የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ በፍራንክፈርት ከተማ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 12.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ በፍራንክፈርት ከተማ

በምሁራን እና አገር ወዳድ ግለሰቦች የተመሰረተው የ " ሀገረ ብሄር ግንባታ " ፕሮጀክት የልዑካን ቡድን በውጭው ዓለም የሚኖረው የዲያስፖራው ማህበረሰብ በአገር ግንባታ ላይ የሚኖረውን ሚና ማጎልበት በሚቻልበት ሥልት ላይ ለመምከር ወደ አውሮፓ ያመራ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ መርሃ ግብሩን አንድ ብሎ ጀምሯል::

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:46

የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ በፍራንክፈርት ከተማ

በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ በፍራንክፈርት ከተማ ፍራንከንአሌ ባዘጋጀው በዚሁ የ "ሀገረ ብሄር ግንባታ"  የምክክር መድረክ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ አቶ ሚካኤል ሚናሴ እንዲሁም ሌሎች እንግዶች የተጋበዙ ሲሆን በጀርመን ነዋሪ ለሆኑ የተለያዩ ማህበራት አደረጃጀት ተወካዮች በልዩ ልዩ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና በግል እና በቡድን ተደራጅተው የረድኤት አገልግሎት ለሚያከናውኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሰላም በልማት በዴሞክራሲ ተቋማትና በአገር ግንባታ ዙሪያ በጥናት እና ምርምር የተደገፈ ልምድ እና ተሞክሮዋቸውን አካፍለዋል።

አንዳንድ አካባቢ የፖለቲካ አመራሩ ራሱ ገዳይ ወይም አስገዳይ ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ የመብት ተቆርቋሪ ሆኖ ይቀርባል ብሎ ራሱ መንግሥት መግለጫ በሚሰጥበት ሁኔታ እንዲሁም የክልል አመራሮችም በሌብነት እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ለህግ አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኝነት ካለማሳየታቸውም ሌላ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው እንዲፈጸምላቸው ጫና ለመፍጠር ተፈናቃዮችን በካምፕ እስከማገት መድረሳቸው በተረጋገጠበት አግባብ የዜጎች ሰብአዊ መብት እና ደህንነት ሳይጠበቅ ብሎም ህግና ሥርዓት ሳይከበር እንዴት አገርን መገንባት ይቻላል ስንል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ጥያቄ አቅርበን ነበር። "በኢትዮጵያ የመጣውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል መንግሥት የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ለማስጠበቅ በግል በቡድንም ይሁን በመንግሥት አመራር ውስጥ ሆነው ሕዝብን የሚያፈናቅሉ እና የብሄር ግጭቶችን የሚቀሰቅሱ ግለሰቦችን የወንጀል ድርጊት አጣርቶ ለህግ የማቅረቡን ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል " ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው መልስ ሰጥተዋል።

የሥነ ሀገር እና ሰብአዊ ገጽታን የመገንባት ሂደት ላይ ያተኮረው የ " ሀገረ ብሄር ግንባታ " ፕሮጀክት አስተባባሪ ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ በበኩላቸው በመላው ዓለም ከዲያስፖራው ማህበረብ ጋር በሚደረጉ ተከታታይ ውይይቶች በመንግሥት እና ፓርቲዎች መካከል መኖር ስለሚገባው ልዩነት ስለ ህግ የበላይነት መከበር ስለ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አደረጃጀት በለውጡ ሂደት ስላጋጠሙ ተግዳሮቶች እና መፍትሄዎቹ ለዘመናት ሲንከባለሉ የኖሩ የግጭት እና አለመግባባት ችግሮቻችን መንስኤዎችንም ከስር መሰረታቸው ለመፍታት ባህላዊ የዕርቅ ዕሴቶቻችንን መጠቀም እና ማጎልበት ስለሚቻልበት ስልት እንዲሁም በሀገረ ብሄር ግንባታ ዙሪያ ሰፊ ውይይቶችን በማካሄድ ፕሮጀክቱ የፖሊሲ ሃሳቦችን አርቅቆ ለመንግሥት የማቅረብ ስራ የፕሮጀክቱ ዓብይ አላማ መሆኑን ተናግረዋል።

 አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱን ማስተካከልና ሰላምና መረጋጋትን በመላው አገሪቱ ማረጋገጥ ከሁሉም ነገር በፊት ትኩረት የሚያሻቸው ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውም በምክክር መድረኩ በአጽንዖት ተገልጿል:: በመላ አገሪቱ ስር እየሰደደ የመጣው ሌላውን የማህበረሰብ ክፍል በጥላቻ የሚፈርጅ የዘረኝነት እና ብሄርተኝነት አስተሳሰብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጠናከር እና ለአገር ግንባታ ትልቅ እንቅፋት በመሆናቸው በጊዜ ሊታረሙ እንደሚገባቸውም ነው የተጠቆመው።

በክፍለ አህጉራችን አፍሪቃ የዲያስፖራው ማህበረሰብ በዕውቀት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር በጤና በግብርና በኢንዱስትሪና በተለያዩ የልማት ክፍለ ኢኮኖሚዎች የሚያበረክተውን ተሳትፎ ለማጠናከር እንደ ኬንያ ጋና ዩጋንዳ ናይጄሪያ እና ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ባሉ አገራት መንግሥታት አሳታፊ የዲያስፖራ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ጭምር አያሌ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋቸው በፍራንክፈርቱ ውይይት ላይ ያነጋገርናቸው ተሳታፊዎች ለአብነት ገልጸውልናል። ከምዕራቡ ዓለም የእርዳታ ጥገኝነት ተላቀን በራስ መተማመን እና በባለቤትነት መንፈስ አገራችንን ለመገንባት ብሎም ከድህነት ከመልካም አስተዳደር እጦት እና ከኋላቀርነት ለመላቀቅ ነጻ እና ገለልተኛ ማህበራትን ማጠናከርና የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በደንብ ማደራጀት ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ለአገር ግንባታ ወጣቶች የሚኖራቸው ሚና እጅግ የላቀ ነው ያሉት የውይይቱ ተካፋዮች በአሁኑ ወቅት የአብዛኛው ወጣት ሕይወት ሥራ በማጣት እና በልዩልዩ ማህበራዊ ችግሮች ፈተና ላይ በመውደቁ በሕዝብ ስቃይ ለሚነግዱ የፖለቲካ ቁማርተኞች እና ወንጀለኞች የጥፋት ተግባር መጠቀሚያ እየሆነ በመሆኑ አፋጣኝ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባልነው ያሉት:: መስዋዕትነት ከፍሎ ባመጣው ሕዝባችንም ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃትና ከመኖሪያ ቀዬው የማፈናቀል ወንጀል በሚፈጽሙ ግለሰቦችና የመንግስት አካላትም ላይ እንዲሁ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ ከ" የሀገረ ብሄር ግንባታ " ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማጠናከር እና አገሪቱንም መልሶ ለመገንባት የዲያስፖራው ሚና እጅግ የላቀ መሆኑም በፍራንክፈርቱ ውይይት የተወሳ ሲሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ሙያ እና ክህሎታቸውን ለወገኖቻቸው እንዲያካፍሉ ደክመው ያፈሩትንም መዋዕለ ንዋያቸውን በሚወዷት አገራቸው ላይ የህዝቡን ሕይወት በሚለውጡ የልማትና ኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በማዋል የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ ተላልፏል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች