልም። ከዚህ ሌላ ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው ሰላም ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ መልሳ መጠቀም ስትጀምር፣ የፖለቲካ ተሃድሶ በኤኮኖሚ ተሃድሶ ሲደገፍ መረጋጋት ሊመጣ ይችላል።ይህ ከሆነ የጀርመን ተቋማት ፍላጎት ያድርባቸዋል ብዮ አስባለሁ። ይህንንም ተቋማቱ በቦታው ተገኝተው መገምገም ይፈልጋሉ። ስለዚህ በመጪው ህዳር የጀርመን የአፍሪቃ የንግድ ማህበር ኢትዮጵያን ይጎበኛል።  

ኂሩት መለሰ /ዳንኤል ፔልስ 

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic