የኢትዮጵያው ሠፈራ-ዕቅድ | ኤኮኖሚ | DW | 22.04.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የኢትዮጵያው ሠፈራ-ዕቅድ

በየጊዜው ድርቅና ረሃብ በሚደጋገምባት ኢትዮጵያ የእህልን ምርት ለማበርከትና የምግብን እጥረት ለማስወገድ ይቻል ዘንድ፣ ከ፪ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ከደረቅ አካባቢዎች እየተነሱ ለም ወደሆኑት ቦታዎች እንዲዛወሩና እዚያው መልሰው እንዲሠፍሩ የሀገሪቱ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ በፊት ዕቅድ እንዳወጣ በመገናኛብዙሃን ተዘግቦአል።

ስለ ሠፈራው ርምጃ በመንግሥት ቃልአቀባይ የተሰጠው መግለጫ፣ ሀገሪቱን ከምግብ እጥረት ለማላቀቅ በተረጅው ሕዝብ በጎፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሠፊ የሠፈራ መርሐግብር የሚዘረጋ ሲሆን፣ አሁን መጀመሪያው እርከን ነው የሚንቀሳቀሰው ይላል። ግን ዓለምአቀፍ የርዳታ ድርጅቶችና ሌሎችም በሚያቀርቡት ማስጠንቀቂያ መሠረት፤ ቤተሰቦች መልሰው እንዲሠፍሩ የሚደረጉባቸው ቦታዎች ወባን የመሳሰሉት በሽታዎች አሁንም እንደተስፋፉባቸው የሚገኙ ናቸው፣ የጤና ጥበቃ ጣቢያዎች ይጓደሉባቸዋል፣ ትምህርትቤቶች የሏቸውም፣ በጠቅላላውም ሲነገር፥ በቂ ዝግጅት አልተደረገባቸውም። የሠፈራው ርምጃ በመሠረቱ ትክክል ሆኖ ሳለ፣ ከዚሁ ርምጃ በፊት አስፈላጊ የሚሆነው ቅድመ-ዝግጅት አለመደረጉ ብቻ ነው የሚነቀፈው።

ይኸው የሠፈራ መርሐግብር ያልተሟላና በቂ ዝግጅት ያልተደረገለት ሆኖ የሚያየው የአውሮጳው ኅብረትም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት--የመርሐግብሩ ይዘትና ፍጥነት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲታሰብበትና በተለይ ሊደቀን የሚችለው ሰብዓዊ፣ ኤኮኖሚያዊና የተፈጥሮ አካባቢያዊ እክል አስቀድሞ በጥንቃቄ መጠናት እንደሚገባው አሁን አጥብቆ ነው የሚያስገነዝበው።

የእልቂት አደጋ ለሚያሠጋቸው ሕዝቦች የሚቆረቆር አንድ የጀርመን ግብረሠናይ ድርጅትም ነው የኢትዮጵያን ሠፈራ መርሐግብር የነቀፈው። ርምጃው የጎሳን ውዝግብና ግጭት ሊያስከትል የሚችል ሆኖ የሚያየው ይኸው ድርጅት፣ ለዚሁ የቀውስ ዝንባሌ ምሳሌ አድርጎ የሚያቀርበው፣ በአምባገነን መንግሥቱ ኃይለማሪያም አገዛዝ ዘመን ከየመኖሪያ ቀያቸው እየተፈናቀሉ ለመልሶ ሠፈራ ወደሌሎች ቦታዎች የተወሰዱ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበትንና በአዲሶቹ ቦታዎች ዙሪያ የጎሳ ግጭት የገነፈለበትን ድርጊት ነው። አሁንም የተዘረጋው አዲሱ የሠፈራ መርሐግብር በቂ ዝግጅት የሌለበት፣ በነባሮቹና በአዲሶቹም ሠፋሪዎች መካከል የጥቅም ሚዛን ያልታከለበት ሆኖ ነው የሚታየው።

ብዙ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችም ናቸው፣ የመልሶ-ሠፈራው መርሐግብር ይብሱን አዳዲስ ችግሮችን የሚፈጥር እንደሚሆን የሚያመለክቱት። እዚህ ላይ በተለይ የሚጠቀሰው፣ “ሜድሳ* ሳ* ፍሮንቲየ”/ማለት “ሐኪሞች ያለድንበር” የተሰኘው ግብረሠናይ ድርጅት ወደ ሁለት ወራት ከሚጠጋ ጊዜ በፊት ያቀረበው ዘገባ ነው። በዚህም መሠረት፣ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሺህ ተዛዋሪዎች በሀገሪቱ ሰሜንምዕራብ ሁመራ ላይ እንዲሠፍሩ ከተደረጉ ወዲህ ፴፭ ሕፃናት የተገኙባቸው ሰባ ያህል ሰዎች ወባን በመሳሰሉ በሽታዎች እየተያዙ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ሁመራ ላይ በቂ የጤና ጥበቃ ጣቢያዎች ባለመኖራቸው ነው ሕክምናው ተጓድሎ ሠፋሪዎቹ ለሞት የተዳረጉት ይላል የግብረሠናይ ድርጅቱ ማስገንዘቢያ።

ሰሞኑን ደግሞ፣ አሰገደች ይበርታ ከአዲስ አበባ እንደዘገበችው፣ በሠፈራው መርሐግብር ተማልለው ከሐረር ወደ ኢሉባቦር አምርተው የነበሩ ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው የሠፈራውንም ዕድል ሳያገኙ ወደተነሱባቸው መንደሮች መልሰው እንዲያዘግሙ ግዴታ ነው የሆነባቸው። ይኸው በመቶ ኪሎሜትሮች የሚቆጠረው የዝግመት ጉዞ አደጋ ላይ ነው የጣላቸው። እነዚሁ መከረኞች ከዚያው ከኢሉባቦር ተነስተው በአዲስ አበባ በኩል ወደ ሐረር ለመመለስ የሞከሩበትን ሁኔታ ከቅርብ በመመልከትና እነርሱንም በማነጋገር አሰገደች ይበርታ አንድ ዘገባ አሰተላልፋልን ነበር።

ተዛማጅ ዘገባዎች